የኤርትራ መንግሥት ያለፍርድ ለ18 ዓመታት አስሯቸው የነበሩ 13 ሰዎችን ለቀቀ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኤርትራ መንግሥት በወታደራዊ እስር ቤት ያለ ፍርድ ለ18 ዓመታት ያህል አስሯቸው የነበሩ 13 ሰዎችን መልቀቁን ቤተሰቦቻቸው ለቢቢሲ ትግርኛ ተናገሩ።
አስራ ሦስቱ ግለሰቦች ታስረው የነበረው በአስቸጋሪ አነወኗር ማይ ስርዋ ተብሎ በሚጠራ ጥብቅ ቁጥጥር በሚደረግበት ወታደራዊ እስር ቤት ነው።
ከእስር የተለቀቁት ሰዎች ነጋዴዎች፣ የፖሊስ አባላት እንዲሁም በተለያየ የሙያ ዘርፎች ላይ ተሰማርተው የነበሩ ባለሙያዎች ሲሆኑ፣ ያለ ምንም ማብራሪያ ሐሙስ ኅዳር 25/2018 ዓ.ም. ተለቀው ከቤተሰባቸው ጋር ተቀላቅለዋል።
በማይ ስርዋ ወታደራዊ እስር ቤት ታስረው የነበሩ እና ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ አንድ ግለሰብ ለቢቢሲ ትግርኛ እንደተናገሩት ጥቅምት 2000 ዓ.ም. ላይ በወቅቱ የአገር ውስጥ ደኅንነት ኃላፊ ከነበሩት ከኮሎኔል ስምኦን ገብረድንግል የግድያ ሙከራ ጋር ተያይዞ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ገልፀዋል።
አክለውም የተያዙት ከሁለት ነጋዴዎች ጋር በተያያዘ መሆኑን አብራርተዋል።
መጀመሪያ ላይ 30 የሚሆኑ ሰዎች በቁጥጥር ሥር ውለው የነበረ ሲሆን፣ የተወሰኑት ከዓመታት እስር በኋላ ተለቅቀው 20ዎቹ ብቻ በአስቸጋሪው እስር ቤት ውስጥ ቆይተዋል።
ከተለቀቁት መካከል የቀድሞው የኦሊምፒክ ብስክሌተኛ እና ነጋዴ ዘርአግብር ገብረሕይወት፣ በንግድ ሥራቸው ታዋቂ የሆኑት ተስፋለም መንግሥተአብ እና በኩረ መብርሃቱ እንዲሁም ኢንጂነር ዳዊት ኃብተማሪያም እና ማቲዮስ ኃብተማሪያም የተባሉ ሁለት ወንድማማቾች ይገኙበታል።

የፎቶው ባለመብት, Human right council
በተጨማሪም ስድስት ነባር የኤርትራ ፖሊስ አባላት ሁለት አስርት ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ ከቆየው እስር በኋላ ከተለቀቁት መካከል ናቸው።
ከእነዚህም መካከል የቀድሞው ወንጀል መከላከል ኃላፊ፣ የወንጀል ምርምራ፣ ፋይናንስ እና አስተዳደር እንዲሁም ደኅንነት ኃላፊዎች እንዲሁም ካፒቴን እና ሁለት ከፍተኛ የምረምራ ባለሙያዎች ይገኙበታል።
ከተለቀቁት መካከል የቀድሞው የአገር ውስጥ ደኅንነት ባለሙያ እንደሚገኙበትም ቢቢሲ ኤርትራ ውስጥ ከሚገኙት ምንጮቹ ማረጋገጥ ችሏል።
ከዚህ ቀደም አምንስቲ ኢንተርናሽናል በአዲ አቤይቶ እና ማይ ስርዋ በሚባሉት እስር ቤቶች ውስጥ በአሰቃቂ ሁኔታ ያለ በቂ ውሃ እና ንጽህና ተይዘው የሚገኙ ግለሰቦቸ እንዲለቀቁ ጠይቆ ነበር።
ካለፍርድ ቤት ውሳኔ ለረጅም ዓመታት በእስር ላይ የቆዩት ግለሰቦች በቆይታቸው ወቅት ቤተሰቦቻቸው እንዲጠይቋቸው አልተፈቀደላቸውም።
አስራ ሦስቱ የተለቀቁት ሰዎች በ18 ዓመት የእስር ቤት ቆይታቸው ወቅት ፍርድ ቤት ቀርበው እንደማያውቁ ተገልጿል።
ማይ ስርዋ ወታደራዊ እስር ቤት 76 ከኮንክሪት የተሠሩ ክፍሎች ያሉት ሲሆን፣ በቅርቡ አምስት ትልልቅ ክፍሎች እና 20 ኮንቴይነሮች ተጨምረውለት ማስፋፊያ እንደተደረገለት የቢቢሲ ምንጮች ተናግረዋል።
ማይ ስርዋ የሚገኘው ከኤርትራ ዋና ከተማ አሥመራ ወጣ ብሎ በሰሜን ምዕራብ 9 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው።
የኤርትራ መንግሥት የግለሰቦቹን መለቀቅ በተመለከተ እስካሁን ድረስ ያለው ነገር የለም።















