በእስራኤል ጥቃት እየተፈተኑ በሥልጣን ላይ አንድ ዓመት የሆናቸው የኢራኑ ፕሬዝዳንት

የፎቶው ባለመብት, AFP
ማሱድ ፔዜሽኪያን ሐምሌ 2024 የኢራን ፕሬዝዳንት ሆነው ከተሾሙ ከአንድ ቀን በኋላ በቀጥታ ወደ ፖለቲካ እሳት ውስጥ ገብተዋል።
ቃለ መሃላ ከፈፀሙ ከሰዓታት በኋላ በምሥረታው ላይ ከተገኙ ታዋቂ እንግዶች መካከል አንዱ የሆኑት የሐማስ መሪ ኢስማኢል ሃኒዬ በእስራኤል ጥቃት ተገደሉ የሚለው ዜና ተሰማ።
ግድያው የተፈጸመው ደግሞ በጋዛ ሳይሆን በመሃል ቴህራን ነው። ኢራን ሐማስን በገንዘብ፣ በጦር መሳሪያ እና በፖለቲካዊ ደጋፊ ነበረች።
ግድያው በቀጠናው ከፍተኛ ድንጋጤ ፈጥሯል፤ እናም አልጋ በአልጋ የሆነ ሽግግርን ህልም አንኮታኩቶታል።
ይህም አለመረጋጋት በሌለው በኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ መሪዎች ታሪክ ውስጥ ከታዩት ጅማሪዎች መካከል እጅግ አስደንጋጩ እና በቀውስ የታጀበ ነበር።
ከተስፋ ወደ መከራ
ፔዝሽኪያን በዚህ ብሔራዊ ድንጋጤ ውስጥ ሆነው ነው ወደ ሥልጣን የወጡት።
ከእርሳቸው በፊት የነበሩት ጠንካራው ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራኢሲ ከኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር በሄሊኮፕተር አደጋ ተገድለዋል።
ይህ ያልተለመደ ክስተት አገሪቱን በሳምንታት ውስጥ አስቸኳይ ምርጫ እንድታደርግ አስገድዷታል።
በዚያች ጠባብ ቀዳዳ የሾኩት የልብ ቀዶ ሕክምና ባለሙያው፣ የቀድሞ የጤና ሚኒስትር እና የፓርላማ አባል ፔዝሽኪያን የአገሪቱን ከፍተኛ ሥልጣን ተረከቡ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ፕሬዝዳንቱ በሂጃብ አለባበስ ላይ ያሉ ደንቦች እና በማኅበራዊ ገደቦች ላይ ያላቸው የተለሳለሰ አቋም እና ከምዕራቡ ዓለም ጋር ከመጋጨት ይልቅ ለመነጋገር ቃል መግባታቸው በማዕቀብ ለደከመችው አገር የተስፋ ጭላንጭል የሰጠ ነው።
ነገር ግን የፕሬዝዳንትነቱን ቦታ ይዘው በወራት ውስጥ እስራኤል ከባድ ጥቃቶችን ፈጸመች።
አሜሪካም ይህንን ተከትላ በኢራን የኒውክሌር ተቋማት ላይ ድብደባ ፈፀመች።
ቀድሞውንም ደካማ የነበረው የአገሪቱ ምጣኔ ሃብት የበለጠ ተደቆሰ።
በመላ አገሪቱ የኤሌትሪክ ኃይል እና የውሃ እጥረት ተከሰተ።
እአአ በ2024 ለአጭር ጊዜ ብልጭ ያለው ብሩህ ተስፋ ወደ ተስፋ መቁረጥ የተለወጠ መሰለ።
የኢራኑ ፕሬዚዳንት ለምን አቅመ ቢስ ሆኑ?
አጭሩ መልስ የኢራን ፕሬዚዳንት ያስተዳድራል እንጂ ገዢ ወይንም መሪ አይደለም የሚለው ነው።
እንደ ሌሎች አገራት የኢራን ፕሬዝዳንት በግዛቱ ውስጥ ከፍተኛ ሥልጣን ያላቸው ሰው አይደሉም።
በእስላማዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት እውነተኛው ሥልጣን ያለው በጠቅላይ መሪው እጅ ነው።
እአአ ከ1989 ጀምሮ ያ ቦታ በጦር ኃይሉ፣ በፍትሕ አካላት፣ በስለላ አገልግሎቶች እና በወሳኙ የውጭ ፖሊሲ ላይ ከፍተኛ ቁጥጥር በሚያደርጉት በአያቶላ አሊ ኻሜኔ እጅ ተይዘዋል።
ፔዝሽኪያን የፕሬዚዳንትነት ወንበሩን አሸንፈው ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ሥልጣኑ ሁልጊዜ በሥርዓቱ ያልተመረጡ የሥልጣን ማዕከላት ማለትም በአብዮታዊ ዘብ፣ የበላይ ጠባቂው ምክር ቤት እና በጠቅላይ መሪው ጽ / ቤት የተገደበ ነው።
የካቢኔ አባላቱን እንኳን የጠቅላይ መሪውን ይሁንታ ማግኘት ይጠበቅባቸዋል።
ወደ ዲፕሎማሲው ሲመጣ፣ በኒውክሌር መርሃ ግብርም ሆነ በቀጠናዊ ውጣጥረቶች ምላሽ ሲሰጡ ፔዝሽኪያን ብዙ ጊዜ እንደ ውሳኔ ሰጪ ሳይሆን እንደ ቃል አቀባይ በሌላ ቦታ ተወስነው የመጡ ጉዳዮችን ያስፈጽማሉ።

የፎቶው ባለመብት, Majid Saeedi / Getty Images
በጣም አስፈላጊ የሆነው ሌላ ምርጫ
በኢራናውያን ዘንድ "የአሜሪካ ምርጫ የሚያስከትለው ዳጋ የሚመለከተው እኛን ስለሆነ በምርጫው ላይ ድምጽ እንድንሰጥ መፈቀድ አለበት" የሚል ረዥም ዓመት ያስቆጠረ ቀልድ አለ።
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ዋይት ሐውስ ዳግም መመለሳቸውን ተከትሎ ይህ ከመቼውም ጊዜ በላይ እውነት ነበር።
የትራምፕን ለሁለተኛ ጊዜ መመረጥ ብዙዎች ለቴህራን በጣም መጥፎ አ���ጣሚ አድርገው ነው ያዩት።
የመጀመሪያው የፕሬዝዳንትነት የሥልጣን ዘመናቸው የአሜሪካ እና የኢራንን ግንኙነት ወደ ገደል አፋፍ ገፍቶታል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት በአንድ ወገን ኢራን በትጋት ከተደራደረችው የኒውክሌር ስምምነት አገራቸውን አስወጥተው ከባድ ማዕቀቦችን የጣሉ ሲሆን፣ የኢራን ከፍተኛ ወታደራዊ ባለሥልጣን የሆኑት ጄኔራል ቃሴም ሱሌይማኒ እንዲገደሉ አዝዘዋል።
የትራምፕ ወደ ሥልጣን መመለስ ችግርን እየመጣ መሆኑን አመልክቷል፤ ኢራንም ይህንኑ ታውቃለች።
ብዙም ሳይቆይ እስራኤል በኢራን ቀጣናዊ አጋሮች ማለትም በጋዛ በሐማስ፣ በሊባኖስ በሒዝቦላህ እና በየመን በሁቲዎች ላይ ወታደራዊ ዘመቻዋን አጠናክራለች።
ከዚያ በኋላ የተከተለው ዓመት በተባባሰ ግጭት የጠነከረ ነበር።
ለፔዜሽኪያን ይህ በጣም የከፋው ጊዜ ነበር። ለስላሳ የሆኑት ፕሬዚዳንት ከሁለት ወገን በሚሰነዘርባቸው ትችት እና ነቀፋ ተያዙ።
ከአሜሪካ እና እስራኤል በኩል የሚያላጋቸውን ማዕበል ለመቀየር ምንም ዓይነት አቅም አልነበራቸውም።

የፎቶው ባለመብት, Majid Saeedi / Getty Images
'አንተ ዜሌንስኪ አይደለህም'
ከእስራኤል ጋር ለ12 ቀናት በዘለቀው ጦርነት ያሳዩት ባህሪ በሕዝብ ዘንድ ተስፋ መቁረጥን ፈጥሯል።
እስራኤል በኢራን ላይ ጥቃት የጀመረችው ባለፈው ሰኔ መጀመሪያ ላይ በኢራን ምድር ላይ መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ በከፈተችበት ወቅት ነበር።
በርካታ የኢራን ከተሞች ከፍተኛ የአየር ጥቃት ደርሶባቸዋል፤ ይህም በሰላማዊ ሰዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል።
በዚህ ወቅት ፔዝሽኪያን በችግር ውስጥ ያለን ሕዝብ የሚመሩ መሪ መስለው ሊታዩ አልቻሉም።
የኢራን ከተሞች በእስራኤል ቦምቦች እና ሚሳዔሎች ሲደበደቡ እና ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ሲገደሉ ፕሬዝዳንቱ ልክ እንደ ጠቅላይ መሪው ዝምታን መረጡ።
ቀስቃሽ ንግግሮች የሉም፤ ወሳኝ የሆኑ ነገሮች ላይ አልታዩም። እንዲሁም በእስራኤል ሚሳዔል ፍዳውን ለሚያየው ሕዝብ ተገቢ የሆነ የግንኙነት መስመር አልነበራቸውም።
በሌሎች ቦታዎች ከሚገኙ የጦርነት ጊዜ መሪዎች ጋር ያላቸው ልዩነት በጣም አስደናቂ ነበር።
አንዳንድ ኢራናውያን ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ "አንተ ዜሌንስኪ አይደለህም" ሲሉ የዩክሬን ፕሬዝዳንት ሩሲያ አገራቸውን በወረረችበት ወቅት ካሳዩት አመራር ጋር አነጻጽረዋቸዋል።
የኢራን ሕዝብ ማፅናናትን እና መፍትሄን በሚፈልግበት በዚያ ወቅት፣ ፔዝሽኪያን አፋቸው እንደተሸበበ ታየ፤ እና ለብዙዎች ይህ ከመሪ የማይጠበቅ እና አግባብነት የሌለው ተግባር ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Majid Saeedi / Getty Images
ሂጃብ ፣ ጭቆና እና ማኅበራዊ ቅርቃር
በኢራን ውስጥ ያለው ማኅበራዊ ገጽታም በውጥረት የተሞላ ነው። በ2022 አገሪቱን ያናወጠው የተቃውሞ እንቅስቃሴ ይመራ የነበረው "ሴት ፣ ሕይወት፣ ነፃነት" በሚል መፈክር ነበር።
ይህ በመላ አገሪቱ የተቀሰቀሰው የተቃውሞ ድምጽ በአብዛኛው ጋብ ያለ ቢሆንም፣ ነገር ግን ከኋላው ያሉት ጥያቄዎች እና ቁጣዎች አልተመለሱም።
ሴቶች ሂጃብ በግዴታ እንዲለብሱ የሚደነግገውን ሕግ መተላለፋቸውን ቀጥለዋል።
አክቲቪስቶች፣ ጋዜጠኞች እና ተማሪዎች እየታሰሩ ነው።
ፔዝሽኪያን "ብሔራዊ እርቅ" እና "የጋራ መከባበር" እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።
"ከጋብቻ ውጪ የሚደረግ ግንኙነትን እና የሂጃብ ሕግን ማስከበር አልችልም፤ ምክንያቱም በሰዎች ላይ ችግር ስለሚፈጥር ከሕዝቡ በተቃራኒ አልቆምም" ሲሉ በይፋ ተናግረዋል።
ነገር ግን ብዙ ኢራናውያን፣ በተለይም ወጣቶች፣ እንደዚህ ዓይነት ቃላቶች ምሳሌያዊ ሊሆኑ እንደሚችሉ ግን የማይጠቅሙ እንደሆኑ አድርገው ይመለከቷቸዋል።
የሥርዓቱ አፋኝ ባህሪ ሳይነካ ባለበት ቀጥሏል።
እናም ያለ መዋቅራዊ ለውጥ፣ ለስላሳ ንግግር ፋይዳው ኢምንት ነው።

የፎቶው ባለመብት, Atta Kenare / AFP via Getty Images
በይደር የቆየ ችግር
ለበርካታ ኢራናውያን የፔዝሽኪያን የፕሬዝዳንትነት አንድ ዓመት ሥልጣን ምንም ለውጥ አላመጣም።
የዋጋ ንረት ጨምሯል፣ የኤሌትሪክ ኃይል መቆራረጡ ቀጥሏል፤ የፖለቲካ ነፃነቶች ባሉበት ደርቀው ቆመዋል።
በመንግሥት እና በሕብረተሰቡ መካከል ያለው ልዩነትም እየሰፋ ሄዷል።
ፕሬዝዳንቱ ስለ አንድነት ሊናገሩ ይችላሉ፤ ነገር ግን አንድነት፣ በተለይም እውነተኛ ሥልጣን ከቢሮው ሩቅ በሆነበት በዚህ ሁኔታ በአዋጅ ሊመጣ አይችልም።
ኢራን በዲፕሎማሲያዊ፣ በኢኮኖሚያዊ እና በማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ በይደር የማይቆይ ጥያቄ ገጥሟታል።
አመራሩ መንገዱን መቀየር ካልቻለ ወይም ካልፈቀደ ተንታኞች እንደሚናገሩት የሚቀጥለው ስብራት ከእስራኤል ሚሳዔል ወይም ከአሜሪካ ማዕቀብ ሳይሆን ከአገር ውስጥ የሚመጣ ነው።















