ፕሬዝዳንት ኢሳያስን በሁለት ወራት ወደ ሦስት አገራት የወሰዳቸው ምክንያት ምንድን ነው?

ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በሳዑዲ

የፎቶው ባለመብት, @hawelti

ከኢትዮጵያ ጋር እየተካሰሱ ያሉት የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በዙሪያቸው ካሉ አገራት ጋር ያላቸውን ግንኙነት በማጠናከር በሁለት ወራት ውስጥ ሦስተኛውን ይፋዊ ጉብኝታቸውን በሳዑዲ አረቢያ ለማድረግ ሪደድ ገብተዋል።

ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን መምጣት በኋላ ዋነኛ የተደጋጋሚ ጉብኝታቸው መዳረሻ ከነበረችው ኢትዮጵያ ጋር ሆድና ጀርባ የሆኑት ኢሳያስ አፈወርቂ ፊታቸውን ወደ ሌሎች አገራት አዙረዋል።

የፕሬዝዳንት ኢሳያስ የሳዑዲ ጉዞ ከተለመደው የሁለትዮሽ የጋራ ጉዳዮች ባሻገር በውስጡ ምን እንደያዘ ባይጠቀስም ለኤርትራም ለኢትዮጵያም ወዳጅ የሆነችው ሳዑዲ አረቢያ በተፈጠረው ውጥረት ዙሪያ ተጽዕኖ ሊኖራት ይችላል።

በአውሮፓውያኑ 2018 በኢሳያስ እና በዐቢይ መካከል በሳዑዲ አማካኝነት የተፈረመውን ስምምነት የሚያስታውሱት የአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች ተንታኙ አብዱራህማን ሰኢድ አቡ ሐሺም ግምታቸውን ያስቀምጣሉ።

ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ ጉብኝት ጋር ሳዑዲ የተበላሸውን የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ግንኙነትን ለማሻሻል ከዚህ በፊት የተፈረመው ግንኙነት "የሚያንሰራራበት ዕድል የሚኖር ከሆነ ሊመለከቱ ይችላሉ" ይላሉ።

በትግራይ በተካሄደው ጦርነት ውስጥ የኢትዮጵያ መንግሥትን ደግፈው ሠራዊታቸውን አሰማርተው የነበሩት ኢሳያስ ጦርነቱን ካስቆመው የፕሪቶሪያ ስምምነት በኋላ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር የነበቸራው ጠንካራ ወዳጅነት አብቅቷል።

በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያን የባሕር በር የማግኘት ጥያቄን አጥብቀው ማንሳቸታው በኤርትራ በኩል ስጋትን ከመፍጠሩ ባሻገር በሁለቱ አገራት መካከል ዳግም ጦርነት ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ስጋትን ፈጥሯል።

በአካባቢው ያላቸውን ተጽዕኖ ለማጠናከር ከተለያዩ አገራት እና ወገኖች ጋር ትብብራቸውን እያጠናከሩ ያሉት ሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ፉክክር ለፕሬዝዳንት ኢሳያስ የሪያድ ጉብኝት ምክንያት ሊሆን እንደሚችልም አብዱራህማን ይናገራሉ።

ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ባለፉት ጥቂት ወራት ከየመን ውጪ ባሉት ዋነኛ የቀይ ባሕር ተጎራባች አገራት ያደረጓቸውን እና እያደረጉት ያለውን ጉብኝት የኢትዮጵያ የባሕር በር ፍላጎት እየተጠናከረ መምጣት ምክንያት ነው የሚሉት የአፍሪካ ቀንድ ተንታኙ "ይህ ሁኔታ ለቀጣናው አስጊ ሁኔታን በመፍጠሩ ለመነጋገርም ሊሆን ይችላል" ሲሉ ይገምታሉ።

በኤርትራ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ውጥረት ከዛሬ ነገ ሊፈነዳ ይችላል የሚል የጦርነት ስጋት ተፈጥሯል። በተለይ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ፍጥጫ በዚህ ዓመት እየጠነከረ መጥቷል።

እምብዛም ለተደጋጋሚ ጉብኝት ከኤርትራ የመውጣት ልምድ የሌላቸው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ባለፉት ሁለት ወራት ውስጥ ግን ሦስት ጉብኝቶችን በቀይ ባሕር ዙሪያ ባሉ አገራት ውስጥ አድርገዋል።

እነዚህ አገራትም ግብፅ፣ ሱዳን እና ሳዑዲ አረቢያ ሲሆኑ ሁሉም እንደ ኤርትራ ሁሉ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር በኩል ደርሻ እንዳይኖራት የሚፈልጉ ናቸው። እንዲሁም አገራቱ ተመሳሳይ አቋም የሚያንጸባርቀው የቀይ ባሕር ትብብር መድረክ አባላት ናቸው።

በአገሪቱ የማስታወቂያ ሚኒስትር በኩል በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሚተላለፉት መልዕክቶች እንደሚያመለክቱት ሁሉም የፕሬዝዳንት ኢሳያስ ጉብኝቶች በተቀባይ አገራት መሪዎች ግብዣ እንደሆኑ ነው። በጉብኝቶቹም ከአገራቱ መሪዎች ከፍተኛ ባለሥልናት ጋር ውይይቶች መደረጋቸው በጥቅል ከመገለጹ ውጪ ዝርዝር ሁኔታዎች አይገለጹም።

ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በሳዑዲ

የፎቶው ባለመብት, @hawelti

የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በሳዑዲ

ኅዳር 30/2018 ዓ.ም.

ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በኅዳር የመጨረሻ ዕለት ለጉብኝት ከአሥመራ የወጡት የመካከለኛው ምሥራቅ ኃያል አገር እና ከቀይ ባሕር ባሻገር ወደምትገኘው ሳዑዲ አረቢያ ነው።

በአገሪቱ ንጉሥ ሳልማን ቢን አብዱልአዚዝ አል ሳዑድ ግብዣ ለአራት ቀናት ይደረጋል የተባለው የፕሬዝዳንቱ የሥራ ጉብኝት በሁለቱ አገራት ከፍተኛ ባለሥልጣናት መካከል በሁለትዮሽ እንዲሁም የጋራ በሆኑ በቀጣናዊ እና በዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት እንደሚደረግ ተገልጿል።

በተጨማሪም ፕሬዝዳንት ኢሳያስ እና ልዑካቸው ኃያሉን የሳዑዲ ልዑል አልጋወራሽ እና ጠቅላይ ሚኒስትር የሆኑትን ሞሐመድ ቢን ሰልማን እና ከፍተኛ የአገሪቱን ባለሥልጣናትን በቆይታቸው ወቅት እንደሚያገኙ ይጠበቃል።

በቅርቡ የወጡ ሪፖርቶች ሳዑዲ አረቢያ ኢትዮጵያ የይገባኛል ጥያቄ ባነሳችበት በአሰብ ወደብ ላይ ኢንቨስት እንድደታርግ ኤርትራ ጥያቄ ማቅረቧን ሲያመለክቱ ነበር።

ምጣኔ ሀብቷን ከነዳጅ ጥገኝነት ለማላቀቅ የተለያዩ ዕቅዶችን ይዛ እየሠራች ካለችው ሳዑዲ በኩልም በአፍሪካ እና በቀይ ባሕር ላይ ያላትን የምጣኔ ሀብት ተጽዕኖ ለማስፋት በአሰብ ላይ ፍላጎት እንዳላት ይነገራል።

ምናልባትም በዚህ የፕሬዝዳንት ኢሳያስ ጉብኝት ወቅት በሁለቱ አገራት በኩል በአሰብ ላይ ያለውን ዕቅድ በተመለከተ ውይይት እና ስምምነት ሊፈረም ይችላል።

በዚህ ደግሞ በኢትዮጵያ በኩል በጥብቅ እየተራመደ ካለው የባሕር በር የማግኘት ፍላጎት ጋር በተያያዘ ከተነሳው ውዝግብ ውስጥ ሳዑዲ አረቢያ ልትገባ ትችላለች።

ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በፖርት ሱዳን

የፎቶው ባለመብት, @hawelti

የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በፖርት ሱዳን

ኅዳር 20/2018 ዓ.ም.

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በኅዳር 20/2018 ዓ.ም. ለጉብኝት ያቀኑት ሦስት ዓመት ሊሞላው በተቃረበ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ወደምትገኘው ሱዳን ነበር። ግብዣውም መጣ የተባለው ከሱዳን ጦር ኃይሎች አዛዥ ከጄነራል አብደል ፋታህ አል ቡርሐን ነው።

በጄነራል ሐምዳን ዳጋሎ ከሚመራው ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ጋር እየተፋለሙ ያሉት ጄኔራል አል ቡርሐን ኢሳያስን የተቀበሉት ጥቃት ሽሽት መቀመጫቸው ባደረጓት የወደብ ከተማ ፖርት ሱዳን ውስጥ ነው።

ጄነራሉ በሕዳሴው ግድብ ምክንያት ከግብፅ ጋር ወግነው ኢትዮጵያን የሚቃወሙ ሲሆን፣ እየተካሄደ ባለው የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን ትደግፋለች ከምትባለው የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጋር ኢትዮጵያ ባላት ወዳጅነት ምክንያትም ደስተኛ አይደለችም።

ከሱዳን መሪዎች ጋር የቆየ ወዳጅነት ያላት ኤርትራ ለጦር ሠራዊቱ ግልጽ ድጋፍ አላት። በጥቅምት ወር የተደረገው የፕሬዝዳንት ኢሳያስ ጉብኝት የጄነራል አል ቡርሐን ኃይሎች ወሳኝ በሆነው የምዕራብ ሱዳን ግንባር ኤል-ፋሸር ውስጥ ሽንፈት በገጠማቸው ወቅት ነበር።

ፕሬዝዳንት ኢሳያስ እና ልዑካቸው በፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች በተደጋጋሚ የድሮን ጥቃት ወደተመታችው ፖርት ሱዳን ያቀኑት በመኪና ተጉዘው እንደነበር ተገልጿል። በዚህ ጉብኝት ወቅት በሁለቱ ወገኖች በኩል የጋራ ጉዳዮች ላይ ምክክር መደረጉ ከመነገሩ ውጪ ዝርዝር መረጃ አልወጣም።

ነገር ግን በተለያዩ የሱዳን አካባቢዎች ኃይሉን እያጠናከረ እና ይዞታውን እያሰፋ ያለው የሐምዳን ዳጋሎ ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ግስጋሴ ዋነኛው አጀንዳ እንደነበረ የሚታመን ሲሆን፣ ሌሎች የቀጣናው ጉዳዮችም በአጀንዳቸው ውስጥ መኖራቸው አይቀሬ ነው።

ከግብፅ፣ ከኤርትራ፣ ከሱዳን እና ከሳዑዲ አረቢያ ጋር መልካም ግንኙነት በሌላት የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ይደገፋል የሚባለው ፈጥኖ ደራሽ ኃይል በአገራቱ በስጋት የሚታይ ነው። ኤምሬትስ በሱዳን ጦርነት ውስጥ ሚና እንደሌላት ከማስተባበል በተጨማሪ ለማሸማገልም ትሞክራለች።

ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በግብፅ
የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በግብፅ

ጥቅምት 21/2018 ዓ.ም.

ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ግንኙነት ከተበላሸ በኋላ በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ምክንያት ከኢትዮጵያ ጋር ከምትወዛገበው ግብፅ ጋር ወዳጅነታቸውን አጠናክረዋል።

በተደጋጋሚ ወደ ግብፅ ከማቅናታቸው በተጨማሪ ፕሬዝዳንት አል-ሲሲም ወደ አሥመራ ሄደው ሶማሊያን የጨመረ የኢትዮጵያ ተቀናቃኝ ትብብር መመሥረታቸው ይታወሳል።

በዚህ ሁለት ወርም ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ረዘም ላለ ቀናት የቆየ ጉብኝት በግብፅ ውስጥ አድርገዋል። ጥቅምት 21/2018 ዓ.ም. የተጀመረው ጉብኝቱ ለአምስት ቀናት የቆየ ሲሆን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸውን አስከትለው ነበር የተጓዙት።

በፕሬዝዳንት አል-ሲሲ ግብዣ የተካሄደ ነው በተባለው በዚህ ጉብኝት ላይ ሁለቱ መሪዎች ያላቸውን የሁለትዮች ግንኙነት በማጠናከር አንዲሁም በቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት ከማድረጋቸው በተጨማሪ ኢሳያስ በግዙፉ የግብፅ ብሔራዊ ሙዚያም ምረቃ ላይ ታድመው ነበር።

በጉብኝቱ ማብቂያ ላይ ከፕሬዝዳንት አል ሲሲ ጽሕፈት ቤት የወጣ መግለጫ ደግሞ በሁለቱ ፕሬዝዳንቶች ውይይት ወቅት ግብፅ "የኤርትራን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ለመደገፍ ቁርጠኛ" መሆኗን በመግለጽ በተዘዋዋሪ የባሕር በር ጥያቄ እያነሳች ላለችው ኢትዮጵያ የተላለፈ መልዕክት ነው።