በሕንድ ባለሥልጣን ነን ያሉ ሰዎች ገንዘብ የጫና የባንክ መኪና አስቁመው ዘረፉ

የፖሊስ መኪና

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የሕንድ ማዕከላዊ ባንክ ባለሥልጣናት መስለው ገንዘብ እያጓጓዘ የነበረን መኪናን አስቁመው 800 ሺህ ዶላር መዘረፉን በደቡባዊ ሕንድ የምግትገኘው ካርናታካ ግዛት ፖሊስ አስታወቀ።

በሕንድ ገንዘብ 70 ሚሊዮን ሩፒ የሚሆነውን ይህን ገንዘብ፣ ከግዛቲቱ ዋና ከተማ ቤንጋሉሩ ማዕከላዊ ክፍል ውስጥ በጠራራ ፀሐይ መኪናውን አስቁመው የዘረፉትን ሌቦች ለመያዝ ፖሊስ መጠነ ሰፊ አሰሳ እያካሄደ መሆኑንም ገልጿል።

የከተማዋ ፖሊስ አዛዥ ሲማንት ኩማር ሲንግ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ ዘረፋው የተፈጸመው ረቡዕ ከሰዓት በኋላ ነበር። በቅንጡ መኪና የመጡ ስድስት ሰዎች ወደ ባንክ ቅርንጫፎች ገንዘብ እያጓጓዘ የነበረውን ተሽከርካሪ እንቅስቃሴ በሚበዛበት መንገድ ላይ አስቁመው ነው የዘረፉት።

በዘረፋው ወቅት በባንኩ ተሽከርካሪ ውስጥ ሾፌሩ፣ ገንዘቡን የሚቆጣጠር የባንክ ሠራተኛ እና ሁለት የታጠቁ ጠባቂዎች ነበሩ።

ዘራፊዎቹ መኪናውን አስቁመው የሕንድ ማዕከላዊ ባንክ ባለሥልጣናት መሆናቸውን እና ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ሲያጓጉዙ ተገቢውን ሰነድ ይዘው እንደሆነ ለመረጋገጥ መሆኑን ነግረዋቸው እንደነበር የፖሊስ ባለሥልጣኑ ተናግረዋል።

ዘራፊዎቹ የመኪናውን ሹፌር ቦታው ላይ ሆኖ መንዳቱን እንዲቀጥል፣ የባንኩን ሠራተኛ እና የታጠቁትን ጠባቂዎች ደግሞ መሳሪያቸውን መኪናው ውስጥ ትተው ወደራሳቸው ቅንጡ መኪና እንዲገቡ በማዘዝ ነው ዝርፊያው የተፈጸመው ሲል ፖሊስ አስታውቋል።

ገንዘብ የጫነው መኪና ሹፌርን ከመኪናው አስገድደው እስኪያስወርዱት ድረስ ለተወሰነ ኪሎ ሜትር የወሰዱት ሲሆን፣ በራሳቸው መኪና ይዘዋቸው የነበሩትን የባንኩን ሠራተኛ እና ጠባቂዎችን አስወርደው መሳሪያ በመደቀን ገንዘቡን ወዳራሳቸው መኪና አሸጋግረው ተሰውረዋል።

ዝርዘፊያው የተፈጸመበት አካባቢ በቂ የደኅንነት ካሜራ ቁጥጥር ያለበት በመሆኑ ዘራፊዎቹ በርከት ያሉ ተሽከርካሪዎችን ተጠቅመው እንደሆነ ለማወቅ ምርመራ እያደረገ ነው።

ገንዘብ የማጓጓዝ አግልግሎት የሚሰጠው እና ዝርፊያው የተፈጸመበት ካምፓኒ ለፖሊስ ክስ አቅርቧል።

ዘራፊዎቹ ይዘውት የነበረው ቅንጡ መኪና ሐሰተኛ የሰሌዳ ቁጥር እና "የሕንድ መንግሥት" የሚል ጽሁፍ ለጥፎ እንደነበረ አንድ ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈቀደ የፖሊስ አባል ለቢቢሲ ተናግሯል።

ባለሥልጣናት እንዳሉት የገንዘብ ማጓጓዝ አገልግሎት የሚሰጠው ድርጅት ሠራተኞች በዘረፋው ውስጥ እጃቸው ይኖር እንደሆነ ለማጣራት ፖሊስ ምርመራ እያደረገ ነው።

ዘረፋው የተፈጸመባት ቅንጡ መኪና በፖሊስ መገኘቷን የግዛቲቱ ዋና አስተዳዳሪ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

ነገር ግን ሌላ ባለሥልጣን ዘራፊዎቹ በምን ዓይነት መኪና እንዳመለጡ ግልጽ አይደለም ሲሉ ገልጸዋል።

"መኪና ቀይረው ገንዘቡን በማዘዋወር ማምለጣቸው ተረጋግጧል" ሲሉ ተናግረዋል።

ባለሥልጣኑ ጨምረውም በቅርቡ በግዛቲቱ ውስጥ የተፈጸመውን ከፍተኛ የባንክ ዝርፊያን ተከታትለው የደረሱበት ፖሊሶች፣ እነዚህንም በአጭር ጊዜ ውስጥ በቁጥጥር ስር እንደሚያውሏቸው እምነታቸውን ገልጸዋል።

ፖሊስ ባለፈው ዓመት ግንቦትወር ላይ ወደ ስድስት ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ 59 ኪሎ ግራም ወርቅ ከአንድ ባንክ የተዘረፈ ሲሆን፣ አስካሁን 39 ኪሎ ግራም ወርቅ እና የተወሰነ ብር አስመልሶ ሁለት የባንኩ የቀድሞ ሠራተኞችን ጨምሮ 15 ሰዎችን በቁጥጥር ስር አውሏል።