መጥፎ ጓደኛ ላለመሆን የሚረዱ አምስት ቀላል መንገዶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
እንዲኖረን የምንፈልገው ዓይነት ጓደኛ ለመሆን ማሻሻል ያለብን ባህሪዎች የትኞቹ ናቸው? እንዴትስ በጎ ጓደኛ መሆን ይቻላል?
እነዚህ የብዙዎች ጥያቄ ናቸው።
ሰዎች ትዕቢተኛ በመሆናቸው ወይም ችላ ባይ በመሆናቸው ልንበሳጭባቸው እንችላለን። የራሳችን ድክመቶችም ይታወቁናል።
አንዳንዴ ሳይታወቀን ሰዎችን ልንጎዳ እንችላለን። በምናደርገው ወይም በምንናገረው ነገር ሰዎችን እናስቀይማለን።
ታዲያ እንዴት የተሻልን ሰዎች መሆን ይቻላል?
የማኅበራዊ ትስስር ጥናት ውስጥ ካሉ ሐሳቦች አንዱ ሁለት ተቃራኒ ማንነት ያላቸውን ሰዎች የማስተናገድ ጉዳይ ነው።
አንዳንዴ ተጫዋች አንዳንዴ ደግሞ ዝምተኛ የሚሆኑ ሰዎች ምሳሌ ይሆናሉ።
አንደኛው ጥሩ ጓደኛ መሆን የሚቻልበት መንገድ ተቃራኒ ማንነትን ማስወገድ ነው። ቋሚ መሆንን ጨምሮ በጎ ወዳጅ መሆን የሚቻልባቸውን መንገዶች እንመልከት።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቋሚ መሆን
እርግጠኛ ያለመሆን ስሜትን ማንም አይወደውም።
በዩናይትድ ኪንግደም የሚገኘው ዩሲኤል የኒውሮሎጂ ተቋም ውስጥ የሚሠራው አርቺ ደ ቤከር አንድ ጥናት አድርጓል።
ሰዎች ሰብስቦ ጌም እንዲጫወቱ ጠየቀ። በጨዋታው ላይ ሰዎቹ እባብ ከአለት ሥር ሲመለከቱ የኤሌክትሪክ ንዝረት እንዲሰማቸው ይደረጋል።
ሰዎቹ በቀጣይ አለት ሲመለከቱ ከሥሩ እባብ ሊኖር ይችላል? የኤሌክትሪክ ንዝረትስ ይሰማኛል? ብለው ጭንቅ ያዛቸው።
የሥነ ልቦናዊ ጭንቀት አካላዊ ምልክት የሆኑ እንደ ማላብ ያሉ ምልክቶች ይታዩባቸውም ጀመር።
የኤሌክትሪክ ንዝረት እንደሚገጥማቸው በሚያውቁበት ሁኔታ ውስጥ ካላቸው ጭንቀት ይልቅ የኤሌክትሪክ ንዝረት ሊገጥማቸው ላይገጥማቸውም በሚችልበት ወይም 50 በመቶ ዕድል ባለበት ሁኔታ ውስጥ የበለጠ ተጨንቀው ታይተዋል።
ለምን? ቢባል ምን እንደሚገጥማቸው እርግጠኛ ስላልሆኑ።
��ን ዓይነት ጓደኝነት እንደሚጠብቀን አለማወቅም ተመሳሳይ ውዝግብ ውስጥ ይከታል።
ጓደኞች በሕይወታችን ያላቸውን ሚና ለመረዳት ከሚጠየቁ ጥያቄዎች መካከል ችግር ሲገጥመን ምን ያህል ይረዱናል? የሚለው አንዱ ነው።
ጓደኞቻቸው በሕይወታቸው ያላቸው ዋጋ ግልጽ የሆነላቸው ሰዎች ስለ ጓደኞቻቸው እርግጠኛ ካልሆኑ ሰዎች አንጻር እምብዛም አይጨነቁም።
ለጓደኞቻችን መጥፎ ባህሪ ባለማሳየት ምቾት እንዲሰማቸው ማድረግ ይቻላል።
ግልጽነት
ሰዎች ምን ያህል ስሜታችንን ይረዱታል ብለን እናስባለን?
ምን እያሰብን እንደሆነ ሰዎች የሚገነዘቡበትን መጠን አጋነን ልናስብ እንችላለን።
ይህም በእንግሊዘኛው ‘the illusion of transparency’ ይባላል።
ስለ ሰዎች የሚሰማንን ጥሩ ስሜት ሳንገልጽ ስንቀር ቅሬታ ይፈጠራል።
በኦስቲን በሚገኘው ዩኒቨርስቲ ኦፍ ቴክሳስ የሚሠራው አሚት ኩመር እና በቺካጎ በሚገኘው ዩኒቨርስቲ ኦፍ ቺካጎ የሚሠራው ኒኮላስ ኤልፒ በሠሩት ጥናት፣ ሰዎች ምን ያህል ጥሩ እንደሆኑ ሲነገራቸው ጥሩ ስሜት ይሰማቸዋል።
ስለ አንድ ሰው ያለንን አወንታዊ አመለካከት ባንነግራቸውም ያውቁታል ብሎ ማሰብ ስህተት ነው።
በእርግጥ በቃላት ስሜታችንን ባንገልጽም በድርጊት ልናስረዳቸው እንችል ይሆናል።

የፎቶው ባለመብት, Javier Hirschfeld/ Getty Images/ BBC
ለሰዎች ስሜት ዕውቅና መስጠት
ሰዎች ከባድ ሁኔታ ውስጥ ሲያልፉ ዕውቅና ማግኘት ይሻሉ።
ስሜታቸው ዕውቅና እንዲሰጠውና በገጠማቸው ነገር ወዳጆቻቸው የተሰማቸውን ሐዘን እንዲገልጹላቸው ይፈልጋሉ።
ክፉ ጓደኛ ለስሜት ዕውቅና አይሰጥም። ስሜት ዕውቅና ካልተሰጠው ደግሞ የመገፋት ስሜት ያስከትላል።
ይህ ማለት ግን ለአንድ ሰው ሐዘኔታ ስለተሰማን ብቻ በሚሉት ነገር በአጠቃላይ መስማማት አለብን ማለት አይደለም።
ለስሜት ዕውቅና ከሰጡ በኋላ ከዚያ ሰው የተለየ ዕይታን ወይም ዕሳቤን መግለጽ ይቻላል።
ሰዎች የገጠማቸውን ችግር ከተለያየ አቅጣጫ እንዲመለከቱ ለማስቻል በቅድሚያ ለስሜታቸው ዕውቅና መስጠት ይኖርብናል።
አንድ ሰው የሚሰማውን ሐዘን ሲገልጽ ማድመጥ መልካም ቢሆንም ያለ ምንም እርዳታ ወይም አስተያየት ዝም ብሎ ማዳመጥ ብቻ አሉታዊ ጎን ሊኖረው እንደሚችል የሥነ ልቦና ባለሙያዎች ያስረዳሉ።
ገንቢ ንግግር ማድረግ ያለውን ጠቀሜታ የሚያስረዳው በዩኒቨርስቲ ኦፍ ሚችጋን የሚሠራው ኢተን ክሮስ የሠራው ጥናት ነው።
ሰዎች የገጠማቸውን ችግር ከተለያየ አቅጣጫ እንዲያዩ ማድረግ የሚቻልባቸውን ጥያቄዎች እንዲህ ይዘረዝራል፦
- ይሄ ነገር ለምን አስጨነቀሽ/አስጨነቀህ?
- ከዚህ ሁኔታ ምን ተማርሽ/ተማርክ?
- ትልቁን ምሥል መመልከት ስለ ገጠመሽ/ገጠመህ ነገር የተለየ ዕይታ ይሰጥሻል/ይሰጥሀል?
እነዚህ ጥያቄዎች የቀረቡላቸው ሰዎች በተሻለ ሁኔታ ስሜታቸውን ማብላላት እና ከገጠማቸው ፈተና መውጣት እንደቻሉ አጥኚው ገልጿል።
ስኬትን ማድነቅ
ጓደኛነት ሐዘንን መጋራት ብቻ አይደለም። ስኬትም የጋራ ደስታ መፍጠር አለበት።
ሻሊ ጌብል እና ሄንሪ ሬይስ እአአ በ2010 በሠሩት ጥናት መሠረት፣ በሕይወት አሉታዊ የሆኑ ነገሮች ከአወንታዊው በላቀ መነጋገሪያ ይሆናሉ።
አሁን አሁን ግን አወንታዊ ነገሮችን በጉልህ መናገር እየተለመደ መጥቷል።
ጤናማ ጓደኝነት ለመመሥረት በጎ ነገርን ማድነቅ አንድ መንገድ ነው።
በጎ ጓደኛ ስለ አንድ ጉዳይ ዝርዝር መረጃ ይጠይቃል፣ ደስታውንም ይገልጻል።
በጓደኞቻችን ስኬት የሚሰማንን ደስታ መግለጽ የበጎ ወዳጅነት ማሳያ ነው።
የሰዎች ስኬት ያለውን ዋጋ ማጣጣል ወዳጅነትን ያጠለሻል።
አንዳንዴ በሕይወት ሩጫ ምክንያት የጓደኞቻችንን ስኬት ችላ እንል ይሆናል። ጊዜ ወስዶ አድናቆትን መግለጽ ግን መረሳት የለበትም።
አንዳንዶች ትዕቢተኛ ላለመባል ስኬታቸውን እምብዛም አይናገሩም።
ስኬትን ከጓደኞች መደበቅ ግን ጤናማ እንዳልሆነ የሥነ ልቦና ባለሙያዎች ያስረዳሉ።
ዩኒቨርስቲ ኦፍ ቴክሳስ የምትሠራው አናቤል ሮበርትስ፣ በኮርኔል ዩኒቨርስቲ የምትሠራው ኦቩል ሴዝር እና በዩኒቨርስቲ ኦፍ ቺካጎ የምትሠራው ኤማ ሌቪን እንደሚሉት፣ የሥራ ዕድገትም ይሁን ማንኛውም ዓይነት ስኬት ለሰዎች መነገር አለበት።

የፎቶው ባለመብት, Javier Hirschfeld/ Getty Images/ BBC
ይቅርታ መጠየቅ
ሁሉም ሰው ቢሳሳትም ሁሉም ሰው ግን ይቅርታ አይጠይቅም።
ይቅርታ አመጠየቅ መቃቃር ያስከትላል። ማኅበራዊ ትስስርን ያላላል።
የሥነ ልቦና ባለሙያዎች እንደሚሉት፣ ሰዎች ይቅርታ የማይጠይቁባቸው አራት ምክንያቶች አሉ።
አንደኛው ያስከተሉትን ጉዳት አለመረዳት ነው። ሁለተኛው ይቅርታ መጠየቅን ማፈር ነው። ሦስተኛው ይቅርታ መጠየቅ ዋጋ የለውም ብሎ ማሰብ ሲሆን፣ አራተኛው ደግሞ እንዴት በጥሩ ሁኔታ ይቅርታ መጠየቅ እንደሚቻል አለማወቅ ነው።
ሰዎች ስህተታቸውን አውቀው ሲያርሙ ጥሩ ስሜት እንደሚሰማቸው ጥናቶች ይጠቁማሉ።
ይቅርታ በትክክለኛው መንገድ ከተጠየቀ፤ ልብም የተሰበረ ወዳጅነትም ይጠግናል።
ሰዎች የተሰማቸውን ሐዘን እንዲገልጹ ጊዜ መስጠት በተገቢው ሁኔታ ይቅርታ ለመጠየቅ ይረዳል።
እውነተኛ ፀፀት ማሳየት እና የተበላሸውን ጓደኝነት መጠገን ያለው ቦታ ያህል ስህተትን መልሶ አለመድገምም ትልቅ ዋጋ ይኖረዋል።
ሁሉም ሰዋዊ ግንኙነት ቀላል አይደለም። ውጣ ውረድም ይበዛዋል።
ጠንካራ ትስስር ከጓደኞቻችን ጋር ለመፍጠር ስህተትን ማስወገድ አንድ መንገድ ነው።
ሲጠቃለል፣ ራሳችንን እንዲኖረን የምንፈልገው ዓይነት ጓደኛ ማድረግ በሥነ ልቦና ባለሙያዎች ይመከራል።















