የታይታኒክ ተሳፋሪ የወርቅ ሰዓት በ1.78 ሚሊዮን ፓውንድ ተሸጠ

የኢሲዶር ስትራተስ የወርቅ ሰዓት

የፎቶው ባለመብት, BNPS

የምስሉ መግለጫ, የኢሲዶር ስትራተስ የወርቅ ሰዓት

ከታይታኒክ መርከብ ተጓዦች አንዱ የነበሩት ኢሲዶር ስትራተስ የወርቅ ሰዓት በ1.78 ሚሊዮን ፓውንድ ተሸጠ።

በዘመኑ የናጠጡ ሃብታም የነበሩት ኢሲዶር እና ባለቤታቸው ኢዳ እአአ በ1912 በመርከብ አደጋው ከሞቱት 1,500 ሰዎች መካከል ናቸው።

ሰዓታቸው በጨረታ የተሸጠበት ዋጋ ከዚህ ቀደም የተያዘውን ሪከርድ ሰብሯል።

አደጋው ከደረሰ ከቀናት በኋላ የኢሲዶር አስክሬን እና ባለ 18 ካራት የወርቅ ሰዓታቸው ተገኝቷል።

የጁልስ ጁርገንሰን ምርት የሆነው የወርቅ ሰዓት ለዓመታት በቤተሰቡ እጅ ቆይቷል። ባለፈው ሳምንት በሄነሪ አልድሪጅ ኤንድ ሰንስ ጨረታ ላይ ተሽጧል።

ትውልደ ባቫሪያ-አሜሪካዊው ነጋዴ እና ፖለቲከኛ፤ በኒው ዮርክ የሚገኘው ማሲስ መደብር ባለድርሻ ነበሩ።

ባለቤታቸው ኢዳ የነፍስ አድን ጀልባ ላይ እንድትሳፈር ብትጠየቅም ባለቤቷን ጥላ ለመሄድ አልፈቀደችም።

በታይታኒክ መርከብ ላይ ሳሉ የጻፈችው ደብዳቤ በጨረታ 100,000 ፓውንድ ተሸጧል።

የታይታኒክ ተጓዦች ዝርዝር በ104,000 ፓውንድ ሲሸጥ፤ ለመርከቡ ሠራተኞች የተሰጠ የወርቅ ሜዳልያ በ86,000 ፓውንድ ተሸጧል።

ከታይታኒክ ጋር በ��ያያዘ ለጨረታ የቀረቡ ቁሳቁሶች በአጠቃላይ 3 ሚሊዮን ፓውንድ አውጥተዋል።

የኢሲዶር ስትራተስ ሰዓት መቁጠር ያቆመው መርከቧ ከመስጠሟ በፊት 02:20 ላይ ነው።

ሰዓቱ ለኢዳ 43ኛ ዓመት ስጦታ እንደነበር ይታመናል። እአአ በ1888 በሰዓቱ ጀርባ ላይ የኢሲዶር ስም መነሻ ተጽፏል።

ሰዓቱ ለቤተሰቡ ከተመለሰ በኋላ ከትውልድ ትውልድ እየተሸጋገረ ለዓመታት ቆይቷል። የኢሲዶር የልጅ ልጅ ሰዓቱን አሳድሷል።

በዘመኑ የናጠጡ ሃብታም የነበሩት ኢሲዶር እና ባለቤታቸው ኢዳ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በዘመኑ የናጠጡ ሃብታም የነበሩት ኢሲዶር እና ባለቤታቸው ኢዳ

አጫራቹ አንድሪው አልድርጊ "ሰዓቱ የተሸጠበት ዋጋ በዓለም ከፍተኛው ነው። አሁንም ድረስ ሰዎች ስለ ታይታኒክ ማወቅ እንደሚሹ ያሳያል" ብሏል።

"ሁሉም ተሳፋሪ ታሪክ ነበረው። 133 ዓመታት አልፎም ታሪካቸውን ለማወቅ እንጓጓለን" ሲልም አክሏል።

የኢሲዶር እና ኢዳ ታሪክ "ድንቅ የፍቅር ታሪክ" ነው ሲል የገለጸው አንድሪው "ኢዳ የ41 ዓመት ባለቤቷን ጥላ ሕይወቷን ለማዳን አልመረጠችም። ሰዓቱ በከፍተኛ ዋጋ መሸጡ ለትስስራቸው ምስክር ነው" በማለትም ተናግሯል።

700 የሚደርሱ የመርከቡ ተሳፋሪዎችን ላዳነው የካርፓቲያ መርከብ ካፕቴን የተሰጠው የወርቅ ሰዓት በ1.56 ሚሊዮን ፓውንድ መሸጡ ይታወሳል።