ፎጣዎቻችን ለ���ለያዩ በሽታዎች ሊያጋልጡን እንደሚችሉ ያውቃሉ? እንዴት ንጽህናቸውን እንጠብቅ?

መታጠቢያ ቤት የተሰቀለ ፎጣ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሰውነታችንን አሊያም እጃችንን ከታጠበን በኋላ የምናደርቅባቸው ፎጣዎች ብዙ ጠቀሜታ ቢሰጡም እግረ መንገዳቸውን ረቂቅ ተህዋስያንን ከሰውነታችን ላይ ያነሳሉ።

ለመሆኑ እነዚህን ፎጣዎች ሳያጥቡ ለምን ያህል ጊዜ ይገለገሉባቸዋል? በምን ያህል ጊዜስ መታጠብ ይኖርባቸዋል?

አብዛኞቻችን እነዚህን ፎጣዎች የምናጥበው ቢያንስ በሳምንት አንድ ቀን ነው።

አንድ ጥናት እንዳመለከተው ግን በጥናቱ ከተሳተፉት 100 ሰዎች አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት ፎጣዎቻቸውን በወር አንድ ጊዜ ነው የሚያጥቡት።

በዩናይትድ ኪንግደም በተሠራ አንድ የዳሰሳ ጥናት ደግሞ ጥቂት ሰዎች የሚገለገሉባቸውን ፎጣዎች በዓመት አንድ ጊዜ እንደሚያጥቡ አምነዋል።

እነዚህ ለስላሳ ፎጣዎች መቆሸሻቸውን ላያሳብቁ ይችላሉ። ሆኖም በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ረቂቅ ተህዋስያን ምሽግ ናቸው።

ጥናቶች እንደሚሉት ፎጣዎች በተለይ በሰዎች ቆዳ ላይ በሚገኙ ባክቴሪያዎች በቀላሉ ሊበከሉ ይችላሉ።

ሰውነታችንን ከታጠብንም በኋላ እንኳን ቢሆን ሰውነታችን በማይክሮብስ (ረቂቅ ተህዋሶች) የተሸፈነ ነው።ሰውነታችንን በምናደርቅበት ጊዜ ታዲያ እነዚህን ተህዋሶች እናነሳቸዋለን።

ሆኖም በፎጣችን ውስጥ የሚገኙት ረቂቅ ተህዋስያን ምንጫቸው ሰውነታችን ብቻ አይደለም። ምንጩ ሌላም ሊሆን ይችላል።

ለምሳሌ አየር ወለድ ፈንገስ እና ባክቴሪያ ተንጠልጥለው እና ተሰቅለው በሚገኙ ፎጣዎች ውስጥ ተደላድለው ይኖራሉ። ከዚህም በተጨማሪ ፎጣዎቻችንን በምናጥብበት የተበከለ ውሃ በረቂቅ ተህዋስያን ሊበከሉ ይችላሉ።

እዚህ ላይ ዋናው ጥያቄ የሚሆነው በፎጣዎቻችን ውስጥ የሚገኙት ባክቴሪያዎች ምን ያህል አሳሳቢ ናቸው የሚለው ነው።

ፎጣ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ፎጣ ስለማጠብ ማውራት ተራ ነገር ሊመስል ይችላል።

የሥነ ሕይወት ፕሮፌሰር እና በአሜሪካ ቦስተን፣ ሳይመንስ ዩኒቨርሲቲ የንጽህና እና ጤና ማዕከል ረዳት ዳይሬክተር የሆኑት ኤልዛቤት ስኮት ረቂቅ ተህዋስያን በቤት ውስጥ እንዴት እንደሚሠራጩ እና የጤና እክል እንደሚያመጡ ያስረዳሉ።

"እነዚህ ተህዋስያን በፎጣ ውስጥ ብቻ አይቀመጡም" የሚሉት ፕሮፌሰር ስኮት፣በፎጣ ውስጥ ሆነው የጤና እክል የሚፈጥሩ ተህዋስያን ከሰዎች የሚመጡ እንደሆኑ ይገልጻሉ።

በሰውነታችን ቆዳ ላይ ካሉ ቫይረሶች እና ፈንገሶች በተጨማሪ አንድ ሺህ የሚሆኑ የባክቴሪያ ዝርያዎች ይኖራሉ።አብዛኞቹ ጠቃሚ ናቸው። እነዚህ ባክቴሪያዎች ብዙም ከሰውነታችን ጋር ባልተላመዱ ሌሎች ባክቴሪያዎች አማካኝነት ከሚመጡ በሽታዎችም ይጠበቁናል።

በዕለት ተዕለት ሕይወታችን የምንጠቀማቸውን የሰውነት ኬሚካሎች በመሰባበርም የበሽታ መከላከያ ሥርዓታችንን ለመገንባትም ወሳኝ ሚና አላቸው።

በፎጣዎቻችን ውስጥ የሚገኙት አብዛኞቹ ባክቴሪያዎች በሰውነታችን ቆዳ ላይ ከሚገኙ የባክቴሪያ ዝርያዎች ጋር ተመሳሳይ ሲሆኑ፣ ከምንኖርበት አካባቢ ካሉትም ጋር እንዲሁ ተመሳሳይነት አላቸው።

እነዚህ ባክቴሪያዎች ስታፊይሎኮከስ ባክቴሪያ እና በሰው ልጅ ሆድ ውስጥ የሚገኝ ኢሽሪኪያ ኮሊ የተባሉ የባክቴሪያ ዝርያዎችን ያካትታሉ።

ከዚህም በተጨማሪ ተቅማጥ እና በምግብ መበከል ሳቢያ ህመም የሚያስከትሉ እንደ ሳልሞኔላ እና ሺገላ ባክቴሪያዎችም ይገኛሉ።

ሆኖም ከእነዚህ ባክቴሪያዎች የተወሰኑት እንደ ካንሰር ያሉ ሌሎች በሽታዎች በሰውነታችን መከሰቱን እንደ ዕድል ተጠቅመው ጉዳት ያስከትላሉ።

ሆኖም ጉዳት የሚያስከትሉበት ቦታ ማለትም በተቆረጠ የሰውነት ክፍል በኩል ካልገቡ ያን ያህል ጉዳት አያስከትሉም። ይህንን ዕድል ካገኙ ግን ወደ ሰውነት በመግባት መርዛማነትን በመፍጠር በተለይ የበሽታ መከላከል አቅማቸው የተዳከሙ ሰዎችን ያጠቃሉ።

ቆዳችን ከተለያዩ በሽታዎች የሚጠብቀን የሰውነት ክፍላችን ነው።ውስጣዊ የሰውነት አካላችን በባክቴሪያ እና በሌሎች በሽታዎች እንዳይጠቃ የሚከላከልልን ሽፋናችን ነው። በመሆኑም ከፎጣዎቻችን ወደ ሰውነታችን የሚገቡ ባክቴሪያዎች ብዙም ሊያስጨንቁን አይገባም።

ነገር ግን ሰውነታችንን በፎጣ ማጠብ፣ ማሸት እና ማድረቅ የቆዳችንን በሽታ የመከላከል ሥርዓት ሊያስተጓጉል ይችላል።

ትልቁ ችግር የሚከሰተው ሰውነታችንን ያደረቅንበትን እና ጎጂ ተህዋስያን ያለበትን ፎጣ በእጃችን አንስተን ከነካን በኋላ አፋችንን፣ አፍንጫችንን እና ዓይናችንን ከነካን ነው።

በመሆኑም ለእጃችን ማድረቂያ በተደጋጋሚ ለምንጠቀምባቸው ፎጣዎች ትኩረት መስጠት አስፈላጊ ነው።

ፎጣ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በኩሽናችን የምንገለገልባቸው ፎጣዎችም ምግብ ወለድ በሽታ አምጪ ተህዋስያን እንዲከሰቱ መንስኤ ይሆናሉ።

ፕሮፌሰር ስኮት እንደሚሉት በሳልሞኔላ ባክቴሪያ የሚከሰተው ጋስትሮኢንተሪክ በሽታ፣ ኖሮቫይረስ እና ኢ ኮሊ በፎጣዎች አማካኝነት ነው የሚተላለፉት።

ጥናቶችም እንደሚያሳዩት እንደ ኮቪድ 19 ያሉ ቫይረሶች ምንም እንኳን በሽታው የተበከሉ ቦታዎችን መንካት ዋነኛ የበሽታ መተላለፊያ እንዳልሆነ ቢታሰብም ከጥጥ በተሠሩ ፎጣዎች ውስጥ ለ24 ሰዓታት መቆየት ይችላሉ።

ሌሎች በንክኪ የሚተላለፉ እንደ ኤምፖክስ ቫይረሶች ያሉ ቫይረሶችም በፎጣ አማካኝነት የመተላለፍ ዕድል አላቸው።የጤና ባለሙያዎችም በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ፎጣዎችን እና አንሶላዎችን መጋራትን አይመክሩም።

ከዚህም በተጨማሪ የኪንታሮት እና ቬሩኬ በሽታ የሚያስከትሉ የሰው ፓፒሎማ ቫይረሶች ፎጣዎችን ከሌሎች ሰዎች ጋር በመጋራት እንደሚተላለፉ ጥናቶች አረጋግጠዋል።

ለዚህም ነው ሆስፒታሎች እና የሕዝብ መታጠቢያ ቤቶች የወረቀት ፎጣ እና የአየር ማድረቂያ የሚጠቀሙት። ሆኖም ከእነዚህ አማራጮች የትኛው የተሻለ እንደሆነ የሚያሳይ ማስረጃ የለም።

በመሆኑም ፎጣዎችን ለረዥም ጊዜ ሳናጥብ ከተጠቀምንባቸው እና እርጥቡን ተቀምጠው ከቆዩ ለጥቃቅን ጎጂ ተህዋስያን መከማቻ ይሆናሉ።

እንደ ኤምአርኤስኤ ያሉ ፀረ ባክቴሪያን የሚቋቋሙ ባክቴሪያዎች በተበከሉ ቁሶች ንክኪ ይተላለፋሉ።

በመሆኑም የፎጣን ንጽህና በመጠበቅ በዓለማችን ካሉ ዋና ዋና የጤና እክሎች አንዱን ለመከላከል እንደሚረዳ ፕሮፌሰር ስኮት እና ባልደረቦቻቸው ይናገራሉ።

በካርዲፍ ዩኒቨርሲቲ የፋርማሱቲካል ማይክሮባዮሎጂ ፕሮፌሰር የሆኑት ጂን ይቭስ ሜላርድ እንደሚሉት ፎጣዎችን ማጠብ በባክቴሪያ የሚመጡ በሽታዎችን የሚቀንስ ሲሆን፣ በምላሹም ፀረ ባክቴሪያ መድኃኒት መጠቀምን ይቀንሳል።

"የቤት ውስጥ ንጽህና በሽታን ከመከላከል ጋር የሚያያዝ ነው። መከላከል ደግሞ ሕክምና ከመውሰድ የተሻለ ነው" ብለዋል።

ታዲያ ፎጣዎቻችንን በምን ያህል ጊዜ ነው ማጠብ ያለብን ?

ፕሮፌሰር ስኮት ፎጣዎቻችንን በሳምንት አንድ ቀን ማጠብ እንደሚገባ ይመክራሉ።ይህ ግን የተደነገገ ሕግ አይደለም።በአንዳንድ ሁኔታዎች በተደጋጋሚ ማጠብ ሊያስፈልግ ይችላል።

"ለምሳሌ አንድ ሰው ከታመመ ያስመልሰዋል፤ያስቀምጠዋል። በመሆኑም የራሳቸው ፎጣ ያስፈልጋቸዋል። በመሆኑም እነዚህ ፎጣዎች በየቀኑ መታጠብ ይኖርባቸዋል።"

በሕንድ ለተሠራ አንድ ጥናት ምላሽ ከሰጡ ሰዎች 20 በመቶ የሚሆኑት ፎጣቸውን በሳምንት ሁለት ጊዜ እንደሚያጥቡ አመልክቷል።

እንደ ስኮት ከሆነ ፎጣዎች ከሌሎች ልብሶች በበለጠ ከ40 እስከ 60 ዲግሪ ሴልሽየስ የሞቀ ውሃ እና ረዘም ላለ ጊዜ በፀረ ባክቴሪያ ሳሙና መታጠብ አለበት።

ሳሙናዎች ባክቴሪያዎች በፎጣዎቹ ውስጥ ተጣብቀው እንዳይቀሩ የሚያደርጉ ሲሆን፣ አንዳንድ ቫይረሶችንም ይገድላሉ።

በእርግጥ በከፍተኛ ሙቀት በተደጋጋሚ ማጠብ አካባቢያዊ ዋጋ ያስከፍላል።

በዚህ ምክንያት በዝቅተኛ ሙቀት የምናጥብ ከሆነም የሚያነጹ አሊያም ሌሎች ፀረ ባክቴሪያ ኤንዛይሞችን መጠቀም ረቂቅ ተህዋስያንን ለመከላከል ይረዳል።

በሕንድ የተሠራ አንድ ጥናት ፎጣዎችን ስናለቀልቅ ወይም ስናደርቅ ፀረ ባክቴሪያ ፈሳሽ መጠቀም የባክቴሪያ እና የፈንገስ ክምችትን ለመቀነስ ውጤታማ እንደሆነ አሳይቷል።

ስኮት የቤት ውስጥ ንጽህና እንደ ክትባት ነው ይላሉ። ራሳችንን ለመጠበቅ የምናደርገው እያንዳንዱ ተግባር በዙሪያችን ያሉ ሰዎችን ጤንነት ለመጠበቅም ይረዳል።