ኦፌኮ በቀጣዩ ምርጫ ከመንግሥት እና ከታጣቂዎች የሚደርስ ጫና ላይ ፍራቻ እንዳለው ገለፀ

ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና

ኦፌኮ ኦሮሚያ ክልል ያለው የፀጥታ ሁኔታ እና የፖለቲካ ምህዳሩ መጥበብ ለምርጫ የሚጋብዝ ስላልሆነ "በአዲስ አበባ ብቻ ለመወዳደር መወሰኑን" የፓርቲው ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ለቢቢሲ ተናገሩ።

ፕሮፌሰሩ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ የፖለቲካ ምህዳሩ መጥበብ እና አስተማማኘ ፀጥታ አለመኖር ብቻ ሳይሆን "በኦሮሚያ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች"ም እንዲወዳደሩ እንደማይፈልጉ ገልፀዋል።

የኦፌኮ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀ መንበር ፕ/ር መረራ በምርጫ ቦርድ ሕግ መሠረት በተከታታይ ሁለት ምርጫዎችን ያልተሳተፈ ፓርቲ እንደሚሰረዝ ጠቅሰው በዚህም ምክንያት በአዲስ አባባ ብቻ ለመወዳደር መወሰናቸውን ተናግረዋል።

ከአስር ያላነሱ ፓርቲዎች በጋራ በመሆን በተደጋጋሚ የምርጫ አስቻይ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩ መንግሥትንም ምርጫ ቦርድንም መጠየቃቸውን ያስታወሱት ፕሮፌሰር መረራ "ብዙ የተሻሻለ ነገር የለም" ብለዋል።

"ተወዳዳሪ ካላመጣችሁ ስላሉን" ቅዳሜ ኅዳር 20/2018 ዓ.ም. አስቸኳይ የማዕከላዊ ስብሰባ አካሂደን በኦሮሚያ አካባቢ ያሉትን ሁኔታዎች ከገመገምን በኋላ በሙሉ ድምጽ "ኦሮሚያ ላይ ለምርጫ የሚሆን አስቻይ ሁኔታ የለም" የሚል ውሳኔ ማሳለፋቸውን ተናግረዋል።

ኦፌኮ ማክሰኞ ኅዳር 23/2018 ባወጣው መግለጫ ላይ በመጪው አጠቃላይ ምርጫ 'ምሳሌያዊና ስልታዊ ተሳትፎ' የተሰኘ ስትራቴጂን በመከተል በአዲስ አበባ የምርጫ ክልሎች ላይ እና የደህንነቱ ሁኔታ በምርጫ ለመሳተፍ አስቻይ መሆኑን የሥራ አስፈፃሚዉ ገምግሞ በሚያፀድቃቸዉ የምርጫ ክልሎች ብቻ ዕጩዎቹን እንደሚያቀርብ ገልጿል።

ፕሮፌሰር መረራ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ለነጻ እና ፍትሃዊ ምርጫ መጀመርያ የሚጠይቀው አስቻይ የፖለቲካ ምህዳር አለ ወይ የሚለውን ነው በማለት ፓርቲያቸው እንደሌለ እንደሚያምን ተናግረዋል።

ምርጫ ቦርድ ገለልተኛ አይደለም ሲሉ የተናገሩት ፕሮፌሰር መረራ፣ በተቃዋሚዎች ስምምነት እና በጋራ የተቋቋመ ተቋም አይደለም ብለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አሁን ባለው የምጫ ስርዓት ቦርዱን ከላይ ጀምሮ እስከ ታች ድረስ "በአንድ ፓርቲ የሚታዘዙ እና አንድ ፓርቲ የመለመላቸው ናቸው" ብለዋል።

"ከ200 በላይ ቢሮዎች ነበሩን አሁን ግን ሦስት ብቻ ነው ያሉን" በማለት በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ተንቀሳቅሰው የምርጫ እንቅስቀሴ ለማድረግ አዳጋች መሆኑን ተናግረዋል።

ከሁሉም በላይ አስደንጋጭ ሁኔታ የፀጥታ ጉዳይ ነው የሚሉት የኦፌኮ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር "በተደጋጋሚ እንደተናገርነው አሁን ባለው የፀጥታ ሁኔታ ኦሮሚያ ላይ ተወዳዳሪ፣ ታዛቢ ማቅረብ፣ ከዚያ በኋላ ደግሞ ተንቀሳቅሶ የምረጡኝ ዘመቻ ለማድረግ አመቺ አይደለም ብቻ ሳይሆን ብዙ የሚታሰብ አይደለም" ብለዋል።

በኦሮሚያ "ሰው በነጻ ተንቀሳቅሶ መመለሱ ችግር ውስጥ ገብቷል" ያሉት ፕሮፌሰር መረራ "ስለዚህ የአባሎቻችንን ሕይወት ለአደጋ ከማጋለጥ ውጪ ትርፍም አናገኝበትም" ሲሉ ተናግረዋል።

ከሁሉም በላይ የፀጥታ እና የፖለቲካ ምህዳሩ እጅግ በጣም እየጠበበ በመምጣቱ በኦሮሚያ ውስጥ ላለመወዳደር መወሰናቸውን ተናግረዋል።

"ምርጫ ሺዎችን ከቻልክ ሚሊዮኖችን የምታንቀሳቅስበት ነው" የሚሉት ፕሮፌሰር መረራ፣ በምርጫው ተወዳዳሪ ማቅረብ ብቻ ሳይሆን ተወዳዳሪዎቻችን ዋስትና ይፈልጋሉ በማለት ይህንን ማድረግ የሚቻልበት የፀጥታ ሁኔታ አለመኖሩን ተናግረዋል።

የፀጥታ ሁኔታውን ኃላፊነት መንግሥት እወስዳለሁ ቢል እንኳን "በግልጽ ቋንቋ በኦሮሚያ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች አይፈልጉም" ያሉት ፕሮፌሰር መረራ በዚህ መካከል አባሎቻቸውን እና ደጋፊዎቻቸውን ለአደጋ ማጋለጥ እንደማይፈልጉ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረገው ምርጫ ሁለት መሠረታዊ ነገሮች ካልመለሰ "ዋጋ አለው ብለን አናስብም" የሚሉት የኦፌኮ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር አንደኛው ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት አስተዋጽኦ ያደርጋል ወይ የሚለው ነው" ብለዋል።

"እኔ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለማዋለድ የሚያስቸል ነጻ እና ፍትሃዊ ምርጫ ይኖራል የሚል እምነት የለኝም።"

ሁለተኛው ደግሞ ምርጫው ሠላም እና መረጋጋት ያመጣል ወይ የሚለው ነው በማለት በኦሮሚያ እና በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ያሉት የፀጥታ ሁኔታዎች ሳይስተካከሉ ይህ አስቸጋሪ እንደሚሆን ተናግረዋል።

"ኢትዮጵያ ውስጥ ድሮውንም ቢሆን [በምርጫ] የሕይወት ዋጋ ስንከፍልበት ነበር። አሁን ደግሞ የባሰ ሁኔታ ስለመጣብን ዝም ብሎ አጉል ጨዋታ ውስጥ ላለመግባት ገምግመን . . . ለምርጫ አስቻይ ሁኔታ እንደሌለ በሙሉ ድምጽ ወስነናል።"

"እዚህ አገር ምርጫ ማለት መለስተኛ ጦርነት ማለት ነው" የሚሉት ፕሮፌሰር መረራ "ለደጋፊዎቻችን ዲሞክራሲ አለ፣ ምርጫ አለ ብለን ሕዝቡን ማወዛገብ፣ ሥራ ማስፈታት፣ የሕይወት ዋጋ ማስከፈል ተገቢ አይደለም።"

በአሁኑ ወቅት በኦሮሚያ በመንግሥት እና በታጣቂዎች መካከል ጦርነቶች እየተካሄዱ ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበሩ፣ በክልሉ ከመንግሥት ብቻ ሳይሆን ከታጣቂዎችም ጫና እንዳለባቸው ይናገራሉ።

"አሁን ባለው ሁኔታ ታጣቂዎቹም ምርጫው ነጻ እና ፍትሃዊ ስለማይሆን ለመንግሥት ሽፋን ለመስጠት ካልሆነ እዚህ ውስጥ መግባቱን እንደማይደግፉ ይታወቃል" ብለዋል።

በኦሮሚያ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ባለፈው አገራዊ ምርጫ በክልሉ በምርጫ ታዛቢነት የተሳተፉ ግለሰቦችን "በሌለ ምርጫ ለምን ታዛቢ ሆናችሁ በሚል ብዙ ሺህ ገንዘብ የተቀጡበት ሁኔታ አለ" ሲሉ አስታውሰዋል።

"መንግሥት እና ታጣቂዎች የፖለቲካ ስምምነት ላይ ባልደረሰቡት ሕዝቡን ወደ አላስፈላጊ ግጭት ማስገባት አንዱ ፍራቻችን ነው" ሲሉም ተናግረዋል።

ኦፌኮ አባላቱን ጨምሮ የፓርቲው መሪዎች ባለፉት ዓመታት መታሰራቸውን፣ የፓርቲው ጽህፈት ቤቶች መዘጋታቸውን በመግለጽ ነጻ እና ፍትሃዊ ምርጫ ይካሄዳል ብሎ እንደማያምን ይናገራል።

ኦፌኮ ማክሰኞ ዕለት ኅዳር 23 ባወጣው መግለጫ በአዲስ አበባ ብቻ ምርጫ እንደሚሳተፍ እና እስከ ምርጫው ድርስ ሁኔታዎች የሚሻሻሉ ከሆነ በሌሎች አካባቢዎችም ሊሳተፍ እንደሚችል ገልጿል።

ከቢቢሲ ጋር ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበሩ በነበራቸውም ቆይታ "ሐረር እና ድሬዳዋን" ለመጨመር እንደሚችሉ ተናግረዋል።

ፕሮፌሰር መረራ በዘህ ምርጫ አዲስ አበባ ላይ ይወዳደሩ እንደሆን ተጠይቀው "እኔን የሚያውቀኝ የአምቦ ሕዘብ ነው። . . . አምቦ ደግሞ ከሄድኩ አራት ዓመት አልፎኛል" በማለት እንደማይወዳደሩ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰባተኛው አገራዊ ምርጫ ግንቦት 24/2018 ዓ.ም. እንደሚካሄድ ጊዜያዊ የጊዜ ሰሌዳ አውጥቷል።