ከጦርነቱ ማብቃት በኋላ ጋዛን ማን ይቆጣጠራል? እያወዛገበ ያለው መጻኢው የጋዛ ዕጣ ፈንታ

የእስራኤል ጦር ታንኮች በአቧራማ መንገድ ላይ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ ንግግር እየተደረገ ባለበት ወቅት፣ እስራኤል በሰርጡ ላይ የምታካሂደውን ወታደራዊ ዘመቻ አጠናክራ በመቀጠል ጋዛ ከተማን ለመቆጣጠር የሚያስችል ዕቅድ አጽድቃለች።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የእስራኤል ጦር መላውን የጋዛ ሰርጥ እንዲቆጣጠር እንደሚፈልግ አስታውቀዋል።

በዕቅዱ መሠረት ወታደሮቹ ሐማስን ሙሉ በሙሉ በማፍረስ ግዛቱን በሙሉ በአሜሪካ ቁጥጥር ስር ለሆኑ የአረብ ኃይሎች ያስረክባሉ።

የኔታኒያሁ ምክረ ሀሳብ የእስራኤል የቀኝ ክንፍ ፖለቲከኞች ድጋፍ አለው።

ነገር ግን ዕቅዱ በሐማስ የታገቱት የእስራኤላውያን ቤተሰቦች እና ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የዓለም አገራት ተቃውሞ ገጥሞታል።

የእስራኤል የፀጥታ ካቢኔ የጋዛ ከተማን የመቆጣጠር ዕቅድ መላውን ጋዛ ሰርጥ መቆጣጠር የሚለውን ሳይጠቅስ አጽድቆታል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዳለው ከሆነ 87 በመቶ የሚሆነው የጋዛ ክፍል አሁን በወታደራዊ ቀጠናዎች ውስጥ ወይም ከእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ልቀቁ የሚል ትዕዛዝ የተሰጠበት አካባቢ ስር ነው።

ካርታ

የውጭ የፀጥታ ኃይሎች

የጋዛ ፀጥታን ለመቆጣጠር ጋዛን ለውጭ ኃይሎች አሳልፎ መስጠት የሚለው አዲስ ሀሳብ አይደለም።

ይህ ምክረ ሃሳብ በ2023 መጨረሻ ላይ በአንዳንድ የአረብ አገራት በተለይም በዮርዳኖስ ውድቅ ተደርጓል።

የዮርዳኖስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አይማን ሳፋዲ "ወደ ጋዛ የሚሄድ የአረብ ጦር አይኖርም፤ እንደ ጠላት መታየት አንፈልግም" ብለዋል።

በግንቦት 2024 በቀድሞው የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ዮአቭ ጋላንት "ከጦርነት በኋላ" በሚል ባቀረቡት ምክረ ሀሳብ ላይ ተመሳሳይ ነጥብ ተጠቅሷል።

የእስራኤል ጋዜጣ ሃሬትዝ አምደኛ የሆኑት የቀድሞው የእስራኤል ዲፕሎማት አሎን ፒንካስ ለቢቢሲ "በተግባር የትኛውም አረብ አገር የዚያ ዕቅድ አካል ሊሆን አይችልም፤ በተለየ ሁኔታ የፍልስጤም ባለስልጣን ካልጠየቃቸው በስተቀር" ብለዋል።

የፍልስጤም አስተዳደር የጋዛ ሰርጥ ከዌስት ባንክ የመለየት ዕቅድን "የእስራኤል ፕሮጀክት" ብሎ በመጥራት ውድቅ አድርጎታል።

ካርታ

የጋዛ ሰርጥ የፍልስጤም ግዛት ዋና አካል ነው ሲል አቋሙን ገልጾ፣ የጋዛ አስተዳደር የፍልስጤም አስተዳደር እና የፍልስጤም መንግሥት ብቸኛ ኃላፊነት ነው ብሏል።

ባለፈው ሚያዝያ ወር ግብፅ እና ዮርዳኖስ የጋዛ ሰርጥን እንደገና ለመገንባት በቀረበ ሀሳብ ላይ ተስማምተዋል።

ይህ ከጦርነቱ በኋላ የፍልስጤም ፖሊሶች ወደ ጋዛ እንዲሰማሩ ማሠልጠንን ያካትታል።

በዚህ ሳምንት የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አብደላቲ እንዳሉት አገራቸው ከጦርነቱ በኋላ 5,000 የፍልስጤም ፖሊሶችን በጋዛ ለማሰማራት ማሠልጠን ጀምራለች።

የፍልስጤም የዜና ወኪል ማአን ምንጮቹን ጠቅሶ እንደዘገበው "አሁን እየተካሄደ ያለው ድርድር የተኩስ ማቆም እና የእስራኤል ጦር ከጋዛ ሰርጥ መውጣቱን እና በአሜሪካ ቁጥጥር ስር ያሉ የአረብ ጦር ኃይሎች መግባታቸውን ያካትታል።"

አክሎም "የመልሶ ግንባታውን ሂደት ከመቆጣጠር በተጨማሪ የሲቪል ጉዳዮችን እና ደኅንነትን የሚቆጣጠር የፍልስጤም ገዥ ሹመት እንደሚኖር ተነግሯል።"

የትኞቹ አገራት ይህንን ኃይል እንደሚቀላቀሉ እና እስራኤል እና ሐማስ ምን ያህል በዚህ ጉዳይ ላይ እንደሚስማሙ በዝርዝር አልተገለፀም።

መሳሪያቸውን ይዘው የደንብ ልብሳቸውን ለብሰው በመደዳ የቆሙ የሐማስ ወታደሮች

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, እስራኤል ሐማስን ማፍረስ ቀዳሚ ከሆኑት ጥያቄዎቿ መካከል ዋነኛው ነው

"የደኅንነት ራስ ምታት"

የዩናይትድ ኪንግደም የቀድሞ የመካከለኛው ምሥራቅ ሚኒስትር አልስታይር በርት የአረብ ጦርን ወደ ጋዛ የመላክ ሀሳብ "ተግባራዊ ሊሆን የሚችል ውጤት ይመስላል፤ ነገር ግን ቀላል ሥራ አይሆንም" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በርት አክለውም ወደዚህ መፍትሄ ለመድረስ ከሐማስ፣ ከእስራኤ�� እና ከሚመለከታቸው አገራት ጋር ወታደሮቻቸውን ወደ ጋዛ ከመላካቸው በፊት "ትክክለኛ ስምምነት" መደረግ አለበት ብለዋል።

"የትኛውም የአረብ አገር እንደዚያ የሚያደርግ አይመስለኝም። ለምንድን ነው ወታደሮቻቸውን አደጋ ላይ የሚጥሉት? በሚኖረው ደኅንነት ላይ ሙሉ በሙሉ ስምምነት መደረግ አለበት" ብለዋል።

"የአረብ ጦር ጥቃት እንደማይደርስባቸው ማረጋገጥ አለባቸው።"

በርት ሐማስ መስከረም 26/2016 ዓ.ም. የፈጸመው ጥቃት በእስራኤል የወደፊት የፀጥታ ዕቅድ ላይ ወሳኝ የሆነ አዲስ ገጽታን ይጨምራል ብሏል።

ቡድኑ በእስራኤል ላይ ታይቶ የማይታወቅ ጥቃት በመፈጸም ወደ 1,200 የሚጠጉ ሰዎችን ገድሎ ሌሎች 251 ሰዎችን አግቷል።

"መስከረም 26 በእስራኤል ዕይታ በጣም ትልቅ ቀን ነው። የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት እዚያ ካልተገኘ እስራኤል ደኅንነቷ መጠበቁን ማን ያረጋግጣል። ይህንን ዓለም አቀፍ ኃይሎች መልስ መስጠት አለባቸው።"

በርት የጋዛን የፀጥታ ሁኔታ እንደ "ራስ ምታት" ሲገልጹት "በወንበዴዎች፣ በጠመንጃ እና በሕገወጥ ገንዘብ የተጨማለቀች ነው" በማለት ነው።

"በተራው ሕዝብ ላይ ጥቃት ሳይደርስ ወይም ንብረቱ ሳይዘረፍ ወደ ጉዳዩ ለመሄድ በበርካታ ረገዶች ራስ ምታት ነው።"

የእስራኤል ታንክ ሁለት ወታደሮችን ጭኖ አጥሩን ለማጠናከር ሲንቀሳቀስ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, የእስራኤል መካለከያ የጋዛ ከተማን በኃይል ተቆጣጥሮ ከሐማስ ጋር ውጊያ እያካሄደ እገኛል

ሐማስን ትጥቅ ማስፈታት

የአረብ የስትራቴጂክ ጥናት ተቋም ኃላፊ ጄነራል ሳሚር ራጌብ ለቢቢሲ ኒውስ አረብኛ እንደተናገሩት "የአረብ ጦርን ወደ ጋዛ ሰርጥ ለመላክ ሐማስ መሳሪያውን መፍታት አለበት" ብለዋል።

ራጌብ እንዲህ ባለው ኃይል ውስጥ ለመሳተፍ ፈቃደኛ የሆነ አንድም የአረብ አገር የለም ብለዋል።

ሆኖም የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አብዴላቲ በዚህ ሳምንት እርምጃው የፍልስጤም አስተዳደር "መንግሥትን ለማካተት" እና የሁሉንም ወገኖች ደኅንነት ለማረጋገጥ የሚያስችል ከሆነ አገራቸው በጋዛ የሚሰማሩትን ዓለም አቀፍም ሆነ ክልላዊ ኃይሎች አትቃወምም ብለዋል።

ራጌብ ግን "ሐማስ ይህንን ምክረ ሃሳብ እስራኤል ሙሉ በሙሉ ከሰርጡ እንደምትወጣ ዋስትና ከሚሰጥ አጠቃላይ የሰፈራ ማዕቀፍ በስተቀር አይቀበለውም። ምክንያቱም ከእንደዚህ ዓይነት ኃይል ጋር መስማማት ማለት ሐማስን ትጥቅ ማስፈታት ማለት ነው" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

በመቀጠልም "ይህ ማለት ሐማስ ወደ ሰርጡ የፀጥታ ቁጥጥር አይመለስም ማለት ነው። እናም ተደራዳሪዎች የፍልስጤም ኃይል በጋዛ ውስጥ ያለውን የፀጥታ ሁኔታ ለመረከብ እስኪዘጋጅ ድረስ የሚተካ ጦር በማቋቋም ላይ ናቸው ማለት ነው።"

አለመግባባቶች

አጠቃላይ እልባት ላይ ለመድረስ እስራኤል እና ሐማስ ያልተስማሙባቸውን ጉዳዮች መፍታት እንደሚያስፈልግ ራጌብ ጠቁመዋል።

"ሐማስ የጠየቃቸው እና እስራኤል የተቃወመቻቸው ነጥቦች ጦሯ ሙሉ በሙሉ ከሰርጡ እንዲወጣ የሚለውን እና ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን በማቆም መልሶ ግንባታ ይጀመር የሚለውን ነው።"

እስራኤል በበኩሏ ሐማስ ትጥቁን እንዲፈታ፣ የቡድኑ መሪዎች ጋዛን ለቅቀው እንዲወጡ እና ከሐማስ ወይም ከፋታህ ጋር ግንኙነት የሌለው መንግሥት ይቋቋም የሚል ሀሳብ ማቅረቧን ራጌብ ተናግረዋል።

መጋቢት ወር ላይ የተካሄደው የአረብ አገራት ጉባዔ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ግብጽ በጋዛ የሚካሄደው ጦርነት እንዲቆም የተለያዩ ውይይቶችን አድርጋለች

ድርድር በካይሮ

ረቡዕ ዕለት የሐማስ ቡድን ከግብፅ ተደራዳሪዎች ጋር ለመነጋገር ካይሮ ገብቷል።

የግብፅ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማምሻውን እንደገለፁት ጦርነቱ ካበቃ በኋላ 15 ከፍልስጤም የፖለቲካ ቡድኖች ጋር ግንኙነት የሌላቸው 15 ሰዎች ሰርጡን ለስድስት ወራት ለማስተዳደር ተዘጋጅተዋል።

በምክረ ሃሳቡ መሠረት የፍልስጤም ባለሥልጣን ጋዛን ያስተዳድራል።

"አሁን ጠረጴዛው ላይ ያለው የዩናይትድ ስቴትስ ልዑክ ስቲቭ ዊትኮፍ ዕቅዱን ማብራራት ነው" ብለዋል።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ዕቅድ ደጋፊዎች ቢኖሩትም እዚያ ካሉ ታዛቢዎች የሚሰሙ ማስጠንቀቂያዎችም አሉ።

የእስራኤል ሃሬትስ ጋዜጣ አምደኛው ጌዲዮን ሌቪ "ማንም የአረብም ሆነ የዓለም አቀፍ ኃይል ወታደሮቹን ሙሉ በሙሉ ወደ ወደመችው ጋዛ የመላክ አደጋን አይጋፈጥም" ብሏል።

"ሙሉ ደኅንነት እና የጤና አደጋ ነው እንዲሁም ትልቅ እና የማይጨበጥ ኃላፊነት ነው።"

ፍልስጤማዊ ታዳጊ በፈራረሰ ቤት ላይ ተቀምጦ

የፎቶው ባለመብት, Mohammed Saber / EPA

የምስሉ መግለጫ, በጋዛ ሰርጥ የሚገኙ አብዛኞቹ ቤቶች በእስራኤል ትቃት ወድመዋል

ውሉ የጠፋው አማራጭ ሃሳብ

የግብፅ የስትራቴጂክ ጥናት ማዕከል ዳይሬክተር ጄነራል ካሌድ ኦካሻ አሁን በጋዛ የአረብ ጦር መመሥረትን ይቃወማሉ።

ይልቁንስ አሁን ያለው ድርድር ያተኮረው የአሜሪካው ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ ጦርነቱን ለማስቆም ባቀረቡት ሀሳብ ላይ እና ሙሉ በሙሉ ታጋቾችን ማስለቀቅ ላይ ያተኮረ መሆኑን ለቢቢሲ ኒውስ አረብኛ ተናግሯል።

ኦካሻ አክለው እየተካሄዱ ያሉት ንግግሮች ያተኮሩት "እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ከተቆጣጠረቻቸው አካባቢዎች መውጣቷ" ላይ ነው።

"ሐማስን በተመለከተ ከጦርነቱ ማብቂያ በኋላ የግብፅም ሆነ የአረብ መንግሥታት ምንም ቦታ እንደሌለው አስታውቀዋል። ሐማስ ራሱ ከጦርነቱ በኋላ የእስራኤል ወታደሮች ለቀው ከወጡ የጋዛ ሰርጥ አስተዳደር ላይ እንደማይሳተፍ ገልጿል" ይላሉ።

ኦካሻ የድጋፍ ኃይሎችን ለማቋቋም ወይም ለማምጣት የቀረበው ሀሳብ ወደፊት ለውይይት ሊቀርብ እንደሚችል ጠቁመው፣ "በአሁኑ ጊዜ ግን ግብፅን ጨምሮ የትኛውም የአረብ አገር ከእስራኤል ቀጥሎ አማራጭ ወራሪ ኃይል መሆን አይፈልግም" ብለዋል።

የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, የአሜሪካው ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ

የዊትኮፍ ዕቅድ

የስቲቭ ዊትኮፍ ���ቅድ ለ60 ቀናት የሚቆይ የተኩስ አቁም ስምምነት እና በሐማስ የተያዙ ዘጠኝ ሰዎችን ከ18 ታጋቾች አስከሬን ጋር መልቀቅን ያካትታል።

እስራኤል ከኔትዛሪም ለቅቃ ለመውጣት በአንድ ሳምንት ውስጥ ሁለት ደረጃዎች ይኖራሉ።

በዚህ ወቅት ጦርነቱን ለማቆም ድርድር ይደረጋል። ስምምነት ላይ ካልተደረሰ እስራኤል ተጨማሪ ታጋቾችን ለማስለቀቅ ጦርነቱን መቀጠል ወይም ድርድሩን መቀጠል ትችላለች።

ከሦስት ሳምንታት በፊት በኳታር ሲካሄድ የነበረው ድርድር ተቋርጧል። ዊትኮፍ "ሐማስ እየተናበበ አይደለም ወይም በቅን ልቦና እየሠራ አይመስልም" ብለዋል።

ሐማስ ዊትኪፍ የሰጡትን አስተያየት ውድቅ በማድረግ ለቀረቡት ጥያቄዎች በሙሉ አዎንታዊ ምላሽ ሰጥቻለሁ ሲል ተናግሯል።

ኔታንያሁ ማክሰኞ ማምሻውን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ታጋቾቹን ለመመለስ ምንም ዓይነት ከፊል ስምምነት እንደማይቀበሉ ተናግረዋል።

"በእስራኤል በሚወሰን መግባቢያ መሠረት ሁሉንም ታጋቾች ለመመለስ ወደ አጠቃላይ ስምምነት እየሄድን ነው" በማለት የእስራኤል ወታደሮች በጋዛ ከተማ የሚቆዩበት ጊዜ እንዲቀንስ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።

በጋዛ ቀጥሎ ስለሚሆነው ክርክር እና ውይይት እየተደረገ እያለ በሰርጡ ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ ፍልስጤማውያን በአነስተኛ የምግብ አቅርቦት እና በወደሙ ከተሞች ለመኖር እየታገሉ ነው።

በሐማስ የሚመራው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ሁለት ዓመት ሊሞላው በተቃረበው የእስራኤል ጥቃት ቢያንስ 61 ሺህ ሰዎች ተገድለዋል።