'ዝምተኛው ገዳይ' በኢትዮጵያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኤላ አዶ-ኪሲ-ዴብራህ በዘጠኝ ዓመቷ ነው የሞተችው።
የሞተችው በአስም ምክንያት ነው። በዓለም ለመጀመሪያ ጊዜ በአየር ብክለት መሞቷ የተረጋገጠ ታዳጊ ናት ኤላ።
እአአ በ2013 ነበር ሕይወቷ ያለፈው። በደቡብ ምሥራቅ ለንደን ትኖር የነበረችው ታዳጊ ከመሞቷ በፊት 27 ጊዜ የሆስፒታል አልጋ ይዛለች።
እናቷ ራዛሙንድ ልጇ ከሞተችበት ጊዜ አንስቶ ንጹህ አየር ማግኘት ሰብአዊ መብት ነው በሚል በመላው ዓለም ትግል በማድረግ ትታወቃለች።
ላለፉት 10 ዓመታት ባደረገችው ንቅናቄ አማካይነት በለንደን የካርበን ልቀት አነስተኛ የሚሆንባቸው አካባቢዎች ተከልለዋል፤ ተሽከርካሪዎች የሚጓዙበት ፍጥነት ተገድቧል፤ የኤሌክትሪክ መኪና ቻርጅ ማድረጊያ ቦታዎች ተስፋፍተዋል፤ ንጹህ አየር የማግኘት መብት ሕግም ወጥቷል።
ይህ ሕግ በሟቿ ታዳጊ ስም 'ኤላስ ሎው' ተብሏል።
የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚለው፣ 99 በመቶው የዓለም ሕዝብ የሚተነፍሰው አየር ተበክሏል። ታዳጊ አገሮች ደግሞ የበለጠ ተጎጂ ናቸው።
በየዓመቱ ከ4 ሚሊዮን እስከ 7 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች በአየር ብክለት እንደሚሞቱ የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያሳያል።
የዓለም ጤና ድርጅት የኢትዮጵያ የአየር ብክለት ልኬት ከፍተኛ መሆኑን ያሳያል። ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው የቤት ውስጥ የአየር ብክለት ነው።
የአየር ብክለት 'ዝምተኛ ገዳይ' የሚባለው የሚያስከትለው ጉዳት በግልጽና በቶሎ ስለማይታይ እንደሆነ ተመራማሪው ፕ/ር ሰለሞን ቢልልኝ ይናገራሉ።
ላለፉት 35 ዓመታት በዩኒቨርስቲ ኦፍ ዩታ እና በኖርዝ ካሮላይና አግሪካልቸራል ኤንድ ቴክኒካል ስቴት ዩኒቨርስቲ ሲያስተምሩና ሲመራመሩ ቆይተዋል።
በፊዚክስ እንዲሁም በአፕላይድ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ትምህርት ክፍል ፕሮፌሰር ናቸው።
ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች የሚዳርገው የአየር ብክለት በኢትዮጵያ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ፕ/ር ሰለሞን ሙያቸው አቶሚክ ሞሎኪውላር ኤንድ ኦፕቲካል ፊዚክስ እና ኬሚካል ፊዚክስ ነው።
ብዙ ጊዜ ወደ አዲስ አበባ ሲመላለሱ፣ ከአውሮፕላን ማረፊያው ከወጡ በኋላ "ዓይን የሚቆጠቁጥ" የአየር ብክለት ማስተዋላቸውን ይናገራሉ።
ጥናታቸውን ወደ አትሞስፌሪክ ኬሚስትሪ ያዞሩትም ለዚህ ነው። ለአቶሚክ ፊዚክስ የሚጠቀሙባቸውን መሣሪያዎች ተጠቅመው ምርምራቸውን ቀጠሉ።
ወደ አየር የሚለቀቁ የተለያዩ በካዮችንና ኬሚካሎችን አጥንተዋል።
በኢትዮጵያ ዋነኛ አየር በካዮች የትኞቹ ናቸው?
የአየር ብክለት 'ዝምተኛ ገዳይ' የሚባለው ያለ ምክንያት አይደለም።
ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዘው የሚከሰቱት እንደ መሬት መንቀጥቀጥ፣ ጎርፍ፣ አውሎ ንፋስ፣ የመሬት መንሸራተት እና ሰደድ እሳት ያሉት ተፈጥሯዊ አደጋዎች ብዙ ይነገርላቸዋል።
የአየር ብክለት ግን ከእነዚህ ሁሉ ይለያል።
"በአንድ ጊዜ ብዙ ሰው ጨርሶ ዜና አይሆንም። ጉዳቱ ጊዜ ይወስዳል። ለዜና ግብዓት ቶሎ አለመብቃቱ 'ማራኪ ጉዳይ አይደለም' አስብሎታል" ሲሉ ፕ/ር ሰለሞን ያስረዳሉ።
እአአ በ2019 በመላው አፍሪካ በአየር ብክለት 1.1 ሚሊዮን ሰዎች ሞተዋል። በ2021 ከደም ግፊት ቀጥሎ ሁለተኛው ገዳይ ተብሏል።
በአየር ብክለት ምክንያት በ2021 በዓለም 1.8 ሚሊዮን ሰዎች ሞተዋል። ከ709 ሺህ በላይ የሚሆኑት ከአምስት ዓመት በታች ያሉ ሕጻናት ናቸው።
በጣም አስከፊው በካይ ጭስ ነው።
ፕ/ር ሰለሞን እንደሚሉት፣ እንጨት ሲቃጠል ብላክ ካርበን የተባሉ እጅግ ጥቃቅን ቅንጣቶች አየር ላይ ይበትናል።
ፕላስቲክና ኤሌክትሮኒክስ የያዘ ቆሻሻ ሲቃጠል 'ዳዮክሲንስ' የሚባል ካንሰር የሚያስከትል ኬሚካል ይረጫል። ይህም የጉበት ሕመም ያስከትላል። የሰውነትን በሽታ የመከላከል አቅም ያዳክማል።
ሌላው በካይ የመኪና ጭስ፣ ���ላክ ካርበን ወደ አየር ይለቃል። መኪና በካይ ጭስ እንዳይለቅ የሚያደርገው ካታሊቲክ ኮንቨርተር የሌላቸው መኪኖች ከፍተኛ መጠን ያለው ጭስ ነው የሚያወጡት።
እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገራት መኪኖች ላይ የሚደረገው ቁጥጥር ጥብቅ ስላልሆነ የብክለት መጠኑም ከፍተኛ ነው።
ፕ/ር ሰለሞን "ብዙም ሰዎች የማያስተውሏቸው" የሚሏቸው ባሕር ዛፍ፣ ግራር እና ዘንባባ ባዮጀኒክ ቮላታይል ኦርጋኒክ ኮምፓውንድ የሚባሉ ኬሚካሎችን ይረጫሉ።
"እነዚህ ከመኪና ጭስና ከፋብሪካ ጭስ ጋር ሲገናኙ በፀሐይ ብርሃን አማካይነት ፎቶኬምስትሪ ይካሄዳል። ብክል አየር (ስሞግ) የሚፈጠረውም በዚህ ነው" ይላሉ።
ጠዋት ላይ በርቀት የምናየው ነገር ሁሉ በጭስ የሚታፈነው በበካዮች ምክንያት ነው።
"እነዚህን ጥቃቅን ፓርቲክሎች ተንፍሰናቸው፣ በሳምባችን ጥቃቅን የደም ሥሮች ውስጥ ገብተው ወደ ጭንቅላት ይሄዳሉ። ስትሮክ ሊያስከትሉም ይችላሉ" ይላሉ ባለሙያው።
የአየር ብክለት ተላላፊ ያልሆኑ ሕመሞች እንደሚያስከትል ጥናቶች አሳይተዋል።
የልብ ሕመም፣ የሳምባ ምች (ኒሞኒያ)፣ ፓርኪንሰንስ፣ አልዛይመርስ፣ ዩቲአይ፣ ብሬን ኢንፍላሜሽን፣ ጭንቀት፣ ድባቴ፣ አስም፣ የጽንስ መጨንገፍ፣ የወሊድ ምጣኔ መቀነስ (ሬድዩስድ ፈርቲሊቲ)፣ የጨቅላዎች ቀጭጮ መወለድ (ሎው በርዝ ዌት) እና ሌሎችም ሕመሞችን ፕ/ር ሰለሞን ይጠቅሳሉ።
"እነዚህ በሽታዎች በአንድ ጊዜ ሰውን አይገድሉም። ከጊዜ ብዛት ዕድሜያችንን ሊያሳጥሩ ይችላሉ። አንዳንዴም ለከፋ አደጋ ያጋልጣሉ" ይላሉ።
የአየር ብክለት ከዕድሜያችን ላይ 1.8 ዓመት እየቀነሰ እንደሆነ ይታመናል።
'ኅዳር ሲታጠን' ይበክላል?
ከግማሽ በላይ የዓለም ቆሻሻ የሚወገደው ተቃጥሎ ነው።
በኢትዮጵያም 'ኅዳር ሲታጠን' ከተባለው አገር አቀፍ የቆሻሻ ማቃጠል ባህል አንስቶ በየከተማው ቆሻሻን ማቃጠል የተመለደ ነው።
ቆሻሻ በማቃጠል ወደ ከባቢ አየር ከሚለቀቁ አደገኛ ኬሚካሎች መካከል ዳዮክሲንስ እና ፉራንስ ይጠቀሳሉ።
በዓይናችን ባናያቸውም አየር ላይ ይሄዳሉ።
ቆሻሻ በዘላቂነት የሚሰበሰብበት አማራጭ መፈጠር እንዳለበት ባለሙያው የሚመክሩትም ለዚህ ነው።
'ኅዳር ሲታጠን' እንደ አንድ ቀን ባህል ገናና ቢሆንም፣ በየከተሞቹ ያለው ቆሻሻ የማቃጠል ልማድ "የሚመጣውን መዘዝ ማሳወቅ አለብን" ይላሉ።

የፎቶው ባለመብት, Solomon Bililign
በሌላ በኩል ደግሞ በድህነትና በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ውስንነት ምክንያት በርካቶች በማገዶ እንጨት ያበስላሉ።
ወደ ከተሞች ስንመጣ፣ ዘለግ ላለ ጊዜ አገልግለው ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ መኪኖች ለተጨማሪ ረዥም ዓመታት ይነዳሉ።
በአንዴ ያረጁ መኪኖች ባጠቃላይ ይታገዱ ቢባል የበርካቶች ኑሮ ይመሳቀላል። ስለዚህም ቀስ በቀስ አዲስ መኪና እንዲገባ ድጎማ ወይም ማበረታቻ መስጠትን ባለሙያው ይመክራሉ።
የአየር ብክለት በጤና እና በምጣኔ ሃብት ላይ እያደረሰ ያለው ጉዳት እየተባባሰ መሄዱን ጥናቶች ያሳያሉ።

የፎቶው ባለመብት, Solomon Bililign
እአአ በ2019 በአየር ብክለት ምክንያት በደረሰው ሞትና ሕመም ምክንያት በአገሪቱ ምጣኔ ሃብት ላይ የደረሰው ጉዳት በ3.02 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ነው (ይህም ከአገሪቱ ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት 1.16% ይሸፍናል)።
ዩኤንዲፒ ከጤና ሚኒስትር ጋር በ2024 በሠራው የዳሰሳ ጥናት መሠረት፣ በቤት ውስጥ የአየር ብክለት ምክንያት በየዓመቱ 39ሺህ ሰዎች ይሞታሉ። 281 ትሪሊዮን ብር ኪሳራም ይደርሳል።
የኢትዮጵያ የአየር ብክለት የዓለም ጤና ድርጅት ካስቀመጠው ጣሪያ አምስት እጥፍ የበለጠ ነው።
ፕ/ር ሰለሞን እንደሚሉት፣ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ አገሮች የኢንዱስትሪ ቁጥጥር ይደረግ ቢባል በቀላሉ ተቀባይነት አይኖረውም። ባለሃብቶችም ቁጥጥር የሌለው ቦታ ሄደው ፋብሪካቸውን ይከፍታሉ።
ለምሳሌ፣ አሜሪካ የነበሩ ፋብሪካዎች የአየር ብክለትን ለመቀነስ የቁጥጥር እርምጃ ሲወሰድ ወደ ቻይና ሄደዋል። በቻይና ቁጥጥር ሲጀመር ደግሞ ወደ አፍሪካ እየመጡ ነው።
የሥራ ዕድል መፍጠርና የምጣኔ ሃብት ዕድገት ምን ዋጋ እያስከፈለን ነው? የሚለው ሊታሰብበት እንደሚገባ ባለሙያው ይገልጻሉ።
"በአንድ ጊዜ ፋብሪካዎች ሁሉ አይዘጉም። የምጣኔ ሃብት ቀውስ ያስከትላል። ሰው ሥራ እስካገኘ ድረስ የመጣው ይምጣ ማለትም በረዥም ጊዜ የጤና መዘዝ ያስከትላል። ነገሩ አንድ መልስ የለውም። በመካከል ያለውን አማካይ መንገድ መከተል ያስፈልጋል።"

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአየር ብክለትና የአየር ንብረት ለውጥ
በካዮች (ፖሉተንትስ) ግሪን ሀውስ ጋዝ ናቸው። ለአየር ንብረት ለውጥ ይዳርጋሉ።
ካርቦን ዳይኦክሳይድ፣ ካርቦን ሞኖኦክሳይድ፣ ናይትሮጅን ዳይኦክሳይድ እና ሜቴን ከግሪን ሀውስ ጋዞች መካከል ይጠቀሳሉ።
ፕ/ር ሰለሞን እንደሚሉት፣ አየር በካዮችንና ግሪን ሀውስ ጋዝን መለየት አይቻልም። ምክንያቱም አንዳቸው ሌላቸውን ይደግፋሉ።
"እነዚህን በካዮች በማስወገድ አየር ንጹህ ሲሆን የአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭነትንም መቀነስ ይቻላል" ይላሉ።
የአየር ንብረት ለውጥና የአየር ብክለት ዑደት ወይም እሽክርክሪትን ለመረዳት አንድ ምሳሌ እንውሰድ።
የአየር ንብረት ለውጥ ድርቀት ያመጣል። ድርቀት ደግሞ ሰደድ እሳት ያስነሳል። ሰደድ እሳት አካባቢ በካይ ኤሮሶል ይለቃል። የሚለቀቀው ኬሚካል መልሶ የአየር ብክለት ያስከትላል።
የአየር ብክለት ግብርናን ይጎዳል፤ ከሥራ ያስተጓጉላል፤ የሕክምና ወጪን ይጨምራል።
ከኢንዱስትሪና ከከተማ መስፋፋት ጋር በተያያዘ የአየር ብክለት እየተባባሰ ነው።
በ2100 ከዓለም 20 ትልልቅ ከተሞች 13ቱ በአፍሪካ ይሆናሉ። አሁን ሁለቱ ብቻ በአፍሪካ ይገኛሉ።
"ካሁኑ ቁጥጥር ማድረግ ካልተቻለ፣ ከተሞች ሲሰፉ ብክለቱ አብሮ እየጨመረ የጤና እክሉም በዛው ልክ እየተባባሰ ይሄዳል" ይላሉ ፕ/ር ሰለሞን።
በመላው ዓለም በአየር ብክለት ምክንያት በዓመት ውስጥ ከሥራ በሚቀሩ ሰዎች ሰበብ 1.2 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ እንደሚደርስ ይገመታል።
ይሄንን በመረጃ አስደግፎ ለማ��ረብ "በታዳጊ አገሮች የአቅም ውስንነት አለ" ሲሉ ችግሩን ባለሙያው ያስረዳሉ።

የፎቶው ባለመብት, Solomon Bililign
በኢትዮጵያ ያለው የግንዛቤ ክፍተት፣ የባለሙያዎች ውስንነት፣ ለጥናት የሚውል በጀት ማነስና የአካባቢ ጥበቃ ሕጎች አለመተግበርም ችግሩን ያባብሳሉ።
በጎረቤት አገራት የተሻሉ የቅድመ ጥንቃቄ እርምጃዎች እንደሚተገበሩ ፕ/ር ሰለሞን ይጠቅሳሉ።
በኬንያ ተንቀሳቃሽ የአየር ብክለት መቆጣጠሪያ መሣሪያ ጥቅም ላይ ይውላል።
በኡጋንዳ፣ ካምፓላ በአነስተኛ ዋጋ የንጹህ አየር መቆጣጠሪያ መሣሪያ በማካራሬ ዩኒቨርስቲ ተሠርቷል።
የሩዋንዳ መዲና ኪጋሊም የአየር ብክለትን ለመቀነስ ንቅናቄ በማድረግ ትታወቃለች።
"ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ ግን፣ ምን ያህል ኤሮሶል በአየሩ ላይ አለ የሚለውን የሚቆጣጠር መሣሪያ ቢኖርም የኬሚካሎቹ መነሻ ምን እንደሆነ ካልታወቀ እርምጃ ለመውሰድ ቀላል አይደለም። ለከባቢ አየር ጥበቃ ተቋማት ጠንካራ የሳይንስ ድጋፍ ያስፈልጋል።"

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
'ሁላችንም አንድ ዓይነት አየር ነው የምንተነፍሰው'
የአፍሪካው ብክለት አውሮፓ፣ የአውሮፓው ብክለት እስያ፣ የእስያው ብክለት አፍሪካ ይደርሳል።
ቆሻሻ በሚቃጠልባቸው ቦታዎች በሙሉ አዲስ አበባም ይሁን ደሴ ወይም አርባ ምንጭ ያለው ብክለትም ተመሳሳይ ነው።
በአዲስ አበባና በአብዛኞቹ የአፍሪካ ከተሞች ያለው የአየር ብክለት የዓለም ጤና ድርጅት ጤናማ ከሚለው አምስት እጅ ስለሚበልጥ በብዛት የአደገኛ ምልክት የሆኑት ቀይና ሮዝ ቀለም ይሰጣቸዋል።
በተለይ ጠዋት የትራፊክ መጨናነቅ ሲኖር ብክለቱ የበለጠ ጎልቶ ይታያል።

የፎቶው ባለመብት, Solomon Bililign
"እጅግ የተበከለ አየር ነው እየተነፈስን ያለነው። ሰው ሲረፈረፍ ስለማይታየን ነው ከዜናው የተደበቀው። በከተማ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ባጠቃላይ ለተበከለ አየር ተጋልጠዋል። ከቤት እስከ ሥራ ቦታ ሲሄዱ በሚተነፈሰው አየር ማወቅ ይቻላል" ይላሉ ፕ/ር ሰለሞን።
ሰዎች አኗኗራቸውን ከማሻሻል አልፈው እንደ ማኅበረሰብ የጋራ ለውጥ እንዲያመጡ ባለሙያው ያሳስባሉ።
ከቤት ውስጥ አንስቶ እስከ አገር አቀፍ ደረጃ የአየር ብክለትን ለመከላከል ባለሙያው ቀጣዮቹን ምክሮች ይሰጣሉ።
- ከሰል አደገኛውን ካርቦን ሞኖኦክሳይድ ኬሚካል ያመነጫል። ብዙ በእንጨትና በከሰል ምግብ በሚበስልባቸው ቦታዎች የበለጠ ብክለት ስላለ በተለይ በታፈነ ቤት ከሰል አለማቀጣጠል።
- በክፍት ቦታ የሚቃጠል ነገር ሲኖር ከቤት በማስወጣት የበካይ ቅንጣቶችን ክምችት መቀነስ ይቻላል።
- በተለይም ፕላስቲክና ኤሌክትሮኒክስ ያለበት ቆሻሻ መቃጠል ያለበት ከከተማ ውጪ ሲሆን፣ የቆሻሻ አወጋገድ ባጠቃላይ ሊስተካከል ይገባል።
- ከፍተኛ ብክለት ባለበት ቦታ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል መጠቀም ይመከራል።
- ሰዎች የሚተፍሱት አየር ውስጥ ያለውን የብክለት መጠን መቆጣጠር የሚችሉበት መሣሪያ መጠቀም።
- የአየር ብክለትን ለመከላከል የሚወጡ መርሆች አተገባበርን ማረጋገጥ ያስፈልጋል።
- ተቆጣጣሪ ሕግ ከማውጣት ባሻገር በአገር በቀል ባለሙያዎች ጥናቶች ተሠርተው ውጤታቸው መተግበር አለበት።
- የአየር ብክለት የከፋ የጤና እክል እንደሚያስከትል ለማኅበረሰቡ ማስገንዘብና የትኛው ጉዳይ ቅድሚያ ተሰጥቶት ገንዘብ ይፍሰስበት ሲባል የአየር ብክለትን ማስቀደም ያሻል።












