ጋዛን በማይታመን ሁኔታ መልሶ ለመገንባት የትራምፕ እና የፍልስጤማውያን ፉክክር
ገና ባልጸና የተኩስ አቁም ውስጥ ያሉት የጋዛ ነዋሪዎች ረዥሙን እና አስቸጋሪውን የመልሶ ግንባታ ሂደት ጀምረውታል።
ቡልዶዘሮች መንገዶችን እየጠረጉ፣ ጦርነቱ ያፈራረሳቸውን እያነሱ በገልባጭ መኪኖች ላይ እየጫኑ ነው።
በአንድ ወቅት ግርግር እና ሁካታ የማይጠፋባት ከተማ የነበረችው አሁን የፍርስራሽ ክምር፣ የተጣመሙ ብረቶች ብቻ አግጥጠው የሚታዩበት ሆናለች።
የጋዛ ከተማ የተወሰነው ክፍል ሕይወት እንደነበረበት በማያስታውቅ መልኩ ፈራርሷል። ከመፈራረስ የተረፉት ሕንጻዎች አጽማቸው ቆሟል።
አቡ ኢያድ ሃምዶና "ይህ ቤቴ ነበር" በማለት በፍርስራሽ አርማታ እና ብረት የተሞላውን የሼክ ራድዋን አካባቢ ያሳያል።
ይህ አካባቢ በአንድ ወቅት በጋዛ ከተማ ከሚገኙ ሥፍራዎች ሁሉ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ የሚኖርበት ነበር።
"እዚህ ነበር። አሁን ግን ቤት የለበትም" ይላል።
የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
አቡ ኢያድ 63 ዓመቱ ነው። ጋዛ የተጫናትን አመድ አራግፋ ስትነሳ ለማየት በሕይወት ሊቆይ እንደሚችል አያስብም።
"በዚህ ፍጥነት 10 ዓመታት ይወስዳል ብዬ አስባለሁ" የተዳከመ እና የሰለቸው ይመስላል። "እንሞታለን... ዳግም ስትገነባ ሳናይ እንሞታለን።"
በአቅራቢያው፣ የ43 ዓመቱ ኒሃድ አል ማድሁን እና የወንድሙ ልጅ ሰይድ በአንድ ወቅት ቤታቸው የነበረው ስፍራ ላይ የተከመረውን ፍርስራሽ እያነሱ ነው።
አፅሙ የቆመው ሕንጻ ሊፈርስ ቢችልም ግድ የሰጣቸው አይመስልም። ከፍርስራሽ ውስጥ ጡብ እየሰበሰቡ ከአሮጌ ቀይ ሶፋ ላይ የአቧራ ክምር ያራግፋሉ።
"ፍርስራሾችን ማስወገድ ብቻ ከአምስት ዓመታት በላይ ሊወስድ ይችላል" ይላል። "እናም እንጠብቃለን ሌላ አማራጭ የለንም።"
የችግሩ ስፋት እጅግ ግዙፍ ነው። የተባበሩት መንግሥታት የጉዳቱን መጠን 70 ቢሊዮን ዶላር ሲል ገምቷል። የተባበሩት መንግሥታት የሳተላይት ማዕከል ዩኤንሳት እንደገለጸው ወደ 300 ሺህ የሚጠጉ ቤቶች እና አፓርታማዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል ወይም ወድመዋል።
የጋዛ ሰርጥ በ60 ሚሊዮን ቶን ፍርስራሾች የተሞላ ሲሆን፣ ይህም አደገኛ ከሆኑ ያልፈነዱ ቦምቦች እና አስከሬኖች ጋር ተደባልቆ ይገኛል።
የሐማስ ጤና ሚኒስቴር በአጠቃላይ ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ከ68,000 በላይ ሰዎች በጋዛ ተገድለዋል ይላል።
በእንደዚህ ዓይነት ውድመት መካከል፣ ከየት መጀመር እንደሚያስፈልግ ማወቅ አስቸጋሪ ነው።
የሃሳብ እጥረት የለም። በርቀት በሚገኙ አገራት የሚኖሩ እና ገንዘብ እና ሥልጣን ያላቸው አካላት ታላላቅ ንድፎችን አቅርበዋል። የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕም የራሳቸውን አስተያየት ሰጥተዋል።
ነገር ግን ያነጋገርናቸው የጋዛ ነዋሪዎች በውጭ አገር ስለሚዘጋጁ ዕቅዶች ጥርጣሬ አላቸው። ከምንም በላይ ደግሞ የራሳቸው ራዕይ አላቸው። ስለዚህ ትግሉ የጋዛን የወደፊት ዕጣ ፈንታ ለመቅረጽ ነው።
ጥያቄው ማን ያሸንፋል? የሚለው ነው።
ከትራምፕ ሪቬራ እስከ ፊኒክስ ዕቅድ
በጋዛ ከተማ በሐማስ የተሾመው ከንቲባ ያህያ አል ሳርራጅ ጃኬት ለብሶ መንገድ ላይ በመውጣት ፍርስራሹን ይቃኛል። ሱቆች እና ምግብ ቤቶች እንደገና መከፈት እንደጀመሩ ይናገራል።
"በእርግጥ በጣም መጠነኛ ነው" ካለ በኋላ "ነገር ግን መኖር ይፈልጋሉ፤ መኖርም ይገባቸዋል።"
ሐማስ በእስራኤል ላይ በመስከረም 26/2016 ዓ.ም. የፈጸመውን ድንገተኛ ጥቃት ተከትሎ ከተቀሰቀሰው ጦርነት በፊት በርካታ ግጭቶችን ማስተናገዷን በማስታወስ ጋዛ ለእንደዚህ ዓይነት ውድመት እንግዳ አይደለችም ሲል አክሏል።
"ብዙ ዕቅዶችን ሰምተናል። ከዓለም አቀፍ፣ ከአገር ውስጥ፣ከቀጠናው አገራት የመጡ ዕቅዶችን ሰምተናል። [ነገር ግን] የራሳችን ዕቅድ አለን።
"የጋዛው ፊኒክስ ብለን እንጠራዋለን።"
ይህ በጦርነቱ ወቅት የተገኘ እዚሁ ጋዛ ውስጥ የበቀለ የፍልስጤም የመጀመሪያው ዕቅድ ነበር። በኮምፒዩተር በተሠራ ቪዲዮ የታጀበው ይህ ዕቅድ የተጎሳቆሉ ማኅበረሰቦች ሲለወጡ፣ አካባቢውም ወደ ዘመናዊ መኖሪያነት ሲለወጥ ያሳያል።
ኢራቅን ጨምሮ በግጭት አካባቢዎች የ30 ዓመት ልምድ ያካበቱት የዓለም ባንክ የቀድሞ ከፍተኛ ሥራ አስኪያጅ፣ ያራ ሳሌም "ክፍተቱን መሙላት እንፈልጋለን" ብለዋል።
"ስለ አገርህ ምንም ዓይነት ራዕይ ሳይኖርህ በውጭ አገር የተቀረፁ የመልሶ ግንባታ ዕቅዶች ሊኖሩህ አይችሉም።"
ለ13 ወራት ወደ 700 የሚጠጉ ፍልስጤማውያን የምህንድስና ባለሙያዎች ሲሠሩ የቆዩትን የመልሶ ግንባታ ዕቅድ፣ የፊኒክስ ዕቅድ በየካቲት ወር ይፋ አድርገዋል።
እነዚህ ባለሙያዎች አብዛኛዎቹ መቀመጫቸውን በተለያዩ አገራት ቢያደርጉም፤ የተወሰኑት ግን አሁንም በፍልስጤም ውስጥ ይኖራሉ።
በጋዛ ሰርጥ ውስጥ ባሉ አርክቴክቶች እና መሐንዲሶች እውቀት እና ልምድ ላይ የተመሠረተ ነው። በእስራኤል በወረራ በተያዘው ዌስት ባንክ የሚገኘው የቢርዘይት ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችም ሃሳቡን በማዳበር ላይ ተሳትፈዋል።
በማዘጋጃ ቤቶች ላይ ፖለቲካዊ ቁጥጥር የሚያደርገው ሐማስ በዕቅዱ ላይ አልተሳተፈም።
ዛሬ፣ የፊኒክስ ፕላን ፈጣሪዎች የዕቅዳቸው ዕጣ ፈንታ ተፎካካሪ ዕቅዶች ከመካከለኛው መሥራቅ እና ከሌሎች አካባቢዎች መምጣታቸውን ተከትሎ ከእጃቸው እንደወጣ፣ እንዲሁም የጋዛን የወደፊት ዕጣ ፈንታ ለመቆጣጠር እንደሚቸገሩ ያውቃሉ።
ይህ ራዕይ በየካቲት ወር የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እና ዶናልድ ትራምፕ በዋይት ሐውስ በተገናኙበት ወቅት ከተገለፀው አወዛጋቢ ሀሳብ "ጋዛ ሪቪዬራ" ጋር በእጅጉ ተቃራኒ ነው።
የፎቶው ባለመብት, Phoenix
ትራምፕ በኤአይ የተሠራ ተንቀሳቃሽ ምሥል በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ያጋሩ ሲሆን፣ ከኔታንያሁ እና ከቢሊየነሩ ኤሎን መስክ ጋር ሆነው በዱባይ መልክ በተሠራው ከተማ ላይ ሲዝናኑ ይታያል።
በምሥሉ ላይ የፕሬዝዳንቱ ግዙፍ ወርቃማ ሐውልት በአውራ ጎዳናው አደባባይ ከፍ ብሎ የተቀመጠ ሲሆን፣ አረንጓዴ ሻሽ ጭንቅላቱ ላይ ያሰረ ፂማም ወንድ ደግሞ በባሕር ዳርቻው ላይ ሲደንስ ይታያል።
ምንም እንኳን ቪዲዮው ተመሳስሎ የተሠራ ቢሆንም፣ ፕሬዝዳንት ትራምፕ አሜሪካ ጋዛን "በረጅም ጊዜ ባለቤትነት" እንደምትወስድ አስቀድመው ተናግረዋል።
የትራምፕ አማች የሆነው ጃሬድ ኩሽነር ባለፈው ዓመት በሐርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ለተገኙ ታዳሚዎች "ሰዎች ኑሯቸውን መገንባት ላይ ካተኮሩ የጋዛ የውሃ ዳርቻ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ በጣም አዋጭ ሊሆን ይችላል" ብሏል።
በጥቅምት ወር በትራምፕ መሪነት ከስምምነት ላይ የተደረሰበት ባለ 20 ነጥብ የጋዛ የተኩስ አቁም ሀሳብ "ጋዛን መልሶ መገንባት እና ኢኮኖሚዋን ማነቃቃት" የሚል ሃሳብ ሰፍሯል።
ከዚህም በተጨማሪ የመንግሥት አስተዳደሩን የቀድሞው የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌር ይመሩታል ተብሎ የሚጠበቀው የዓለም አቀፍ "የሰላም ቦርድ" እንደሚይዘው ይገመታል።
የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በቴክኖሎጂ የበለፀጉ "ስማርት ከተሞች"
የወደፊቷ ጋዛን በሚመለከት ብቅ ያለው ዕቅድ ግን የትራምፕ "የጋዛ ሪቪዬራ" ብቻ አይደለም።
በነሐሴ ወር በዋሽንግተን ፖስት የታተመው ሾልኮ የወጣ ሰነድ እንደሚያሳያው የጋዛ ሰርጥ ለ10 ዓመት በዩናይትድ ስቴትስ ባለአደራ ስር በመሆን በከፍተኛ ቴክኖሎጂ የታገዘች ከተማ የማድረግ ዕቅድን ይዟል።
የጋዛ መልሶ ግንባታ፣ የኢኮኖሚ ማሳለጥ እና ትራንስፎርሜሽን ትረስት የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ ዕቅድ በአጭሩ ሲጠራ "ግሬት" ይሰኛል።
ዕቅዱ የእስራኤል እና የአሜሪካ አማካሪዎች ነው የተባለ ሲሆን ከቶኒ ብሌየር የዓለም አቀፍ ለውጥ ኢንስቲትዩት አባላት የተገኘ ሃሳብ ተካትቶበታል።
ዕቅዱ ተከታታይ "ዘመናዊ እና በኤአይ [ሰው ሠራሽ አስተውሎት] የታገዘ ስማርት ከተሞችን" ለመፍጠር ያቀደ ሲሆን "በጋዛን አለመረጋጋት ውስጥ" ደካማ የሆነ የከተማ ዕቅድ እጅ አለበት ይላል።
የፎቶው ባለመብት, Great
በዕቅዱ ስር የተጻፈው ጽሑፍ በትራምፕ የመጀመሪያ ፕሬዝዳንታዊ የሥልጣን ዘመን ላይ የተደረሰውን የአብርሃም ስምምነት በሚያመለክት መልኩ "ከፈራረሰች የኢራን ተቀጥላ ወደ የበለፀገች የአብርሃም አጋር" የሚል ጽሑፍ ተቀምጧል።
ይህም መልሳ የምትገነባው ጋዛ በቀጠናው ግዙፍ የሰላም ጥረት አካል ሊሆን እንደሚችል ይጠቁማል።
ዕቅዱ በተጨማሪም "በፈቃደኝነት ወደ ሌላ ቦታ መዘዋወር" የሚለውን ሀሳብ ያነሳ ሲሆን፣ በዚህ ስር አንድ አራተኛው የጋዛ ሕዝብ ከሰርጡ ወጥቶ በምላሹም 5,000 ዶላር የመቋቋሚያ ገንዘብ ይሰጣቸዋል።
ይህ የጋዛን ነባር መሠረተ ልማት ለመጠበቅ እና ከተቻለም የአካባቢውን ማኅበራዊ እና መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ለመጠበቅ ከሚያልመው የፊኒክስ ዕቅድ ጋር በተቃራኒ የቆመ ነው።
የፍልስጤም የኢኮኖሚ ፖሊሲ ጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ራጃ ካሊዲ "እንዲህ ዓይነት በቅዠት የተሞሉ ዕቅዶች አውዳሚ ለሆነ ካፒታሊዝም ክፍተት እየፈጠሩ ነው" ሲሉ ይከራከራሉ።
"የአገሪቱ መንግሥት የማቀድ አቅም አለው... ምን ዓይነት ጋዛ መገንባት እንደምንፈልግ፣ ስንገነባ ምን ያህል እንደሚያስወጣን ማቀድ እንችላለን። ይህ የፍልስጤማውያን ራዕይ መሆን አለበት - የእኔ ስጋት ወደ ጎን እንገፋለን የሚል ነው።"
የፎቶው ባለመብት, Reuters
መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገው ራንድ (RAND ) የተሰኘው የምርምር ቡድን ውስጥ ከፍተኛ ተመራማሪ እና በጋዛ መልሶ ግንባታ ላይ ዝርዝር ጥናት ያቀረቡት ሼሊ ኩልበርትሰን የጋዛ ሰርጥ በቀላሉ ወደ ዱባይ ለመለወጥ የተዘጋጀ ምድረ በዳ አይደለም ይላሉ።
"ለሺህ ዓመታት የቆዩ ብዙ ቅርሶች፣ ከተሞች አሉ፤ ሁሉንም ማጥፋት እና እንደገና መጀመር ጥሩ ልምምድ አይደለም፤ ይልቁንም ባለው ነገር ላይ መገንባት የተሻለ ነው።"
"የጋዛ ነፍስ እና መንፈስ"
ይሁን እንጂ በጋዛ መልሶ ግንባታ ላይ የቀረቡት ዕቅዶች እነዚህ ብቻ አይደሉም።
ሌላው በግብፅ በችኮላ ተዘጋጅቶ በመጋቢት ወር በካይሮ በተካሄደው የአረብ ሊግ ስብሰባ ላይ ቀርቦ ተቀባይነት ያገኘው ዕቅድ ጋዛን በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ እንደገና ስለመገንባት ያትታል።
እንደ ፊኒክስ ዕቅድ የጋዛ ነዋሪዎችን "የባለቤትነት ስሜትን ለማጎልበት እና የአካባቢው ማኅበረሰብ ፍላጎቶች መሟላታቸውን ለማረጋገጥ" በሚል በሁሉም ደረጃ ማሳተፍ አስፈላጊ መሆኑን አፅንዖት ሰጥቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በፕሬዝዳንት ማህሙድ አባስ የሚመራው የፍልስጤም አስተዳደር ለጋዛ ሰርጥ የራሱን ዕቅድ በማዘጋጀት ላይ ይገኛል። ይህም ጋዛን እና በወረራ የተያዘውን ዌስት ባንክን በወደፊቷ የፍልስጤም ግዛት እንደገና ለማገናኘት ያለው ሰፊ ዕቅድ አካል ነው።
የፍልስጤም አስተዳደር የዕቅድ ሚኒስቴር ሚኒስትር፣ ኢስቴፋን ሳላሜህ በራማላህ በሚገኘው ቢሯቸው የፍልስጤም አስተዳደር ምንም ዓይነት የተለየ ዕቅድ እየነደፈ መሆኑን አብራርተዋል፤ ነገር ግን አንዳንድ ነገሮች በነበሩበት መልኩ እንደማይቀጥሉም ያስረዳሉ።
የፎቶው ባለመብት, Great
"70 በመቶ የጋዛ ሕዝብ ስደተኛ መሆኑን አትዘንጉ" ብለዋል። "እና የስደተኛ ማንነትን መጠበቅ አለብን፤ የጋዛን ነፍስ እና መንፈስ መጠበቅ አለብን።"
ለሳላሜህ፣ ይህ ማለት እአአ በ1948-9 በእስራኤል ምሥረታ ወቅት በተካሄደው ጦርነት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ተሰደድው እና ተፈናቅለው የመሠረቱትን የጋዛ የስደተኞች መጠለያን እንደገና መፍጠር ማለት ነው።
በጊዜ ሂደት፣ እነዚህ መጠለያዎች በ1950ዎቹ ከነበሩበት የሸራ ድንኳኖች ወደተጨናነቁ እና ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ ወደሚኖርባቸው ቆርቆሮ ቤቶች ተለውጠዋል።
የፍልስጤም አስተዳደር ዕቅዱ የተጎሳቆሉ የመኖሪያ አካባቢዎችን ዳግም መፍጠር ሳይሆን ጥብቅ ትስስር ያላቸው ማኅበረሰቦች ወደነበሩበት መመለስ መቻላቸውን ማረጋገጥ ነው ይላል።
ሳላሜህ በአንድ ወቅት ከ100 ሺህ በላይ ሰዎች ይኖሩበት የነበረውን ትልቁን ካምፕ በማጣቀስ "ጃባሊያ ባለበት ዳግም እንዲገነባ እንፈልጋለን" ብለዋል።
ነገር ግን ለጊዜው የፍልስጤም አስተዳደር አገዛዝ በዌስት ባንክ ላይ እንጂ በጋዛ አይደለም።
የትራምፕ የጋዛ የተኩስ አቁም ዕቅድ የሰላም ቦርዱ የጋዛን መልሶ ግንባታ "የፍልስጤም አስተዳደር የማሻሻያ መርሃ ግብሩን እስከሚያጠናቀቀ ድረስ" እንደሚቆጣጠር ይናገራል።
አዝጋሚው እና አድካሚው የመልሶ ግንባታ ጉዞ
መልሶ መገንባት አዝጋሚ፣ እና አድካሚ ሂደት ነው። ሼሊ ኩልበርትሰን "የከተሜነት መጨመር" በማለት በጥንቃቄ መሥራት እንዳለበት ይመክራሉ።
"በፈራረሱ ነገር ግን መኖር በሚችሉ ማኅበረሰቦች ውስጥ መኖር እና እነርሱ እዚያው እያሉ መልሶ መገንባት ማኅበረሰቦችን ለመጠበቅ እና ሰዎች ወደ መኖሪያቸው እንዲመለሱ ለማድረግ ቁልፍ መንገድ ይሆናል ብለን እናስባለን" ሲሉ አክለዋል።
"[ነገር ግን] አንዳንድ ቦታዎች በጣም በመውደማቸው እና በመጎዳታቸው የተነሳ አደገኛ ስለሆኑ ማድረግ የሚቻለው ግድግዳውን ማፍረስ እና ሙሉ በሙሉ እንደገና መገንባት ነው። ይህ ግን የአምስት ዓመት ሥራ ብቻ አይሆንም፤ ምናልባት አሥርተ ዓመታትን ይወስዳል።"
የፎቶው ባለመብት, Anadolu via Getty Images
የፍልስጤም ባለሥልጣን የዕቅድ ሚኒስትር ፈጣን የጊዜ ሰሌዳን እንደሚጠቀሙ በመናገር ነገርግን የፖለቲካ እና የደኅንነት ሁኔታዎች እስካልተስተካከሉ፣ ድንበሮች ክፍት እስኪሆኑ (የግንባታ ቁሳቁሶችን ለማስገባት) እና የገንዘብ ድጋፍ እስካልተገኘ ድረስ ምንም ነገር ሊጀምር አይችልም ብለዋል።
ዋነኛው ተግዳሮት ደግሞ ያ ነው።
ዓለም አቀፍ ለጋሾች ጋዛን መልሶ ለመገንባት የሚያስፈልገውን በአስር ቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ቃል እንዲገቡ ለማድረግ፣ የማገገሚያ ዕቅዱ ምን እንደሚመስል ስምምነት ላይ መደረስ አለበት።
ግብፅ የመልሶ ግንባታ ጉባኤ ለማካሄድ አቅዳለች፤ ነገርግን ቀን እስካሁን ድረስ አልተወሰነም። እና ምናልባትም የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርጉት አገራት ሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ትልቅ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰሳቸው ወደፊት በሚከሰት የጋዛ ጦርነት ውስጥ በቀላሉ ዶግ አመድ እንዳይሆን ማረጋገጫ ያስፈልጋቸዋል።
አሁን ያለው የእስራኤል መንግሥት ግን የፍልስጤም አገር መመሥረትን አጥብቆ እየተቃወመ ሳዑዲ አረቢያ ደግሞ ምሥረታውን እየደገፈች የፖለቲካ መሰናክሎች አይኖሩም ብሎ መገመት የዋህነት ነው።
የፎቶው ባለመብት, Reuters
እስራኤል ከተለያዩ አገራት የሚመጡ ባለሃብቶች በጦሩ ቁጥጥር ስር ያሉ አካባቢዎችን መልሶ መገንባት ቢጀምሩ እንደማትቃወም ገልጻለች።
ጃሬድ ኩሽነር በቅርቡ በእስራኤል ባደረገው ጉብኝት አሁንም በእስራኤል ወታደራዊ ቁጥጥር ስር ባለው ግዛት ላይ "አዲስ ጋዛ" ስለመገንባት ተናግሯል። ምንም ዓይነት የመልሶ ግንባታ ገንዘብ በሐማስ ቁጥጥር ስር ወደሚገኙ አካባቢዎች እንደማይሄድም ጨምሮ ገልጿል።
ነገር ግን የጋዛ የተኩስ አቁም ረግቶ ባልቆመበት ሁኔታ እና እስራኤል እና ሐማስ አሁንም አልፎ አልፎ እየተታኮሱ ምንም የረባ ነገር መጀመር አይቻልም።
ወደፈራረሰው የጋዛ ከተማ የሼክ ራድዋን አካባቢ ስንመለስ አቡ ኢያድ ሃምዱና ቶሎ ምላሽ ማግኘት ያለባቸው ስጋቶች አሉት።
"ዳግም ግንባታ?" በመደነቅ ይጠይቃል። "ውሃስ?"
በጦርነቱ ወቅት ለአምስት ያህል ጊዜ በግዳጅ ከተፈናቀሉ በኋላ አቡ ኢያድ ባገኘው በማንኛውም መጠለያ ውስጥ መኖር ወይም ለራሱ የሚኖርበትን መገንባት ይፈልጋል።
እሱ ፊኒክስ የጋዛን ፍርስራሽ ፈንቅላ እስክትነሳ ወይም በእርግጥ የጋዛ ሪቪዬራ እውን እስኪሆን አይጠብቅም።
"እነሆ እኛ ድንኳን እየሠራን ነው" ይላል። "አሁንም መኖር ከማይቻልበት ቤት አጠገብ፤ ድንኳን እየሠራን ተቀምጠናል።"
እንዳያመልጥዎ
ከየፈርጁ
በስፋት የተነበቡ
የሚፈልጉት ይዘት የለም