እስራኤል 15 የጦር አውሮፕላኖችን አሰማርታ ኳታር ውስጥ የፈጸመችው ጥቃት

ከጥቃቱ በኋላ የሚታይ ጭስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ፍልስጤማዊው ቡድን ሐማስ እስራኤል በኳታር ዋና ከተማ ዶሃ ላይ በፈጸመችው የአየር ጥቃት አምስት አባላቱን መገደላቸውን ቢያምንም፣ ከእስራኤል ጋር በሚደረገው ድርድር ተሳታፊ የሆኑት የቡድኑ ተወካዮችን ለመግደል የተደረገው ሙከራ ግን "ከሽፏል" ብሏል።

ሐማስ አክሎም እስራኤል ዶሃ የሚገኙትን የቡድኑን ተደራዳሪ ልዑካንን ለመግደል ድንገተኛ የአየር ጥቃት የሰነዘረችበት ተደራዳሪ ቡድኑ በቅርቡ አሜሪካ በጋዛ ሰርጥ የተኩስ አቁም እንዲደረስ ባቀረበችው ሃሳብ ላይ ለመወያየት በተገናኘበት ጊዜ ነው ብሏል።

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በኳታር የመኖሪያ ሕንጻ ላይ የተፈጸመው ጥቃት "ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት ያለው ነው" በማለት በጋዛ ጦርነት የቀሰቀሰውን የመስከረም 26/2016 ዓ.ም. ጥቃትን ያቀናበሩ እና የመሩ የሐማስ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ላይ ያነጣጠረ ነው ብለዋል።

ኳታር በግዛቷ ውስጥ በእስራኤል የተፈጸመውን ጥቃት "የፈሪ ዱላ" እና "ዓለም አቀፍ ሕግን በግልጽ የጣሰ" በማለት አውግዛዋለች።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ዎል ስትሪት ጆርናል እንደዘገበው የሐማስ መሪዎች ጥቃቱ ከመፈፀሙ በፊት ባሉት ሳምንታት ውስጥ ግልጽ ያልሆነ፣ ነገር ግን ከባድ ማስጠንቀቂያ ደርሷቸው ነበር።

ጋዜጣው "የግብፅ እና የቱርክ ባለሥልጣናት 'ስብሰባ በምታደርጉበት ስፍራ ያለውን የደኅንነት ጥበቃ አጠናክሩ' ብለው ነግረዋቸዋል" ሲል ዘግቧል።

የሐማስ መሪዎች ለጥቂት ያመለጡበት ጥቃት

እስራኤል ኳታር ውስጥ ባልተጠበቀ ሁኔታ በፈጸመችው ጥቃት የኳታር የፀጥታ ኃይል አባላት መገደላቸውን እና የመቁስል ጉዳት መድረሱን የአገሪቱ ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።

ሐማስ በበኩሉ በጥቃቱ ተገድለዋል ያላቸውን ስድስት ሰዎች በስም ዘርዝሮ አሳውቋል። አምስቱ የቡድኑ አባል መሆናቸውን እና ስድስተኛው የኳታር የአገር ውስጥ ደኅንነት አባል መሆኑንም ጨምሮ አመልክቷል።

ጥቃቱን ተከትሎ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በእስራኤል የአየር ጥቃት "ደስተኛ አይደለሁም" ሲሉ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ ላይ አሳውቀዋል። "ታጋቾች እንዲለቀቁ እንፈልጋለን፣ ነገር ግን ዛሬ በሆነው ነገር [ኳታር ውስጥ በተፈጸመው ጥቃት] ደስተኛ አይደለንም" ብለዋል።

አሜሪካ የእስራኤል የቅርብ አጋር ብትሆንም፣ ኳታርም በበኩሏ በባሕረ ሰላጤው አካባቢ የአሜሪካ ዋነኛዋ ወዳጅ ናት። በግዛቷ ውስጥም ግዙፍ የአሜሪካ የአየር ኃይል ጦር ሰፈር ይገኛል።

በተጨማሪ ደግሞ ከአውሮፓውያኑ 2012 ጀምሮ የሐማስ የፖለቲካ ቢሮ ኳታር ውስጥ የሚገኝ ሲሆን፣ በእስራኤል እና በሐማስ መካከል የሚካሄደውን ቀጥተኛ ያልሆነ ድርድር ከግብፅ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬት ጋር በመሆን የምትመራው ኳታር ናት።

ከርቀት የሚታይ እሳት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ጥቃቱ በተፈጸመበት ጊዜ

15 ተዋጊ አውሮፕላኖች የተሰማሩበት ጥቃት

በኳታር ዋና ከተማ ዶሃ ውስጥ ማክሰኞ ጳጉሜ 4/2017 ዓ.ም. እስራኤል ጥቃት የፈጸመችው በርካታ የሐማስ ፖለቲካ ቢሮ ባለሥልጣናት በሚኖሩበት የመኖሪያ አካባቢ ላይ ነው።

ከሰዓት በኋላ በተፈጸመው ጥቃት አስከ ስምንት የሚደርሱ ፍንዳታዎችን እና ከፍተኛ ጭስ በዶሃ ሰሜናዊ ክፍል ላይ ማየታቸውን ዓይን እማኞች ተናግረዋል።

ከጥቃቱ ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ እስራኤል ለተፈጸመው ጥቃት በይፋ ኃላፊነቱን ወስዳለች።

የእስራኤል ጦር ኃይል እና የአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት የሆነው ሽን ቤት "በሐማስ አመራሮችን ዒላማ ያደረገ ጥቃት" መፈጻማቸውን የሚገልጽ መግለጫ አውጥተዋል።

በመከተል ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁ እና የመከላከያ ሚኒስትሩ ኢዝራኤል ካትዝ ኢየሩሳሌም ውስጥ ፍልስጤማዊ ታጣቂዎች ስድስት ሰዎች የገደሉበትን የሰኞ ዕለት ጥቃትን እና ጋዛ ውስጥ አራት የእስራኤል ወታዳሮች መገደላቸውን ተከትሎ ዶሃ ውስጥ ለሚፈጸመው ጥቃት ትዕዛዝ መሰጠቱን ገልጸዋል።

የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ኳታር ውስጥ በተፈጸመው ጥቃት 15 ተዋጊ አውሮፕላኖች የተሳተፉ ሲሆን፣ ዒላማ በተደረገው ቤት ላይ በሰከንዶች ውስጥ 10 ሚሳዔሎችን ተኩሰዋል።

አንድ የእስራኤል ባለሥልጣን በጥቃቱ ዒላማ ከተደረጉት የሐማስ መሪዎች መካከል ከእስራኤል ጋር በሚደረጉት ድርድሮች ቡድኑን በመወከል ዋነኛ ተደራዳሪ የሆኑት ኻሊል አል-ሃያ እና ዛሂር ጃባሪን ይገኙበት ነበር ብለዋል።

የአሜሪካ ጦር አውሮፕላን

የፎቶው ባለመብት, US Department of Defense

የምስሉ መግለጫ, በመካከለኛው ምሥራቅ ትልቁ የአሜሪካ የአየር ኃይል ጦር ሰፈር ያለው ኳታር ውስጥ ነው

ጥቃቱ እና የአሜሪካ አቋም

ሐማስ በአባላቱ ላይ ኳታር ውስጥ የተፈጸመውን ጥቃት ባወጣው መግለጫ "ጭካኔ የተሞላበት ወንጀል፣ ጠብ ጫሪነት እና የዓለም አቀፍ ሕግ ጥሰት" በማለት አጥብቆ አውግዞታል።

በተጨማሪም እስራኤል ተደራዳሪዎቹን ዒላማ ማድረጓ በአሜሪካው ፕሬዝዳንት የቀረበውን አዲስ የስምምነት ሃሳብ ኔታኒያሁ እና መንግሥታቸው ለመቀበል ፍላጎት እንደሌላቸው ያሳየ ነው በማለት "ጠላታችን [እስራኤል] የተደራዳሪ ልዑካኖቻችንን ለመግደል ያደረገችው ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል" በማለት በጥቃቱ አመራሮቹ አለመገደላቸውን አረጋግጧል።

ሐማስ ለጥቃቱ ተጠያቂ ያደረገው ኃላፊነቱን የወሰደችው እስራኤልን ብቻ ሳይሆን፣ ለእስራኤል ሠራዊት ድጋፍ ያደርጋል ያለውን የአሜሪካ መንግሥትን ጭምር ነው።

እስራኤል ጥቃቱን ከመፈጸሟ በፊት ለአሜሪካ ጦር ሠራዊት ማሳወቋን የገለጸው የፕሬዝዳንት ትራምፕ ጽህፈት ቤት በኳታር ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ተቃውሞታል።

የዋይት ሐውስ ቃል አቀባይ ካሮላይን ሌቬት "የአሜሪካ የቅርብ አጋር በሆነችው፣ ሉዓላዊቷ እና ሰላም ለማምጣት እየጣረች ባላችው ኳታር ላይ የተፈጸመው ጥቃት የእስራኤልንም ሆነ የአሜሪካንን ዓላማ አያሳካም" በማለት ተናገራለች።

ጨምራም "ነገር ግን በጋዛ ሕዝብ ስቃይ እየቆመሩ ያሉትን የሐማስ አመራሮች መደምሰስ የሚደነቅ ግብ ነው" በማለት እስራኤል ሐማስ መሪዎች ላይ የምትወስደውን እርምጃ አሜሪካ እንደምትደግፈው ገልጻለች።

አሜሪካ ከእስራኤል ጥቃት በኋላ ጉዳዩን ለኳታር ብታስታውቅም አገሪቱ በሉዓላዊነቷ ላይ የተፈጸመ ጥቃት በመሆኑ ቁጣዋን ገልጻለች። ፕሬዝዳንት ትራምፕም ከኳታር ኢሚር እና ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ባደረጉት ውይይት ተመሳሳይ ጥቃት እንደማይፈጸም አረጋግጠውላቸዋል።

የጥቃቱ ዒላማ የሆነው ሕንጻ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የጥቃቱ ዒላማ የሆነው ሕንጻ

ተቃውሞ እና ዛቻ

የኳታር መንግሥት ጥቃቱን "የወንጀል ድርጊት" በማለት ግልጽ የዓለም አቀፍ ሕግ እና ደንብ ጥሰት እንደሆነ እና በኳታር ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች "ከባድ ስጋት" ነው ሲል በጽኑ አውግዞታል።

የአረብ አገራት በእስራኤል ላይ ተቃውሞ ማሰማት የጀመሩት ጥቃቱ መፈጸሙን ተከትሎ ነው። በዚህም ዮርዳኖስ፣ ግብፅ፣ ሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤምርትስ ጥቃቱን "ጠብ አጫሪነት" እና "ጭካኔ የተሞላበት የእስራኤል ጥቃት" ሲሉ አውግዘውታል።

የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፣ የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን፣ የብሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር፣ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ሊዮ 14ኛ ይገኙበታል።

ከጥቃቱ አንድ ቀን ቀደም ብሎ የእስራኤል የመከላከያ ሚኒስትር ኢስራኤል ካትዝ ሐማስ ታጋቾችን ለቅቆ ትጥቅ ካልፈታ በውጭ አገራት የሚገኙት መሪዎቹ "እንደሚደመሰሱ" እና ጋዛ "እንደምትወድም" አስጠንቅቀው ነበር።

ከዚህ ቀደም ብሎ ሐማስ የተኩስ አቁም ስለማድረግ እና ታጋቾች መለቀቅን በተመለከተ በአሜሪካ በቀረበው የስምምነት ሰነድ ላይ ከአደራዳሪዎች ጋር ግንኙነት እያደረገ መሆኑን አሳውቆ ነበር።

ትራምፕ ምንም ዓይነት ዝርዝር ሳይሰጡ እስራኤል የቀረበውን የስምምነት ሃሳብ እንደተቀበለችው አመልክተው ሐማስም እንዲስማማ "የመጨረሻ" ያሉትን "ማስጠንቀቂያ" ሰጥተው ነበር። ነገር ግን የትራምፕ ማስጠንቀቂያ እስራኤል ኳታር ውስጥ ከፈጸመችው ጥቃት ጋር እንደማይያያዝ የአሜሪካ ባለሥልጣናት አስተባብለዋል።

የፀጥታ ምክር ቤት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታ ምክር ቤት ጥቃቱን አውግዞታል

የጨነገፈው ድርድር

የፍልስጤም ባለሥልጣናት ለቢቢሲ እንደተናገሩት በአሜሪካ የቀረበው ስምምነት ሐማስ ሁሉንም ታጋቾች በ48 ሰዓትት እንዲለቅ፣ የ60 ቀናት ተኩስ አቁም እንዲደረግ፣ በእስራኤል እስር ቤቶች የሚገኙ ፍልስጤማውያን እንዲለቀቁ እና የዘላቂ ተኩስ አቁም ድርድር እንዲካሄድ ያቀደ ነበር።

በድርድር በጋዛ ውስጥ የሚካሄደው ጦርነት እንዲያበቃ ከማድረግ ይልቅ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ሌላ መንገድን መርጠዋል። በኳታር ውስጥ ጥቃተ ከተፈጸመ በኋላ ምሽት ኢየሩሳሌመ ወስጥ በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ለተሰበሰቡ ሰዎቸ ኔታኒያሁ ባደረጉት ንግግር አገራቸው ኳታር ላይ የወሰደችው እርምጃ "ጦርነቱን ለማብቃት አዲስ በር" ሊከፍት ይችላል ብለው ነበር።

እስራኤል መስከረም 26/2016 ዓ.ም. ሐማስ የፈጸመባትን ጥቃት ተከትሎ በከፈተችው ዘመቻ ጋዛ ውስጥ ካለቁት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ባሻገር በርካታ የቡድኑ ቁልፍ መሪዎችን በተለያዩ ቦታዎች ገድላለች።

ባለፈው ማክሰኞ ኳታር ዶሃ ውስጥ የተፈጸመው ያልተጠበቀ ግልጽ የአየር ጥቃትም የዚሁ አካል ሲሆን፣ ከቀደሙት ግን በእጅጉ የተለየ እና እስራኤል ላይ ከፍተኛ ውግዘትን ያስከተለ ነው።

ኻሊል አል ሃያ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የጥቃቱ ዋነኛ ዒላማ የሐማስ ዋና ተደራዳሪ ኻሊል አል ሃያ

በእስራኤል ዒላማ ውስጥ ያሉት የሐማስ መሪዎች

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በ2016 ዓ.ም. ሐምሌ ወር በኢራን ፕሬዝዳንት ሲመተ በዓል ላይ ተገኝተው የነበሩት የሐማስ ፖለቲካዊ መሪ ኢስማኤል ሃኒዬ አርፈውበት በነበረበት ክፍል ውስጥ በፍንዳታ መገደላቸው ይታወሳል። ግድያው በእስራኤል የተፈጸመ መሆኑን ብዙዎች ቢናገሩም እስራኤል ግን የሰጠችው ማረጋገጫ የለም።

ሐማስ በአስራኤል ላይ የፈጸመው ከባድ ጥቃት አስተባባሪ እና መሪ እንደሆነ የሚታመነው ኢስማኤል ሃንዬን የተካው ያህያ ሲንዋርም ከጥቂት ወራት በኋላ ጋዛ ውስጥ ተገድሏል።

ከጋዛ ውጪ ቁልፍ የሐማስ አመራሮች የሚገኙት ኳታር ውስጥ ሲሆን፣ ከእስራኤል ጋር የሚደረገውን ድርድርንም የሚመሩት እነዚሁ የቡድኑ መሪዎች ናቸው።

ሁለት ዓመት ሊሞላው የተቃረበውን የጋዛ ጦርነት ለማስቆም የመጨረሻ የተባለው የስምምነት ሃሳብ በፕሬዝዳንት ትራምፕ ከቀረበ በኋላ ፍሬ አፍርቶ ታጋቾች የሚለቀቁበት፣ በመከራ ውስጥ የሚገኙት የጋዛ ነዋሪዎች እፎይታ እና እርዳታ የሚያገኙበት ዕድል ሊፈጠር ይችላል ተብሎ ሲጠበቅ እስራኤል ኳታር ውስጥ ���ፈጸመችው ጥቃት ምናልባትም ለጊዜው አጨነገፈው።

እስራኤልም፣ ሐማስም እንዳሉት ጥቃቱ በዶሃ የሚገኙትን የሐማስ ከፍተኛ አመራሮች እና ተደራዳሪዎች ለመግደል የታለመ ነበር። እስራኤል ጥቃቱ ስላለስገኘው ውጤት ያለችው ነገር ባይኖርም፤ ሐማስ ግን አመራሮቹ ከእስራኤል የሞት ወጥመድ አምልጠዋል ሲል አስታውቋል።

አሁን ዋናው ጥያቄ በገቡበት እና በወጡበት በእስራኤል የሞት ጥላ ውስጥ የሚገኙት የሐማስ መሪዎች ድርድሩን እርግፍ አድርገው ይተዉታል? ወይስ በእስራኤል እየታዳኑም ቢሆን በደርድሩ ይቀጥላሉ? የሚለው ነው።

እስራኤል ግን ለተፈጸመባት ጥቃት ተጠያቂ ናቸው ያለቻቸውን የሐማስ መሪዎች ከያሉበት እያደነች እንደምትቀጣቸው በግልጽ እና በተደጋጋሚ እየገለጸች መሆኑ ጥቃቱ ቀጣይ መሆኑን ያመለክታል።