መቀለ ውስጥ ምንድን ነው የተከሰተው? ከበባ፣ ውይይት፣ የድምጺ ወያነ ሥርጭት መቋረጥ፣ ፍንዳታ...

የታጠቁ የትግራይ ኃይል አባላት "ደመወዝ ዘገየብን" በሚል ቅሬታ መቀለ የሚገኘው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ሕንጻ ላይ ከበባ መፈጸማቸውን እና ደምጺ ወያነ ቴሌቪዥን ጣቢያን ተቆጣጥረው እንደነበረ ተገለጸ።
ታጣቂዎቹ በዋናነት ትኩረታቸውን ያደረጉት የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳዳሪ ሌ/ጄነራል ታደሰ ወረደ ጽህፈት ቤት በሚገኝበት የትግራይ ክልል መስተዳደር ሕንጻ ላይ መሆኑን የቢቢሲ ትግርኛ ሪፖርተር ገልጿል።
መቀለ ውስጥ እንቅስቃሴ ያደረገው የትግራይ ኃይል አርሚ 31 የተባለው ክፍል ከ70 በላይ የሚሆኑ አባላት ናቸው።
እነዚህ ታጣቂዎች ረቡዕ ኅዳር 24/2018 ዓ.ም. ምሽት አራጉር (እንደርታ) ከተባለ ቦታ ተነስተው ነው ሐሙስ ዕለት በአስተዳደሩ ሕንጻ ላይ ከበባ የፈጸሙት።
የሠራዊት አባላቱ የነፍስ ወከፍ መሣሪያ የሆነውን ክላሽንኮቭ ጨምሮ ዲሽቃ የተባለውን የቡድን መሣሪያ የታጠቁ መሆናቸውን የዐይን እማኞች ተናግረዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአርሚ 31 የቅርብ አዛዦች ክስተቱን ለማርገብ ሊያናግሯቸው ቢሞክሩም "ከፍተኛ ባለሥልጣናት መጥተው ያናግሩን" በሚል ሳይቀበሏቸው መቅረታቸው ተገልጿል።
እኩለ ቀን ላይ የክልሉ ምክትል ጊዜያዊ አስተዳደር የሆኑት አቶ አማኑኤል አሰፋ እና የሰላም አና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊው ሌ/ጄነራል ፍሰሐ ኪዳኑ ከታጣቂዎቹ ጋር ውይይት ማድረጋቸው የተነገረ ቢሆንም ንግግሩ በምን ውጤት እንደተጠናቀቀ የተገለጸ ነገር የለም።
የቢቢሲ የመቀለ ዘጋቢ እንዳመለከተው ከሰዓት በኋላ ዘግይተው ወደ ከተማዋ የደረሱ ሌሎች የትግራይ ኃይሎች አባላት ወደ ድምጺ ወያነ ቴሌቪዠን ጣቢያ መሥሪያ ቤትን ተቆጣጠረው ሠራተኞቹ ሕንጻውን ለቅቀው እንዲወጡ አድርገው እንደነበር ተገልጿል።
በዚህም ምክንያት ጣቢያው ለሁለት ሰዓታት ያህል ሥርጭቱ ተቋረጦ ቆየቶ አመሻሽ ላይ ወደ አየር መመለሱን የቢቢሲ ዘጋቢ አረጋግጧል።
በተጨማሪም ከሰዓት በኋላ የሰማዕታት ሐውልት በሚገኝበት ጊቢ ውስጥ ከፍተኛ ፍንዳታ መሰማቱን እና ቢቢሲ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ባለሥልጣናትን ቢጠይቅም "እየተጣራ መሆኑን" ከመግለጽ ውጪ ዝርዝር መረጃ ማግኘት አልቻለም።
ታጣቂዎቹ እኩለ ቀን ላይ ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ባለሥልጣናት ጋር ካደረጉት ውይይት በተጨማሪ ሐሙስ አመሻሽ ላይ ሌላ ዙር ንግግር እየተደረገ አንደሆነ የቢቢሲ ዘጋቢ ተረድቷል።
ነገር ግን በውይይቱ ውስጥ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳር ፕሬዝዳንት ሌ/ጄነራል ታደረሰ ወረደ ስለመኖራቸው የታወቀ ነገር የለም።
የታጣቂዎቹ እንቅስቃሴ ከትናንት ጀምሮ የታየ መሆኑን ነዋሪዎች ያመለከቱ ሲሆን በዚህም ሳቢያ በመቀለ ነዋሪዎች ዘንድ ስጋት ተፈጥሯል።
የትግራይ ኃይል አባላቱ በወር የሚያገኙት ደሞዝ እንዲሻሻል እና ሌሎችም ጥቅማጥቅሞችን በተደጋጋሚ ሲጠይቁ ቆይተዋል። ለአሁኑ እንቅስቃሴ ምክንያቱ በክልሉ ያጋጠመው የደሞዝ ከፍያ መዘግየት ሊሆን አንደሚችል እየተነገረ ነወ።
የአርሚ 31 ታጣቂዎች በክልሉ መስተዳደር ሕንጻ እና በተንቀሳቀሱባቸው አካባቢዎቸ የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ተስተጓጉሎ እንደነበር ነዋሪዎች ገልጸዋል።
እንዲህ ያለው የሠራዊት አባላት እንቅስቃሴ በተደጋጋሚ መከሰቱ በነዋሪዎች ላይ ስጋት መፍጠሩን የጠቀሰው የቢቢሲ ዘጋቢ፣ በዚህም ሳቢያ ግጭት ይከሰታል በሚል ከባንኮች ገንዘብ ማውጣት፣ ከገበያዎች መሠረታዊ ፍጆታዎችን መሸመት አንዲሁም አንዳንዶች ደግሞ ወደ አዲስ አበባ ሲሄዱ በተደጋጋሚ ይታያል።
እንዲህ ያለው የትግራይ ኃይል አባላት ተቃውሞ እና ጥያቄ ለመጀመሪያ ጊዜ የተከሰተ ሳይሆን ከዚህ ቀደምም የክልሉ ዋና ከተማ መቀለን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች አጋጥሞ እንደነበር ተዘገግቧል።
በተለይ ባለፈው ጥቅምት ወር መጀመሪያ ላይ በትግራይ ኃይሎች ውስጥ ያሉ የአርሚ 22 አባላት ወደ መቀለ ጎዳናዎች ወጥተው ቅሬታቸውን እና ጥያቄያቸውን አሰምተው ነበር።
የሠራዊቱ አባላት በተመሳሳይ ወደ ክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ሕንጻ ሄደው የነበረ ሲሆን፣ የተለያዩ መንገዶችም በዚህ ሳቢያ ተዘግተው የነዋሪዎች እንቅስቃሴ ተስተጓጉሎ እንደነበር ይታወሳል።
ከዚህ ቀደም በታጣቂዎቹ የቀረቡትን ጥያቄዎችን ተከትሎ የክልሉ መስተዳደር ለደሞዝ እና ለጥቅማጥቅም ጉዳዮች ምላሸ የሚሰጥ ውሳኔ አሳልፎ ነበር።















