ማርስ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ መብረቅ መታየቱን ሳይንቲስቶች ገለጹ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሳይንቲስቶች ማርስ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የኤሌክትሪክ እንቅስቃሴ እንዳስተዋሉ እና ይህም ፕላኔቷ ላይ መብረቅ ሊከሰት እንደሚችል እንደሚጠቁም ይፋ አደረጉ።
እአአ በ2021 ናሳ ወደ ማርስ የላከው ተንቀሳቃሽ ሮቦት ፕሪሰርቪረንስ ሮቨር የተለያዩ ጥናቶችን እያካሄደ ይገኛል።
በማርስ ላይ ሕይወት መኖሩን ለማወቅ ላለፉት አራት ዓመታት አሰሳ ያደረገ ሲሆን፤ የኤሌክትሪክ እንቅስቃሴ መኖሩም የታወቀው በዚህ መሣሪያ አማካኝነት ነው።
ፕሪሰርቪረንስ ሮቨር፤ ማርስ ላይ የ45 ኪሎሜትር ስፋት ባለው ክፍተት ላይ ጥናት አድርጓል። ይህ ጃክሮ ክሬተር የተባለው ክፍተት ማርስ ላይ በአንድ ወቅት ወንዝ እንዳለ ይጠቁማል።
ሳይንቲስቶች የኤሌክትሪክ እንቅስቃሴውን "ትንሽ መብረቅ" ብለው ሰይመዋል። እንቅስቃሴው እንዳለ የታወቀው በድምጽ ሞገድ አማካኝነት ነው።
ፕሪሰርቪረንስ ሮቨር ድምጽ የሚቀዳ መሣሪያ ተገጥሞለታል። ከድምጽ ሞገድ ባሻገር ኤሌክትሮማግኔቲክ ሞገድም መዝግቧል።
ከማርስ ከባቢ አየር የመነጨውን የኤሌክትሪክ እንቅስቃሴ (atmospheric discharge) ለመለካት በጥልቀት ምሥል የሚያነሱ ካሜራዎች ወደ ማርስ ይላካሉ።
የፈረንሳይ የሕዋ ጥናት ባለሙያዎች የ28 ሰዓት የድምጽ ቅጂ ላይ ምርምር አድርገዋል።
የናሳ ፕሪሰርቪረንስ ሮቨር የቀዳው ድምጽ ርዝመት በማርስ ዘመን አቆጣጠር የ2 ዓመታት ሲሆን፤ በምድር ዘመን አቆጣጠር ደግሞ 1,374 ቀናት ወይም ሶስት ዓመት ከዘጠኝ ወር ገደማ ይሆናል።
ሳይንቲስቶቹ የድምጽ ቅጂውን ከሰሙ በኋላ የኤሌክትሪክ እንቅስቃሴው ከአቧራ እና ከአቧራ አውሎ ንፋስ ጋር ትስስር እንደሚኖረው ግምታቸውን አስቀምጠዋል።
ጠንካራው የአቧራ አውሎ ንፋስ (dust devils) በሞቃታማ አየር የሚፈጠው ነው። የአውሎ ንፋሱ እንቅስቃሴ ኤሌክትሪክ ሊያመነጭ ይችላል።
የጥናቱ ዋና ተመራማሪ ዶ/ር ባፕቲስ ቺዴ፤ ለሮይተርስ የዜና ወኪል እንደተናገሩት ግኝቱ "በጣም ትልቅ" ነው።
"የኤሌክትሪክ ልቀቱ ትልቅ ግኝት ነው። የማርስ ከባቢ አየር ያለውን የኬሚካል ይዘት፣ አየር ንብረቱን እንዲሁም ለመኖር ምቹ መሆኑን ለማወቅ ይረዳል። በቀጣይ ሮቦቶች እና ሰዎች ማርስን የበለጠ ያጠናሉ" ብለዋል ባለሙያው።
የኢንስቲትዩት ፎር ሪሰርች ኢን አስትሮፊዚክስ ኤንድ ፕላኒቶሎጂ ባለሙያዎች እንደሚሉት፤ መሬት፣ ሳተርን እና ጁፒተር በከባቢ አየራቸው የኤሌክትሪክ እንቅስቃሴ ያላቸው ፕላኔቶች ናቸው። አሁን ደግሞ ማርስም በዚህ ዝርዝር ውስጥ ተካትታለች።
ፓርቲክል ፊዚሲስት ዶ/ር ዳንኤል ፕሪቸርስ በኔቸር የሳይንስ መጽሔት ላይ ባሳተሙት ጽሑፍ እንዳሉት የድምጽ ቅጂው "አባሯ የተቀላቀለው የኤሌክትሪክ ልቀት መኖሩን" ያሳያል።
ቅጂው የድምጽ ብቻ መሆኑን በመጥቀስ "ምሥል አለመኖሩ ብዙዎች ጥያቄ እንዲያነሱ ማድረጉ አይቀርም። እውን ማርስ ላይ መብረቅ ታይቷል? የሚለውን የሚጠራጠሩ ይኖራሉ" ሲሉ አስረድተዋል።
ከዚህ ቀደም ማርስን በተመለከተ የተገለጹ ግኝቶች ለዓመታት አከራካሪ ሆነው ቆይተዋል። ይሄኛው ግኝትም አነጋጋሪ ሆኖ እንደሚዘልቅ ባለሙያው አክለዋል።
እአአ በ2025 መስከረም ላይ በማርስ ያልተለመደ ቅርጽ ያላቸው ዓለቶች መገኘታቸውን ሳይንቲስቶች አስታውቀዋል።
እነዚህ ዓለቶች ጥንታዊ ከሆኑ ጥቃቅን ነፍሳት (microbes) ጋር ትስስር ባላቸው ሚኒራሎች አማካኝነት የተፈጠሩ ሊሆኑ እንደሚችሉ ተገልጿል። ዓለቶቹ 'leopard spots' እና 'poppy seeds' ተብለዋል።
ሚኒራሎቹ የተፈጠሩት በማርስ እንቅስቃሴ አማካኝነት ቢሆንም እንኳን በፕላኔቷ ላይ ሕይወት ስለመኖሩ በግልጽ ያሳያሉ ተብለዋል።
አሁን ላይ ማርስ ቀዝቃዛ እና ባዶ ናት። ከቢሊዮን ዓመታት በፊት ጠንካራ ከባቢ አየር እና ውሃ እንደነበራት ይታመናል። ማርስ እንደቀደመው ዘመን ሕይወት ሊቀጥልባት የምትችል ፕላኔት ትሆናለች የሚለው መላ ምት መነሻም ይሄ ነው።
የናሳ ተንቀሳቃሽ ሮቦት ፕሪሰርቪረንስ ሮቨር ማርስ ላይ በሚገኘው ጃክሮ ክሬተር (Jezero Crater) በተባለው ክፍተት ላይ ጥናቱን ቀጥሏል።















