እንደ ድሀ የሚኖረው ቱጃሩ ኤሎን መስክ ገንዘቡ ምን ላይ ያውለዋል?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የቴስላው አለቃ ኤሎን መስክ ለበርካታ ዓመታት የቆየበትን የዓለም ቁጥር አንድ ሀብታምነት መንበር እንደተቆናጠጠ አሁንም ቀጥሏል። በቅርቡ ደግሞ ሀብቱ ግማሽ ትሪሊዮን የደረሰ የመጀመሪያው ሰው ሆኗል።
መስክ ከዚህ የሀብት ማማ ላይ ቢሆንም እንኳ አኗኗሩ ቅንጡ የሚባል እንዳልሆነ ይናገራል። ኑሮውን ያደረገው በቴክሳስ በሚገኝ ዋጋው 50,000 ሺህ ዶላር በሆነ ቤት ውስጥ እንደሆነ በአውሮፓውያኑ 2021 ተናግሮ ነበር።
የቀድሞ አጋሩ እና የሁለት ልጆቹ እናት ግሪምስም በተመሳሳይ አኗኗሩ ብዙዎች እንደሚገምቱት ከልክ ያለፈ ቅንጦት ያለበት እንዳልሆነ 2022 ላይ ለቫኒቲ ፌር መጽሔት ተናግራ ነበር።
"ሰውየው እንደ ቢሊየነር አይኖርም። አንዳንዴ ከድህነት ወለል በታች ነው የሚኖረው" ማለቷን መጽሔቱ ዘግቧል። አንድ ጊዜ እንደውም እሷ በምትተኛበት በኩል ያለው የአልጋቸው ፍራሽ ቀዳዳ ያለበት ሆኖ እንኳ አዲስ ፍራሽ ለመግዛት ፈቃደኛ አለመሆኑን አስታውሳለች።
ብዙዎች እንደሚጠብቁት የዕለት ተዕለት ኑሮው በድሎት የተሞላ ባይሆንም ግን ለየት ያሉ መኪናዎች በእጅጉ ይወዳል። የባሕር ሰርጓጅ መሆን የሚችል መኪና አሠርቶ እንደነበርም አይዘነጋም።ኤሎን መስክ የግል ጄቶች ስብስብም አለው፤ ብዙዎቹ በሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ ናቸው።
በ2022 በድንገት ተነስቶ በ44 ቢሊዮን ዶላር ኤክስ በማለት ስያሜውን የቀየረውን ትዊተርን የገዛበት ጊዜም አይረሳም።
መልሶ የሸጣቸው ቅንጡ መኖሪያዎች
ኤሎን መስክ የሆነ ወቅት ላይ እጅግ የሚያስደንቁ የሪል ኢስቴት ቤቶች ነበሩት። በ2019 የወጣ የዎል ስትሪት ጆርናል ዘገባ እንደሚያመለክተው በሰባት ዓመታት ውስጥ ሰባት ቤቶችን ለመግዛት 100 ሚሊዮን ዶላር አውጥቷል።
ከእነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ በካሊፎርኒያ በሚገኘው ቤል ኤር የሀብታሞች መንደር ውስጥ ተቀራራቢ ቦታ ላይ የሚገኙ ነበሩ።
መኖሪያ ቤቶቹ መዋኛ ገንዳ፣ የቴኒስ ሜዳ፣ የወይን ማስቀመጫ፣ የግል ቤተ መጽሐፍት እና አዳራሽ የነበራቸው ናቸው። ከእነዚህ ቤቶች አንዱ ዊሊ ዎንካ የተባለ ገጸ ባህሪን በመጫወት የሚያወቀው የዝነኛው ተዋናይ ጄን ዊለደር መኖሪያ ነበር።
2020 ላይ ግን መስክ ሀሳቡን ቀየረ። ያሉትን "ቁሳዊ ንብረቶች ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ እንደሚሸጥ" እና "ምንም ቤት እንደማይኖረው" ትዊተር ላይ ጻፈ።
በትዊተር ገጹ "ገንዘቡን አልፈልገውም። ራሴን ለማርስ እና ለምድር እሰጣለሁ። [የቁሳዊ ንብረት] ባለቤትነት ያዘናጋል" ብሎ ለጠፈ።
ይህንን ዐቅዱን ይፋ ሲያደርግ ታዲያ አንድ ቅድመ ሁኔታ አስቀምጧል። ቅድመ ሁኔታው የተዋናዩ ጄን ዊለደር ቤትን "ማፍረስ ወይ አንዱንም ነፍስያውን ማሳጣት አይቻልም" የሚል ነበር።
እንዳለውም ሦስት መኝታ ቤቶች ያሉት ይህንን ቤት የተዋናዩ እህት ልጅ ለሆነው ጆርዳን ዎከር ፐርልማን ሸጠለት። ዎከር ፐርልማን ቤቱን መግዛት እንዲችል በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላርም አበድሮታል። ሆኖም ግን ግለሰቡ የተበደረውን ገንዘብ መመለስ ባለመቻሉ ከወራት በፊት ሰኔ 2025 ላይ መስክ መልሶ የቤቱ ባለቤት ሆኗል።
መስክ "ዋነኛ መኖሪያው" በደቡባዊ ቴክሳስ የሚገኝ፣ ቀለል ብሎ የተሠራ እና 50 ሺህ ዶላር የሚያወጣ ቤት እንደሆነ 2021 ላይ በትዊተር ገጹ ጽፎ ነበር። መኖሪያ ቤቱ የሚገኝበት ስፍራ 'ስፔስ ኤክስ' ከተባለው የመሰክ ኤሮስፔስ ኩባንያ አቅራቢያ የሚገኝ ነው። ኩባንያ የሚገኝበት ስፍራ ስታርቤዝ የሚል ስም ወጥቶለታል።
"አሪፍ ነገር ነው" ሲል በዚያ ቤት መኖር ምን እንደሚመስል ይገልጻል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በቀጣዩ ዓመት ደግሞ ጭራሹኑ የአንድም ቤት ባለቤት እንዳልሆነ ተናገረ። ቢሊየነር ሆኖ ሳለ የኑሮ ወጪው ምን ያህል አነስተኛ እንደሆነ ምሳሌ እየጠቀሰ ያስረዳ ጀመር።
"የእውነት የማድረው ጓደኞቼ ቤት ነው" ሲል "ቲኢዲ" የተሰኘው የመገናኛ ብዙኃን ድርጅት ኃላፊ ለሆነው ክሪስ አንደርሰን ተናግሯል።
"ብዙ የቴስላ መሃንዲሶች ወደሚገኙበት ቤይ ኤሪያ [አካባቢ] ከተጓዝኩ ወዳጆቼ ጋር እየተዘዋወርኩ ትርፍ መኝታ ቤት [ውስጥ አድራለሁ]" ብሏል።
መስክ እንዲህ ዓይነት ኑሮ ሲመራ የመጀመሪያው አልነበረም። የቀድሞው የጎግል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ላሪ ፔጅ ኤሎን መስክ "ቤት አልባ ሊባል የሚችል" ሰው እንደሆነ በአውሮፓውያኑ 2015 ጠቅሶ ነበር።
"ኢሜይል ጽፎ፤ 'ዛሬ የት እንደማድር አላውቅም። መምጣት እችላለሁ' ብሎ ይጠይቃል" ሲል ተናግሯል።
መስክ በመላው አሜሪካ ቤቶችን እየገዛ ነው የሚሉ ግምት ለዓመታት ሲሠራጭ ቆይቷል። ኋላ ግን መስክ ባለቤት የሆነበት መኖሪያ የቴክሳሱ ብቻ እንደሆነ ታይቷል።
ለየት ያሉት የመኪና ስብስቦች
መስክ መኖሪያ ቤት ለመግዛት ከፍተኛ ገንዘብ አያወጣም ማለት ግን ስለ መኪናዎችም እንደዚህ ነው የሚያስበው ማለት አይደለም።
የኤሌክትሪክ መኪና አምራቹ ኩባንያ ቴስላ ባለቤት እንደመሆኑ ያልተለመዱ፣ አንዳንድ ጊዜም በጣም የተለዩ ተሽከርካሪዎች ትልቅ ስብስብ ያለው መሆኑ የሚያስገርም አይደለም።
ከስብስቦቹ አንዱ ፎርድ ቲ የተባለው የ20ኛው ክፍለ ዘመን መኪና ነው። ይህ ተሽከርካሪ ማንም ሊገዛ በሚችልበት ዋጋ የቀረበ የመጀመሪያው መኪና ነው። የሞተር ኢንዱስትሪው ላይም አብዮት ያቀጣጠለ ነው።

የፎቶው ባለመብት, NurPhoto via Getty Images
በአውሮፓውያኑ 1967 የተመረተው 'ኢ-ታይፕ ሮድስተር' ጃጓር መኪናም አለው። መስክ ይህንን መኪና ከልጅነቱ ጀምሮ ይፈልገው የነበረ ነው። የ1997 ማክላሬን ኤፍ1 መኪናው ደግሚ ተጋጭቶ ለጥገና ብዙ ገንዘብ ካስወጣው በኋላ ሽጦታል።
መስክ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሽያጭ ያቀረበው ቴስላ ሮድስተር መኪናም ነበር። 2018 ላይ ግን ሮኬት ውስጥ ጭኖ ወደ ከምድር ውጪ ወዳለወ ሕዋ አስወንጭፎታል።
ከሁሉም ለየት ያለው ግን በ1977ቱ 'ዘ ስፓይ ሁ ላቭድ ሚ' በተሰኘ ፊልም ላይ ታዋቂው የጄምስ ቦንድ ገጸ ባህሪ የነዳው የ1976 ሎተስ ኢስፕሪት መኪና ነው።
ፊልሙ ላይ 'ዌት ኔሊ' የሚል ቅጽል ስም የተሰጠው መኪና ወደ የባሕር ሰርጓጅነትን ይቀየራል። መስክ በ2013 ከተካሄደ ጨረታ ላይ በ1 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ገዝቶታል። ዓላማው የነበረውም መኪናውን የእውነት ወደ ባሕር ሰርጓጅነት የመቀየር አቅም እንዲኖረው ማድረግ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Screen Archives/Getty Images
በአውሮፕላን ወደ ሥራ መብረር
መሰክ አውሮፕላኖች ላይ ገንዘቡን ማፍሰስ እንደሚያስደስተው ከዚህ ቀደም ተናግሯል። ይህ የሚሆነው ግን ለሥራው ካለው ቁርጠኝነት በመነጨ እንደሆነ ይገልጻል።
"አውሮፕላን የማይኖረኝ ከሆነ ሥራ ላይ የማውለው ጊዜ ይቀንሳል" ሲል በ2022 ቃለ መጠይቅ ላይ ተናግሯል።
ካሉት የግል ጄት ስብስቦች ውስጥ 'ገልፍስትሪም' የተባለው የአውሮፕላን አምራች ኩባንያ ሞዴል የሆኑ ይገኙበታል። እነዚህ ጄቶች በአስር ሚሊዮኖች ሚቆጠር ዶላር ወጥቶባቸዋል።
አሜሪካ ውስጥ ወደ ስፔስ ኤክስ እና ቴስላ ኩባንያዎች ለመመላለስ ይጠቀምባቸዋል። ለዓለም አቀፍ ጉዞም ይበርባቸዋል።
ጥያቄ የሚያስነሳው የበጎ አድራጎት ሥራ
የአሜሪካ መንግሥት ተቆጣጣሪ መሥሪያ ቤት ሰነዶች እንደሚያሳዩት መስክ በቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ አክስዮኖችን ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች ለግሷል። ለተለያዩ ጉዳዮችም በብዙ ሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ ለመስጠት ቃል ገብቷል።
የመስክ የበጎ አድራጎት ሥራ ግን ትችት ይቀርብበታል።
የአሜሪካው ኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ባለፈው ዓመት ባወጣው ዘገባ የእርዳታ ሥራውን "ዕቅድ የለሽ፣ ብዙውን ጊዜ ራሱን የሚጠቅም፤ ግዙፍ የታክስ እፎይታ እንዲያገኝ ብቁ ያደርገው እና ሌሎች ቢዝነሶቹን ለማገዝ ያስቻለው" እንደሆነ አትቷል።
የበጎ አድራጎት ሥራዎችን የሚያከናውነው 'መስክ ፋውንዴሽን' የተባለው ድርጅቱ በድረ ገጹ ላይ፤ "የሰው ልጅን ዕድገት ለማፋጠን የተቋቋመ" እንደሆነ አስፍሯል። ይህንን የሚያደርገውም "ሳይንሳዊ የፈጠራ ምርምሮችን፣ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎችን" በማከናወን እንደሆነም ይገልጻል።
በኒው ዮርክ ታይምስ ዘገባ መሠረት ግን ፋውንዴሽኑ ለተከታታይ ሦስት ዓመታት መለገስ የሚጠበቅበትን ያህል ገንዘብ አልሰጠም።
የፋውንዴሽኑን የታክስ መዝገቦች የተመለከተው የጋዜጣው ዘገባ እንደሚያመለክተው፤ ብዙዎቹ ልገሳዎች የተሰጡት ከመስክ ጋር ግንኙነት ላላቸው ድርጅቶች ነው።
ኤሎን መስከ እና መስክ ፋውንዴሽን በጉዳዩ ላይ መልስ እንዲሰጡ ጥያቄ ቀርቦላቸዋል።
መስክ ከዚህ ቀደም ወደ በጎ አድራጎት እና ልገሳ ሥራ ውስጥ ስለ ገባበት ምክንያት ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽ ሲሰጥ፤ ባህላዊ የበጎ አድራጎት ተግባር የሚሰጡ ስጦታዎች ላይ ጥርጣሬ እንዳለው ጠቁሞ ነበር።
"ከዕይታ ይልቅ የእውነት ስለ ጥሩነት ግድ የሚልህ ከሆነ የበጎ አድራጎት ሥራ እጅግ ከባድ ይመስለኛል" ሲል ተናግሯል።
መስክ እንደሚናገረው የሚከፍታቸው የቢዝነስ ድርጅቶች ዋነኛ ዓላማቸው በጎ አድራጎት ነው። "ሰውነትን መውደድ በጎ አድራጎት ከሆነ በጎ አድራጎት [ሥራዎች] ናቸው" ሲል ይከራከራል።
ቴስላ፤ "ዘላቂ ኃይል" የመጠቀምን አቅም "እያቀላጠፈ" መሆኑን የሚናገረው መስክ፤ ስፔስ ኤክስ ደግሞ "የሰውን ልጅ የረጅም ጊዜ ህልውና ጉዳይ ለማረጋገጥ እየሞከረ"መሆኑን ያስረዳል።
ኒውራሊንግ የተባለው ኩባንያው ደግሞ የአእምሮ ጉዳት እና የህልውና አደጋን በሰው ሰራሽ ልህቀት (ኤአይ) ለመፍታት እገዛ እያደረገ መሆኑን ይጠቅሳል።















