ግመሎችን እና ወርቅ በመሸጥ ሃብት ያካበቱት፣ አሁን ደግሞ ከፊል ሱዳንን የሚቆጣጠሩት ሐምዳን ዳጎሎ

የፎቶው ባለመብት, Anadolu via Getty Images
ሞሐመድ ሐምዳን ዳጎሎ ወይም "ሄሜቲ" ከሚመሩት የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ጋር በመሆን በአገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሆኑ እና አሁን የአገሪቱን ግማሽ የሚቆጣጠሩ ግለሰብ ናቸው።
የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ የአገሪቱ ጦር እና አጋሮቹ በምዕራብ ዳርፉር የምትገኘውን የጦሩ መቀመጫ የኤል ፋሸር ከተማን በእጁ ሲያስገባ አስደናቂ ድል አግኝቷል።
ሄሜቲ በተቀናቃኞቻቸው የሚፈሩት እና የሚጠሉትን ያህል፤ ባላቸው ፅናት፣ ርህራሄ አልባነት፣ እንዲሁም መንግሥትን ለመጣል በገቡት ቃል በተከታዮቻቸው ይደነቃሉ።
ሄሜቲ አጀማመራቸው እንደማንኛውም ተራ ግለሰብ ነው። የተገኙት በማሃሪያ አካባቢ አረብኛ ከሚናገሩ ሪዜይጋት ማኅበረሰብ ሲሆን፣ ወደ ቻድ እና ዳርፉር እየተመላለሱ ግመል በማርባት ልጅነታቸውን አሳልፈዋል።
እንደማንኛውም በገጠር እንደሚኖር ሰው የተወለዱበትን ጊዜ የሚያሳይ ምዝገባ ባለመኖሩ በትክክል የተወለዱበትን ጊዜ ለማወቅ ቢያስቸግርም እአአ በ1974 ወይም 1975 መወለዳቸው ይገመታል።
በአጎታቸው ጁማ ዳጎሎ የሚመራው ጎሳቸው በ1970ዎቹ እና 80ዎቹ ጦርነትን ሸሽቶ ለከብቶቹ ግጦሽ ወደ ዳርፉር በመምጣት ሰፈረ።
በአሥራዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ ትምህርታቸውን ካቋረጡ በኋላ፣ ሄሜቲ ግመሎችን ወደ ሊቢያ እና ግብፅ በመውሰድ እና በመሸጥ ገንዘብ ማግኘት ጀመሩ።
ያኔ ዳርፉር በሱዳን ሕግ አልባ አካባቢ፣ ነዋሪዎቹ በከፋ ድህነት ውስጥ የሚማቅቁበት እና በወቅቱ ፕሬዝዳንት በነበሩት ኦማር አልበሽር መንግሥት ችላ የተባለ አካባቢ ነበር።
ጃንጃዊድ በመባል የሚታወቁት የአረብ ታጣቂዎች፣ በጁማ ዳጎሎ የሚመራውን ኃይል ጨምሮ፣ የፉር ብሔረሰብ ተወላጆች መንደሮችን ያጠቁ ነበር።
ይህ ተከታታይ ጥቃት እአአ በ2003 ወደ ለየለት ግጭት አደገ።
በዚህ ወቅት የፉር ተዋጊዎች ከማሳሊት፣ ዛግሃዋ እና ሌሎች ቡድኖች ጋር ተጣምረው በአገሪቱ የአረብ ልሂቃን ችላ ተብለናል ሲሉ አመፁ።
በምላሹም አል በሽር የፀረ-ሽምቅ ጥረቱን ለመምራት በሚል ጃንጃዊድን አስፋፉ።
በመቀጠልም ይህ ቡድን የመኖሪያ መንደሮችን በማቃጠል፣ በመዝረፋ፣ በመድፈር እና በመግደል ታዋቂነትን አገኘ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሄሜቲ የሚመሩት ጦር ከእነዚህ መካከል አንዱ ሲሆን፣ እአአ በኅዳር 2004 የአድዋ መንደር ላይ ጥቃት በማድረስ 36 ሕጻናትን ጨምሮ 126 ሰዎች መሞታቸውን የአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል ከሶታል።
የአሜሪካ መንግሥት ባደረገው ምርመራ ደግሞ ጃንጃዊድ የዘር ማጥፋት ወንጀል በመፈፀም ተጠያቂ መሆኑን አረጋግጧል።
የዳርፉር ግጭት ወደ ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት (ICC) የተላለፈ ሲሆን፣ ምንም እንኳን አልፈጸምንም ብለው ቢያስተባብሉም አል በሽርን ጨምሮ በአራት ሰዎች ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ክስ ተመሥርቷል።
ሄሜቲ በወቅቱ በዐቃቤ ሕጉ ዕይታ ውስጥ ከነበሩት በርካታ የጃንጃዊድ አዛዦች ሁሉ በዕድሜ በጣም ትንሽ ናቸው ተብለው ታልፈዋል።
ከጃንጃዊድ አዛዦች መካከል "የኮሎኔል ኮሌኔል" በመባል የሚጠሩት አሊ አብደል ራህማን ኩሻይብ ብቻ ክስ ተመሥርቶባቸው ችሎት ፊት ቀርበዋል።
ባለፈው ወር በ27 የጦር እና በሰብዓዊነት ላይ በተፈፀሙ ወንጀሎች ጥፋተኛ ሆነው የተገኙ ሲሆን እአአ ኅዳር 19/2025 ውሳኔ ይሰጥባቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።
እአአ በ2004 በዳርፉር የሚካሄደው ግጭት እየተባባሰ በመጣበት ወቅት ሄሜቲ ያላቸውን ዕድል ስልታዊ በሆነ መልኩ ተጠቅመዋል።
በዚህም በጣም የሚፈራ የፈጥኖ ደራሽ ኃይል መሪ፣ የበርካታ ንግዶች ባለቤት እና የሱዳንን ፖለቲካ መዘወር የሚያስቸል አቅም አግኝተዋል።
ለአጭር ጊዜም ለወታደሮቻቸው ያልተከፈላቸው ደመወዝ እንዲከፈል፣ ዕድገት እንዲሰጣቸው እንዲሁም ለወንድማቸው የፖለቲካ ሥልጣን በመጠየቅ አል በሽር ላይ አመፁ።
አል በሽር አብዛኛውን የጠየቁትን ሁሉ በመስጠት ሄሜቲ ከጎናቸው እንደተሰለፉ እንዲቆዩ ማድረግ ቻሉ።
በኋላ ሌሎች የጃንጃዊድ ክፍሎች ሲያምፁ ሄሜቲ የመንግሥትን ጦር በመምራት ድል አደረጓቸው።
በዚህ ሂደት ውስጥ ጀበል አሚር በተባለ ቦታ የሚገኝ የዳርፉርን ትልቁን ባህላዊ ወርቅ ማምረቻ ተቆጣጠሩ።
በፍጥነት የሄሜድቲ ቤተሰብ ኩባንያ አል-ጉናይድ፣ የሱዳን ትልቁ ወርቅ ላኪ መሆን ቻለ።
እንደ አውሮፓውያኑ በ2013፣ ሄሜድቲ አዲስ የተቋቋመው ፈጥኖ ደራሽ ኃይል አዛዥ እንዲሆኑ ጠይቀው ተሾሙ።
በዚህ ሥልጣናቸውም የተነሳ ቀጥታ ተጠሪነታቸው ለወቅቱ ፕሬዚዳንት አል በሽር ሆነ።
ጃንጃዊድ ወደ አርኤስኤፍ ተጠቃልሎ አዳዲስ የደንብ ልብሶችን፣ ተሸከርካሪዎችን እና የጦር መሳሪያዎችን እንዲሁም የማሻሻያ ሥራውን እንዲያግዙ ከመደበኛው ሠራዊት የመጡ መኮንኖች ተቀላቀሏቸው።

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
አርኤስኤፍ በዳርፉር አማፂያን ላይ ወሳኝ ድል አስመዝግቧል። ከደቡብ ሱዳን ጋር በሚያዋስን አካባቢ ባሉት የኑባ ተራሮች አማፂያንን በመዋጋት ረገድ ግን እምብዛም ጥረት አላደረገም።
ከሊቢያ ጋር ያለውን ድንበር ለመጠበቅ ደግሞ ኃላፊነትን ወስዷል።
ከአፍሪካ ወደ ሜዲትራኒያን ባሕር የሚደረገውን ሕገወጥ የሰዎች ፍልሰትን ለመግታት እየሠሩ መሆኑን የሚናገሩት የሄሜቲ አዛዦች በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ በስፋት ተሳትፈዋል።
እአአ በ2015 ሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ (ዩኤኢ) የሱዳን ጦር በየመን ሁቲዎ���ን ለመዋጋት ወታደሮቻቹን እንዲልክ ጠየቁ።
ወደ የመን የተሰማራው ጦር የተመራው በዳርፉር ሲዋጉ የነበሩት ጄነራል አብዱል ፈታህ አል ቡርሐን ናቸው።
ጄነራሉ አሁን የሱዳን ጦር አዛዥ ሲሆኑ ከፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ጋር ጦርነት ከገጠሙ ዓመታት ተቆጥረዋል።
ሄሜቲ ዕድሉን በመመልከት ከሳዑዲ አረቢያ እና ከተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ ጋር የአርኤስኤፍ ቅጥረኛ ወታደሮቸን ለማቅረብ በግል ተደራደሩ።
በዚህ የአቡ ዳቢ ግንኙነታቸው ከኤሜሬቱ መሪ ሞሐመድ ቢን ዛይድ ጋር የጠበቀ ግንኙነት መፍጠር ቻሉ።
ወጣት ሱዳናውያን፣ ከጎረቤት አገራት ጭምር እየመጡ እስከ 6,000 ዶላር የሚደርስ ገንዘብ ይከፈልበታል ወደተባለው ውትድርና ለመቀላቀል ወደ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ የምልመላ ማዕከላት መጉረፍ ጀመሩ።
ሄሜቲ ከሩሲያው ቫግነር ግሩፕ ጋር ሽርክና በመፍጠር ወርቅን ጨምሮ በተለያዩ ንግዶች ላይ ለመሰማራት ስምምነትን ያደረጉ ሲሆን፣ በምላሹ ወታደራዊ ሥልጠና ለማግኘት ተዋውለዋል።
ስምምነቱን ለመፈረም ሞስኮ የሄዱት ሄሜቲ፣ እርሳቸው እዚያ እያሉ ሩሲያ ዩክሬንን ወርራለች።
በሱዳን ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ፣ አርኤስኤፍ ከቫግነር እርዳታ እያገኘ አለመሆኑን በመግለጽ አስተባብለዋል።
የአርኤስኤፍ ዋና ተዋጊ ኃይሎች ከጊዜ ወደ ጊዜ በውጊያ የተካኑ ቢሆኑም፣ መደበኛ ያልሆኑ ታጣቂዎችን እና የጎሳ ሚሊሻዎችን ያሳትፋሉ።
አገዛዙ ከፍተኛ ሕዝባዊ ተቃውሞ ሲገጥመው፣ አል በሽር የሄሜቲን ጦር ወደ ዋና ከተማዋ ካርቱም እንዲመጡ አዘዙ።
ሂማይቲ (ጠባቂዬ) በማለት አቆላምጠው በመጥራትም በመደበኛው ጦር እና የደኅንነት ኃይሎች ሊሰነዘርባቸው የሚችለውን የመፈንቅለ መንግሥት ለመከላከል እንደሚረዳቸው ለማሳየት ጣሩ።
ይህ ግን የተሳሳተ ስሌት ነበር። እአአ በሚያዝያ 2019 ዲሞክራሲን የሚጠይቁ ሱዳናውያን ተቃዋሚዎች የአገሪቱን መከላከያ ዋና መሥሪያ ቤትን ከበቡ።
አል በሽር ሠራዊቱ ተቃዋሚዎች ላይ እንዲተኩሱ አዘዙ። ከፍተኛ ጄነራሎች፣ ሄሜቲን ጨምሮ ተነጋግረው ፕሬዝዳንቱን ከሥልጣን ለማውረድ ወሰኑ።

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
ለተወሰነ ጊዜ ሄሜቲ የሱዳን የወደፊት ዕጣ ፈንታ መሪ በመሆን ተሞካሹ።
ወጣት፣ ሰብዕናቸው ለብዙኃን የቀረበ፣ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር በስፋት የሚገናኙ እና ራሳቸውን አገሪቱ የተመሠረተችበትን ታሪካዊ ዳራ የሚያስተካክሉ አድርገው በማስቀመጥ የፖለቲካ ሰብዕናቸውን ለመሳል ሞከሩ።
ይህ ግን ለጥቂት ሳምንታት ብቻ ነበር የቆየ።
ከገዢው ወታደራዊ ምክር ቤት ጥምር መሪው አል ቡርሐን ጋር የያዙትን ሥልጣናቸውን ለሰላማዊ ዜጎች ለማስረከብ ሲያመነቱ፣ ተቃዋሚዎቹ አደባባይ በመውጣት ድምጻቸውን ማሰማት ቀጠሉ።
ሄሜቲ አርኤስኤፍን በማሰማራት በሂውመን ራይትስ ዋች ሪፖርት መሠረት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን እንዲገደሉ፣ ሴቶችን እንዲደፈሩ እና ወንዶች ተገድለው እግራቸው ላይ ድንጋይ እ��ታሰረ ናይል ወንዝ ውስጥ እንዲጣሉ አድርገዋል።
ሄሜቲ ግን ይህንን የሰብዓዊ መብት ድርጅት ሪፖርት አስተባብለዋል።
በሱዳን ሰላም እና ዲሞክራሲን ለማስፈን በጋራ በተሰየሙት በአሜሪካ፣ በዩናይትድ ኪንግደም፣ በሳዑዲ አረቢያ እና በተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ አደራዳሪነት ጄነራሎቹ እና ሲቪሎች በአፍሪካ ሸምጋዮች የተረቀቀውን ስምምነት ለመቀበል ተስማሙ።
ለሁለት ዓመታት በወታደራዊ አመራሮች የበላይነት የሚመራው ሉዓላዊ ምክር ቤት እና ከሲቪሎች ጋር በመሆን የተዋቀረው ካቢኔ አስቸጋሪ ጊዜ አሳልፈዋል።
በካቢኔ የተሰየመው ኮሚቴ በሠራዊቱ፣ በደኅንነት ተቋሙ እና በአርኤስኤፍ ባለቤትነት የተያዙ ኩባንያዎችን ላይ ምርመራ አድርጎ የመጨረሻ ሪፖርቱን እንዳያቀርብ ተደርጓል።
ይህ ሪፖርት የሄሜቲ የንግድ ድርጅቶች እንዴት በፍጥነት እያሰፉ እንደሚሄዱ ያጋልጣሉ ተብሎ ተጠብቆ የነበረ ቢሆንም ቡርሐን እና ሄሜቲ የሲቪል አስተዳደሩን በማባረር ሥልጣን ተቆጣጥረዋል።
ነገር ግን መፈንቅለ መንግሥት ለማድረግ በጥምረት የሠሩት እነዚህ ወታደራዊ አዛዦች ብዙም ሳይቆዩ ወደ ግጭት ገብተዋል።
አል ቡርሃን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በሠራዊት ሥር እንዲሆን ጠየቁ።
ሄሜቲ ደግሞ ይህንን ተቃወሙ። ይህንን አለመግባባት ለመፍታት ሚያዚያ 2023 የመጨረሻ ቀነ-ገደብ የተቀመጠ ቢሆንም፣ የአርኤስኤፍ ጦር ግን ከዚያ ቀድሞ የሠራዊቱን ዋና መሥሪያ ቤት ለመክበብ እና በዋና ከተማዋ ካርቱም የሚገኘውን ብሔራዊ ቤተ መንግሥት በቁጥጥሩ ሥር ለማዋል ተንቀሳቅሷል።
ጥረቱ አልተሳካም። ይልቁንም ካርቱም የጦርነት አውድማ ሆና ተቀናቃኝ ኃይሎች በየመንገዱ ሲዋጉ ነበር።
በዳርፉር ዳግም ጦርነት አገረሸ፤ የአርኤስኤፍ ጦር በማሳሊት ማኅበረሰብ ላይ አስከፊ ዘመቻ ከፈቱ።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በእርስ በርስ ጦርነቱ እስከ 15,000 የሚደርሱ ሰላማዊ ሰዎች መሞታቸውን ይገምታል። አሜሪካ ደግሞ ድርጊቱን የዘር ማጥፋት ወንጀል ስትል ጠርታዋለች።
አሁንም የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ የሚቀርቡበትን ክስ ውድቅ አድርጓል።
የአርኤስኤፍ አዛዦች ተዋጊዎቻቸው ሰላማዊ ሰዎችን ሲያሰቃዩ እና ሲገድሉ፣ ጭካኔያቸውን እና ጥፋተኛነታቸውን የሚያሳዩ ቪዲዮዎች ሲያጋሩ ነበር።
አርኤስኤፍ እና አጋሮቹ ሚሊሻዎች የሱዳንን ከተሞችን፣ ገበያዎችን፣ ዩኒቨርሲቲዎችን እና ሆስፒታሎችን ዘርፈዋል።
እነዚህ የተዘረፉ ቁሳቁሶች ከሱዳን አልፎ ወደ ቻድና ወደ ሌሎች ጎረቤት አገራት እየተሻገረ በተለምዶ "የዳጎሎ ገበያ" እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ለሽያጭ ቀርቧል።
አርኤስኤፍ ተዋጊዎቹ በዘረፋ ላይ እጃቸው የለበትም ሲል አስተባብሏል።
ሄሜቲ በጦርነቱ መጀመሪያ ሳምንታት አካባቢ ብሔራዊ ቤተመንግሥቱ ላይ በደረሰ የመድፍ እና የአየር ድብደባ ክፉኛ ተጎድተው ከሕዝብ ዕይታ ጠፍተው ነበር።
ከወራት በኋላ እንደገና ብቅ ሲሉ ግን ለጭካኔያቸው ምንም ዓይነት ፀፀት ሳያሳዩ ጦርነቱን ለማሸነፍ ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልፀዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
አርኤስኤፍ በቡርሃን ቁጥጥር ሥር የምትገኘዋን እና እንደ ዋና ከተማ እያገለገለች የምትገኘውን ፖርት ሱዳንን ለመደብደብ የተጠቀመባቸውን ዘመናዊ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ጨምሮ ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችን አግኝቷል።
ይህም በኤል-ፋሸር ላይ በደረሰው ጥቃት ወሳኝ ሚና ተጫውቷል።
በኒው ዮርክ ታይምስ የምርመራ ዘገባዎች ላይ እንደተጠቀሰው እነዚህ መሣሪያዎች በቻድ ውስጥ በተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ በተገነባው የአየር ማረፊያ በኩል ተጓጉዘው እንዲገቡ ተደርገዋል።
የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ አርኤስኤፍን እያስታጠቅኩ አይደለም ስትል አስተባብላለች።
እነዚህን ዘመናዊ መሣሪያዎች በመጠቀም አርኤስኤፍ ከቀድሞ አጋሩ ከሱዳን ጦር ጋር የሚያደርገውን ጦርነት ቀጥሎበታል።
ሄሜቲ አንዳንድ የሲቪል ቡድኖችን እና የታጠቁ ኃይሎችን በተለይም በኑባ ተራሮች ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የቀድሞ ተቃዋሚዎቹን በማካተት የፖለቲካ ጥምረት ለመፍጠር እየሞከሩ ነው።
የሊቀመንበርነቱን ቦታ በመያዝ ትይዩ የሆነ "የሰላም እና የአንድነት መንግሥት" መሥርተዋል።
ኤል ፋሸርን በቁጥጥር ስር በማዋል፣ አርኤስኤፍ አሁን ከናይል በስተ ምዕራብ የሚገኘውን ሁሉንም ሰዎች የሚኖሩባቸውን አካባቢዎች በቁጥጥሩ ስር አውሏል።
በኤል ፋሸር የጅምላ ግድያ ተፈጽመዋል የሚሉ ሪፖርቶች መውጣታቸውን እና ውግዘቶች እየጨመሩ መምጣታቸውን ተከትሎ ሄሜድቲ ኤል ፋሸር በተያዘችበት ወቅት ወታደሮቹ የፈፀሟቸውን ጥሰቶች እንዲመረመር አዝዘዋል።
ሱዳናውያን ግምታቸው ሄሜቲ ራሳቸውን ወይ እንደ ተገንጣይ ግዛት ፕሬዝዳንት አድርገው ይመለከታል ወይም አሁንም ሱዳንን በሙሉ የመግዛት ፍላጎት አላቸው ብለው ይገምታሉ።
ራሳቸውን ከፍተኛ ገንዘብ የሚያንቀሳቅስ ንግዶች እንዳሉት፣ ቅጥረኛ ጦር እንደሚመራ እና የፖለቲካ ፓርቲ ያለው ከጀርባ ሆኖ የሱዳን ፖለቲካ አድራጊ ፈጣሪ አድርገውም ሊቆጥሩ ይችላሉ። በዚህም መሠረት የሱዳን ሕዝብ ባይቀበላቸውም ከጀርባ በመሆን ግን ፖለቲካውን መዘወር ያስችላቸዋል።
እናም የሄሜቲ ወታደሮች በአል-ፋሸር ሰላማዊ ዜጎችን ሲጨፈጭፉ፣ ብዙም ደንታ በሌለው ዓለም ውስጥ ጥፋተኛ ሳይባሉ እንደሚኖሩ እርግጠኛ ናቸው።















