የጋዛ ጦርነት የመካከለኛው ምሥራቅን እና የዓለምን የኃይል ሚዛን እንዴት ቀየረው?

ለሁለተ ዓመት በዘለቀው የእስራኤል እና ሐማስ ጦርነት አብዛኛው የጋዛ አካባቢ ወድሟል

የፎቶው ባለመብት, BASHAR TALEB/AFP via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ለሁለተ ዓመት በዘለቀው የእስራኤል እና ሐማስ ጦርነት አብዛኛው የጋዛ አካባቢ ወደ ፍርስራሽነት ተቀይሯል

ለሁለት ዓመት ያህል የዘለቀው የጋዛ ጦርነት ተጽዕኖ ከዚያች አነስተኛ ግዛት ያለፈ ነው።

ወደ ሊባኖስ፣ ሶሪያ፣ ኢራን እና የመን ድረስ የተሻገረው ግጭት የመካከለኛው ምሥራቅን ብቻ ሳይሆን የዓለምንም የፖለቲካ ሚዛን የቀየረ መሆኑን ፖለቲከኞች ይናገራሉ።

በፖለቲካ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት በዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ለንደን ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር ጁሊ ኖርማን "ከእዚህ የሁለት ዓመት ጦርነት በኋላ ቀጠናውም ሆነ ዓለም ምን ያህል እንደተቀየረ ልንዘነጋው የምንችለው አይሆንም" ብለዋል።

ሐማስ መስከረም 26/2016 ዓ.ም. በደቡባዊ እስራኤል ጥቃት ፈጽሞ 1200 ሰዎችን ከገደለ እና 251 አግቶ ከወሰደ በኋላ በመካከለኛው ምሥራቅ በሺህዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ላይ ሞት ያስከተለ ጦርነት ተካሂዷል።

በቻተም ሐውስ የመካከለኛው ምሥራቅ እና የሰሜን አፍሪካ ፕሮግራም ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ሳናም ቫኪል "የእስራኤል የፀጥታ መዋቅር የማይበገር ነው የሚለውን ግምት አፍርሶታል" ይላሉ።

'ተያያዥ ውጤት'

የጋዛን የአየር ክልል፣ የባሕር ዳርቻዎች እና ድንበሮች የምትቆጣጠረው እስራኤል በሁለት ዓመት ውስጥ ባካሄደችው መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ የተነሳ ከ68,000 በላይ ፍልስጤማውያን ተገድለዋል።

ዶ/ር ኖርማን በጋዛ የተፈጠረው የሥነ ልቦና ጉዳት እና ውድመት "ከሚገመተው በላይ ነው" እንዲሁም "ለትውልዶች የሚቀጥል ይሆናል" ሲሉ ተናግረዋል።

እንዲሁ በተመሳሳይ የሐማስ ጥቃቶች እና ታጋቾችን መያዝ "ማኅበረሰቡን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ለውጦታል" ሲሉ ያክላሉ።

ከሁለት ዓመት በፊት ሐማሰ በእስራኤል ላይ የፈጸመው ጥቃት በክልሉ ውስጥ "ተያያዥ ውጤት" እንዳስከተለ ይናገራሉ።

በሁለት ዓመቱ ጦርነት ወቅት በእስራኤል ውስጥ ታጋቾች እንዲለቀቁ የሚጠይቁ ሰልፎች በተደጋጋሚ ተካሄደዋል

የፎቶው ባለመብት, AHMAD GHARABLI/AFP via Getty Images)

የምስሉ መግለጫ, በሁለት ዓመቱ ጦርነት ወቅት በእስራኤል ውስጥ ታጋቾች እንዲለቀቁ የሚጠይቁ ሰልፎች በተደጋጋሚ ተካሄደዋል

እስራኤል በጋዛ ላይ የአየር ድብደባ ስትፈጽም፣ ከሐማስ ጋር ያበሩ የታጠቁ ኃይሎች በእስራኤል ላይ የራሳቸውን ጥቃት ፈጽመዋል። ከእነዚህም መካከል የሊባኖሱ ሔዝቦላህ እና የየመኑ ሁቲ ይጠቀሳሉ።

እነዚህ ቡድኖች ከሶሪያ እና ከሐማስ ጋር በመሆን ኢራን በጦር መሳሪያ እና በገንዘብ የምትደግፋቸው "የተቃውሞ ማዕከል" ተብሎ የሚጠራው ጥምረት አካል ሆነው ቆይተዋል።

በሦስት የሪፐብሊካን ፕሬዝዳንቶች ስር በውጭ ፖሊሲዎች ላይ ያገለገሉት አሜሪካዊው ፖለቲከኛ ኤሊዮት አብራምስ፣ እስራኤል "በዚህ የእሳት ቀለበት" ተከብባ ትኖር ነበር እናም እነዚህን ቡድኖች "ለመከላከል" ስትሞክር ቆይታለች ይላሉ።

ከመስከረም 26 በኋላ ግን እስራኤል "መከላከል አይሠራም ስትል ወሰነች" ብለዋል።

"እናም መጀመሪያ ላይ ሐማስ ላይ ጥቃት ከፈተች፣ ከዚያ ሔዝቦላህ፤ ከዚያ ኢራን እያለች ቀጠለች። ይህ በፀጥታ ሁኔታ ላይ በራሳቸው ትንተና ላይ የተደረገ እውነተኛ ለውጥ ነው" ሲሉም አክለዋል።

በእስራኤል እና በሐማስ፣ በሊባኖስ በእስራኤል እና ሔዝቦላህ ፣ በእስራኤል እና ኢራን እንዲሁም በየመን ከሁቲ ጋር ያደረጋቸውን ጦርነቶች የሚያሳይ ካርታ

እንደ አውሮፓውያኑ መስከረም 2024፣ እስራኤል በሊባኖስ በድብቅ በጠለፈቻቸው በሺዎች በሚቆጠሩ የመልዕከት ማስተላላፊ መሳሪያዎች (ፔጀሮች እና ዎኪ ቶኪዎች) ውስጥ ያጠመደቻቸውን ፈንጂዎች አፈነዳች፤ በዚህም አብዛኞቹ የሔዝቦላህ አባላት ጉዳት ደርሶባቸዋል።

በማስከተልም በሊባኖስ ላይ ከባድ የቦምብ ጥቃት መፈጸም የጀመረች ሲሆን፣ የእግረኛ ጦሯንም ወደ ደቡባዊ የአገሪቱ ክፍል አሰማርታለች።

የእስራኤል የአየር ድብደባ የሔዝቦላህ መሪ ሐሰን ናስራላህን ጨምሮ በርካታ የቡድኑ ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ገድሏል።

እንዲሁም ብዙ መሠረተ ልማቶችን አውድሞ የጦር መሳሪያ ክምችቱ እንዲሟጠጥ አድርጓል።

የሔዝቦላህን የሮኬት ጥቃቶችን ተከትሎ እስራኤል በሊባኖስ ላይ ከባድ እና ተከታታይ የአየር ጥቃት ፈጽማለች

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የሔዝቦላህን የሮኬት ጥቃቶችን ተከትሎ እስራኤል በሊባኖስ ላይ ከባድ እና ተከታታይ የአየር ጥቃት ፈጽማለች

ከሁለት ወራት በኋላ በጎረቤት ሶሪያ የሔዝቦላህ እና የኢራን አጋር በሆነው የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ባሻር አል አሳድ ላይ ጥቃት ፈጸመች። ያንንም ተከትሎ የአሳድ የ24 ዓመታት ሥልጣን በሁለት ሳምንታት ውስጥ እንዲያበቃ ማድረግ ችላለች።

ዶ/ር ኖርማን በአካባቢው የታዩ ለውጦች እንዲሁም በአገሪቱ ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ አማፂያን የደረሰባቸው ጫና ለአገዛዙ ውድቀት ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል ይላሉ።

ሔዝቦላህ እንዲሁም ኢራን በመዳከማቸው፣ የአሳድ መንግሥት "ከእንግዲህ ወዲህ እሱን ለመደገፍ በዙሪያው ያሉ አጋሮች አልነበሩትም" ሲሉ ያብራራሉ።

እስራኤል ዕድሉን ተጠቅማ ከሶሪያ ግዛት ወደፊት የሚደርስ ጥቃትን ለማስወገድ የአገሪቱን የአየር ኃይል እና ሌሎች ወታደራዊ ማዘዣዎችን በቦምብ ደብድባለች።

የሶሪያው አዲሱ ፕሬዝዳንት፣ አህመድ አል ሻራ፣ ቀደም ሲል ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት ያለው እስላማዊ ተዋጊ መሪ ቢሆኑም መንግሥታቸው እስራኤልን መውጋት እንደማይፈልግ እና ሶሪያን የውጭ አካላት እንዲጠቀሙባት እንደማይፈቅዱ ተናግረዋል።

የበሽር አል አሳድ መውረድ እንደተሰማ ሶሪያውያን በዋና ከተማቸው ደማስቆ አደባባይ ወጥተው ደስታቸውን ገልፀዋል

የፎቶው ባለመብት, Rami Alsayed/NurPhoto via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የባሻር አል አሳድ መውረድ እንደተሰማ ሶሪያውያን በዋና ከተማቸው ደማስቆ አደባባይ ወጥተው ደስታቸውን ገልፀዋል

በመካከለኛው ምሥራቅ በእስራኤል እና በኢራን መካከል የለየለት ጦርነት ይቀሰቀሳል የሚለው ስጋት ለብዙ አሥርተ ዓመታት የነበረ ነው።

እስከዚያው ድረስ ግን የሔዝቦላህ ሰፊ የጦር መሳሪያ ክምችት፣ የረዥም ርቀት ሚሳዔሎችን ጨምሮ፣ እስራኤል በኢራን የኒውክሌር ተቋማት ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት ለመከላከል አግዟል።

አብራምስ "እስራኤል እና ኢራን በውክልና እና በተዘዋዋሪ ጦርነት ለረዥም ዓመታት ሲፋለሙ ቆይተዋል፤ ነገር ግን አንዳቸውም ሌላኛቸውን በቀጥታ አላጠቁም" ብለዋል።

ውጥረቱ ወደ የአየር ድብደባ እና የሚሳዔል ልውውጥ ሲቀየር ግን ይህ ተለወጠ። እነዚህ የተከሰቱት በሚያዝያ ወር 2024፣ ጥቅምት 2024 እና በሰኔ 2025 እስራኤል በኢራን ውስጥ የኒውክሌር እና ወታደራዊ ተቋማትን ባጠቃችበት ጊዜ ሲሆን፣ ይህም ለ12 ቀን የቆየ ጦርነትን ቀስቅሷል።

አሜሪካ በ2025 ከእስራኤል ጎን ሆና ጥቃቱን በመቀላቀል ግዙፉን "ምሽግ ደርማሽ" ቦምብ በኢራን የኒውክሌር ተቋሟት ላይ ጥላለች።

ኢራን ወደ እስራኤል ሚሳዔል ማስወንጨፏን ተከትሎ የአየር መከላከያ ስርዓቷ የተወሰኑትን ማክሸፍ ቢችልም የተወሰኑት የሰው ሕይወት መጥፋትን እና ጉዳትን አድርሰዋል

የፎቶው ባለመብት, MENAHEM KAHANA/AFP via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ኢራን ወደ እስራኤል ሚሳዔል ማስወንጨፏን ተከትሎ የአየር መከላከያ ሥርዓቷ የተወሰኑትን ማክሸፍ ቢችልም የተወሰኑት የሰው ሕይወት ማጥፋትን እና ጉዳትን አድርሰዋል

ሰፊው አንድምታ

አብራምስ በእነዚህ ሁሉ ሁነቶች የተነሳ እስራኤልን በተዘዋዋሪ የሚያጠቁት የኢራን አጋሮች፣ ሐማስ እና ሔዝቦላህን ጨምሮ "እንዲወገዱ ተደርገዋል"፤ "በጣም ደካማ ሆነዋል" ብለዋል።

ዶ/ር ኖርማን ደግሞ እነዚህን ቡድኖች ለማዳከም እርምጃ የተወሰደበት ፍጥነት ለክልሉ ተዋናዮች "በጣም አስገራሚ ነበር" ብለዋል።

ሰፋ ያሉ አንድምታዎችም ነበሩት። ሌላኛዋ የኢራን አጋር የሆነችው ሩሲያ በፕሬዝዳንት አሳድ መውደቅ ምክንያት በቀጠናው ውስጥ ቁልፍ የሆነ አጋር እና ቦታ አጥታለች።

በሶሪያ ደም አፋሳሽ የእርስ በርስ ጦርነት ወቅት የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና ፕሬዝዳንት አል ሻራ በተቃራኒ ጎራ በኩል ነበሩ። ሩሲያ የሶሪያን የቀድሞ ፕሬዝዳንት አሳድን ለመደገፍ ከባድ ወታደራዊ ኃይል ትጠቀም ነበር።

ሩሲያ በሶሪያ ውስጥ ሁለት ትላልቅ የጦር ሰፈሮች ያሏት ሲሆን፣ እነዚህም በሩሲያ ጦር እና በአፍሪካ ውስጥ በምታሰማራቸው ቅጥረኛ ወታደሮቿ ውስጥ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል።

በመጀመሪያ ፕሬዝዳንት አል ሻራ ሩሲያ ወታደሮችን በግዛታቸው ውስጥ እንድታሰፍር ይፈቅዱ እንደሆነ ግልፅ አልነበረም።

እስራኤል በኢራን ውስጥ የኒውክሌር እና ወታደራዊ ተቋማት ናቸው ያለቻቸውን ስትደበድብ ሰላማዊ ዜጎች ተገድለዋል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, እስራኤል በኢራን ውስጥ የኒውክሌር እና ወታደራዊ ተቋማት ናቸው ያለቻቸውን ስትደበድብ ሰላማዊ ዜጎች ተገድለዋል

በጥቅምት 2025 ሻራ በሞስኮ ከፑቲን ጋር ባደረጉት ውይይት የሩሲያን ድጋፍ እና ኢንቨስትመንት በመፈለጋቸው የተነሳ "ሁሉንም ስምምነቶች እንደሚያከብሩ" ተናግረዋል። ግንኙነቱ ግን የሚፈለገውን ያህል ጠንካራ አልነበረም።

ቻይናም በመካከለኛው ምሥራቅ ያላትን ተፅዕኖ እየቀነሰ መምጣቱን ተንታኞች ይገልጻሉ። ከጦርነቱ በፊት ግን በአካባቢው የሰላም እና የንግድ አጋር ሆና ብቅ እያለች ነበር ይላሉ ዶ/ር ኖርማን።

በዚህም የተነሳ በኢራን እና በሳዑዲ አረቢያ መካከል የነበረው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን ወደ ቀድሞው ሁኔታ ለመመለስ ስምምነት እንዲደረስ አድርጋለች።

ነገር ግን የጋዛ ጦርነት የአሜሪካን ትኩረት ወደ መካከለኛው ምሥራቅ እንዲመለስ በማድረጉ ቻይና "ወደ ኋላ ማፈግፈግን መርጣለች" ይላሉ።

ቱርክ ግን ከአዲሱ የሶሪያ መንግሥት ጋር ጥብቅ ወዳጅነት እየገነባች ነው። ለአስርት ዓመታት ደማስቆ በኢራን እና በሩሲያ ተጽእኖ ስር ነበረች የሚሉት ዶ/ር ኖርማን፣ አሁን ግን ለቱርክ "ከፍ ያለ ሚና" ሊኖር ይችላል ብለዋል።

"የለውጥ ጊዜ"

ቱርክ ከግብፅ እና ከኳታር ጎን በመሆን በጋዛ የተኩስ አቁም እንዲደረስ ትልቅ ሚና ተጫውታለች።

ቱርክ ለሐማስ አመራሮች እንዲሁም ለአሜሪካ በመካከለኛው ምሥራቅ ግዙፉን የጦር ሠፈር በማስተናገድ ቁልፍ አሸማጋይ ሆና ብቅ ብላለች።

በመስከረም ወር 2025 እስራኤል በኳታር ዋና ከተማ ዶሃ ውስጥ በሐማስ መሪዎች ላይ የአየር ጥቃት ፈፅማለች። ይህ የእስራኤል እርምጃ ኳታርን ያስቆጣ እና የጋዛ የተኩስ አቁም ድርድርን ያስተጓጉላል የሚል ስጋት ፈጥሮ ነበር።

ሆኖም አብራምስ እንደሚሉት ጥቃቱ የዩናይትድ ስቴትስ አጋር የሆነችውን አገር ሉዓላዊነት በመጣስ "ጦርነቱ ወደ ፍጻሜው እንዲቃረብ የለውጥ ጊዜ" በመሆን አገልግሏል ብለው ያምናሉ።

ቱርክ፣ ግብፅ እና ኳታር በጋዛ የተኩስ አቁም ሲደረስ ቁልፍ ሚና ተጫውተዋል

የፎቶው ባለመብት, Evan Vucci - Pool / Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ቱርክ፣ ግብፅ እና ኳታር በጋዛ የተኩስ አቁም ሲደረስ ቁልፍ ሚና ተጫውተዋል

ኳታር በኋላ ከፕሬዝዳንት ትራምፕ ያገኘችውን የደኅንነት ማረጋገጫ መፈለጓን ያምናሉ።

አብራምስ "ውጤቱም ይህንን ጦርነት እንዲያበቃ ማድረግ አለብን…ስለዚህ ሐማስን ትሰጡናላችሁ ነው" ይላሉ።

በተመሳሳይ ጊዜ ትራምፕ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጦርነቱን እንዲያቆሙ ግፊት በማድረግ ኳታርን ለጥቃቱ ይቅርታ እንዲጠይቁ አስገድደዋል።

ዶ/ር ኖርማን ኳታር፣ ግብፅ እና ቱርክ ሐማስ ��መደራደር ፈቃደኛ እንዲሆን እና የትራምፕን ሀሳብ እንዲቀበል ለማድረግ ትልቅ ሚና ነበራቸው።

ፈረንሣይ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ካናዳ እና አውስትራሊያን ጨምሮ በርካታ ዋና ዋና ምዕራባውያን አገራት ለፍልስጤም ግዛት እውቅና ለመስጠት ባደረጉት ውሳኔ ይህ ግፊት የበረታ እንደነበር ያምናሉ።

ምንም እንኳን አንዳንድ ታዛቢዎች ይህን እርምጃ ተምሳሌታዊ ብቻ አድርገው ቢወስዱትም፣ በቀጣናው ያሉ ሌሎች አገራት ሐማስ የተኩስ አቁም እንዲያደርግ "ቀላል አድርጎታል" ብለዋል።

እስራኤል 'ተገለለች'

በጥቅምት ወር የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት የመጣው በብዙ አገራት ውስጥ በእስራኤል ወታደራዊ ዘመቻ እና በጋዛ ስላለው ሰብዓዊ ሁኔታ እየጨመረ የመጣውን የሕዝብ ቁጣን ተከትሎ ነው።

በነሐሴ ወር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሚደገፈው አካል በጋዛ ከተማ እና አካባቢው ረሃብ አለ ሲል ደምድሟል።

እስራኤል ይህንን "ፍፁም ውሸት" በማለት አስተባብላለች።

በቀጣዩ ወር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አጣሪ ኮሚሽን እስራኤል በጋዛ ፍልስጤማውያን ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽማለች ሲል እስራኤል ይህንንም "የተዛባ እና ውሸት" በማለት አጣጥለለች።

በጋዛ ባለው የሰብዓዊ ቀውስ ተነሳ በበርካታ አገራት ቁጣ ተቀስቅሷል

የፎቶው ባለመብት, BASHAR TALEB/AFP via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በጋዛ ባለው የሰብዓዊ ቀውስ ተነሳ በበርካታ አገራት ቁጣ ተቀስቅሷል

ዶ/ር ቫኪል "በመላው አውሮፓ ያሉ ሕዝቦች የእስራኤልን ወታደራዊ እንቅስቃሴ በጥንቃቄ ከመመልከት፣ ከደጋፊነት፣ የእስራኤል እንቅስቃሴ በጋዛ ውስጥ የዘር ማጥፋት ወንጀል እየፈጸመ ነው ብለው ባይጠሩትም ወደ ተቃዋሚነት ተለውጠዋል። ይህም ወደ አሜሪካም ተዛምቷል" ብለዋል።

በአጠቃላይ ዶ/ር ቫኪል "እስራኤል ዛሬ በአካባቢው ወታደራዊ የበላይነት የያዘች አገር ትመስላለች" ብለዋል።

ነገር ግን "የወታደራዊ አካሄዱ ውጤት… እስራኤል በዓለም አቀፍ እና በክልላዊ ሁኔታ ያጋጠማት ሽንፈት ነው፤ እስራኤል ከብዙ አሥርተ ዓመታት በኋላ የበለጠ የተገለለችበት ወቅት አሁን ነው" ሲሉ ሃሳባቸውን ያጠናክራሉ።

ከአውሮፓውያኑ 1967 ጀምሮ ፍልስጤም፣ ጋዛን እና በእስራኤል በወረራ የተያዘው ዌስት ባንክን ጨምሮ፣ በተባበሩት መንግሥታት እውቅና አግኝታለች።

በጥቅምት ወር የተደረሰውን የጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት ተከትሎ ሦስቱ ባለሙያዎች እንደሚናገሩት ሐማስን ትጥቅ ከማስፈታት ጀምሮ፣ ለጋዛ የገንዘብ እና የፀጥታ ኃይል ማቅረብ እንዲሁም እስከ የፍልስጤም አገርነት ድረስ ብዙ እርግጠኛ ያልሆኑ ነገሮች አሉ።

ነገር ግን እንደዚያም ሆኖ፣ ቀጠናው "ሙሉ በሙሉ ተቀይሯል" ሲሉ ዶ/ር ኖርማን አንዳንድ ግንኙነቶችን "ሙሉ ለሙሉ አዲስ መልክ" ይዘዋል ብለዋል።

እና በአጠቃላይ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ ላይ አዲስ ትኩረት አለ ሲሉ ተናግረዋል።

በዚህም የተነሳ "እስከ አሁን ካየነው ጦርነት እና ግጭት ይልቅ በክልሉ ውስጥ ለተሻለ ነገር አዲስ ቁርጠኝነትን ያመጣል" የሚል ተስፋ አለ ይላሉ።