ኢትዮጵያ በ2024 የወባ ስርጭት ከተስፋፋባቸው አገራት አንዷ መሆኗን የዓለም የጤና ድርጅት አስታወቀ

ፓራሳይቱን ተሸካሚ የሆነች አስተላለፊ ቢምቢ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ኢትዮጵያ፣ የመን እና ማዳጋስካር እአአ በ2024 በከፍተኛ ደረጃ የወባ ስርጭት የተስፋፋባቸው አገራት መሆናቸውን የዓለም የጤና ድርጅት አስታወቀ።

ድርጅቱ፤ ወባ በ2024 ብቻ 610,000 ገደማ ሰዎችን መግደሉን ገልጿል።

የተባበሩት መንግሥታቱ የጤና ተቋም ሐሙስ ዕለት ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳለው አብዛኛዎቹ በወባ ተይዘው የሞቱት ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት የሚኖሩ ሕጻናት ናቸው።

መድኃኒትን የሚቋቋም የወባ ዝርያ መፈጠሩ፣ የአየር ንብረት ለውጥ እና የገንዘብ ድጋፍ መቀነስ በሽታው ይበልጥ ሊስፋፋ ይችላል የሚል ስጋት የፈጠሩ ጉዳዮች መሆናቸውን አስታውቋል።

እንደ አውሮፓውያኑ በ2023 በበሽታው ከሞቱ ሰዎች ቁጥር የ2024ቱ ትንሽ ከፍ ያለመሆኑን ጨምሮ ገልጿል።

በተጨማሪም በበሽታው የተያዙ አዲስ ሰዎች ቁጥር ከ273 ሚሊዮን ወደ 282 ሚሊዮን ከፍ ብሏል ተብሎ እንደሚገመት የዓለም ጤና ድርጅት ዓመታዊ የወባ ሪፖርት አሳይቷል።

እአአ በ2000ዎቹ ወባን በመከላከል ረገድ ከፍተኛ መሻሻል ታይቶ የነበረ ሲሆን ባለፉት ጥቂት ዓመታት ግን በሽታውን ለመከላከል የሚደረገው ትግል መቆሙን ድርጅቱ ገልጿል።

እስካሁን ድረስ 47 አገሮች ከወባ ነፃ መሆናቸው ተረጋግጧል። በአንጻሩ፤ በተለይም በኢትዮጵያ፣ ማዳጋስካር እና የመን በበሽታው የሚያዙ አዲስ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ መጨመር አሳይቷል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በዓለም ጤና ድርጅት የዓለም አቀፍ የወባ ፕሮግራም ዳይሬክተር ዳንኤል ንጋሚጄ ማዳንዲ "ብዙ ሰዎች አሁንም መከላከል እና መዳን በሚችል በሽታ እየሞቱ ነው" ማለታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

ከአየር ንብረት ለውጥ እና ግጭት ጎን ለጎን አንዳንድ የወባ ዝርያዎች የመከላከያ መድሃኒቶችን እና በአጎበር ላይ የሚነከሩ ፀረ ተባዮችን የመቋቋም አቅማቸው እየጨመረ መምጣቱ በሽታውን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት የሚፈታተኑ ናቸው ብለዋል።

በበሽታው የሚያዙ አዲስ ሰዎች እና የሞቱ ሰዎች ቁጥር መጨመር በከፊል ከሕዝብ እድገት ጋር የተቆራኘ መሆኑን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት እአአ ከ2015-2024 ባሉት ጊዜያት ውስጥ በበሽታው የሚያዙ አዲስ ሰዎች ቁጥር መጨመሩን ገልጿል።

ከ100,000 ሰዎች ውስጥ ከ59 እስከ 64 የሚሆኑት ለበሽታው የመያዝ ዕድላቸው ከፍ ያለ ነው።

በበሽታው የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ደግሞ በትንሹም ቢሆን መቀነሱን የገለፀው ድርጅቱ ከ100,000 ሰዎች ከ14.9 ወደ 13.8 መቀነስ ማሳየቱን ጠቅሰዋል።

እንደ የዓለም የጤና ድርጅት ገለጻ፤ የተገኘው የገንዘብ ድጋፍም ከሚያስፈልገው በታች ነው። ለጋሾች እና አገራት ወባን ለመቆጣጠር በ2024 ወጪ ያደረጉት ገንዘብ 3.9 ቢሊዮን ዶላር ነው።

ይህ ቁጥር ድርጅቱ ካስቀመጠው የ9 ቢሊዮን ዶላር በላይ ዕቅድ እጅጉን ያነሰ ነው።

ባለፈው ዓመት የተመዘገበው በበሽታው አዲስ የተያዙ እና የሞቱ ሰዎች ቁጥር በዚህ ዓመት ከተቋረጠው እርዳታ ጋር የሚያያዝ አይደለም ተብሏል።

ዶናልድ ትራምፕ በጥር 2017 ዓ.ም. ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ አገሪቱ ለወባ ሕክምና የምትሰጠውን ድጋፍ አቋርጠዋል። ይህ እርምጃ በዚህ ዓመት ወባን ለመከላከል የሚደረገውን ትግል በእጅጉ እንደሚጎዳው ተሰግቷል።

ሮይተርስ የዜና ወኪል ንጋሚጄ "ለወባ መከላከል የሚሰጠው አነስተኛ የገንዘብ ድጋፍ . . . ግልጽ የሆነ አደጋን፣ ትልቅ እና ከቁጥጥር ውጪ የሆነ የበሽታ ስርጭትን ያስከትላል" ሲሉ ማስጠንቀቃቸውን ዘግቧል።

ሕክምና፣ ምርመራ እና የወባ ክትባቶችን ጨምሮ አዳዲስ እና የተሻሉ መሳሪያዎች ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን እንዲሁም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሕይወቶችን መታደግ መቻላቸው ተገልጿል።

ነገር ግን ተገቢ ተፅዕኖ እንዲኖራቸው ለአደጋ የተጋለጡት ሰዎች ጋር መድረስ አለባቸው ሲሉ የተናገሩት ዳይሬክተሩ፣ ኃላፊነቱ የሚወድቀው በተጎዱ አገራት መንግሥታት እንዲሁም በዓለም አቀፍ ለጋሾች ላይ ነው ብለዋል።

አብዛኛውን ጊዜ ሰዎችን ወባ የሚይዛቸው ፓራሳይት ተሸካሚና አስተላላፊ በሆነች ሴት አኖፌሌስ በተሰኘች ቢምቢ ሲነከሱ ነው። የአኖፌሌስ ቢምቢ ብቻ ከ400 ዘር በላይ ሲሆን ከእነሱ መካከል 30ዎቹ ብቻ ናቸው ወባ የሚያስተላልፉት።

ሁሉም የማላሪያ ተሸካሚና አስተላላፊ የሆኑ ቢምቢዎች ሌሊቱ ሊነጋጋ ሲል የሚናከሱ ናቸው።

አኖፌሌስ የተሰኙት ቢምቢዎች እንቁላሎቻቸውን በውሃ ላይ የሚወልዱ ሲሆኑ፤ እንቁላሎቹ ወደ ዕጭ ተቀይረው ሰብረው ሲወጡ ሙሉ በሙሉ ያደገ ቢምቢ ሆነው ይወጣሉ።

ወላጅ ቢምቢዎች እንቁላሎቻቸውን ለማሳደግ የሚመግቧቸው የሰው ደም ነው።