ከአሜሪካ ጋር የጦር መሳሪያ ፉክክርን ያስከትላል የተባለው እጅግ የረቀቀው የቻይና የጦር መርከብ

ሁለት ተዋጊ ጄቶች እና ሂሊኮፕተር የጫነው አዲሱ 80 ሺ ቶን የሚመዝነው ፉጂያን የተሰኘው የቻይና አውሮፕላን ተሸካሚ መርከብ

የፎቶው ባለመብት, CCTV

የምስሉ መግለጫ, ቻይና ያመረተችው አዲሱ ፉጂያን የተሰኘው አውሮፕላን ተሸካሚ መርከብ 80 ሺ ቶን ይመዝናል

እንደ አውሮፓውየኑ በኅዳር 2025 በይፋ ሥራ የጀመረው የቻይና ሦስተኛው አውሮፕላን ተሸካሚ መርከብ ከዚህ ቀደም ከተመረቱት ሁለቱ እጅግ የላቀ መሆኑን ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ቤጂንግ በምዕራባዊ ፓስፊክ የአሜሪካን የበላይነት ለመገዳደር ወደ ያዘችው ግብ በማቅረብ ረገድ ትልቅ ለውጥ እንደሚያመጣ እነዚህ ባለሙያዎች ጨምረው ገልጸዋል።

80,000 ቶን የሚመዝነው ፉጂያን የተሰኘው መርከብ ለታይዋን ቅርብ በሆነው ግዛት ስም የተሰየመ ነው።

እስከ 70 የሚደርሱ አውሮፕላኖችን፣ ተዋጊዎችን ጨምሮ፣ ሄሊኮፕተሮች እና ቅድመ ማስጠንቀቂያ የሚሰጡ አውሮፕላኖችን ይሸከማል።

ከዚህ በተጨማሪ ከረዥም ርቀት አደጋዎችን መለየት፣ የአየር መከላከያዎችን በማስተባበር ዒላማውን የጠበቀ ጥቃቶችን መፈፀምም ይችላል።

ለቻይና የባሕር ኃይሏን ሙሉ ለሙሉ ወደ አዲስ ደረጃ ከፍ የሚያደርግ እና የቅልጥፍና ደረጃውን የሚጨምር ቢሆንም ይህ ግን ለሌላው ዓለም የደረሰችበትን እና ያላትን አቅም የምታሳይበት ብቻ ነው።

ይህ ለቻይና የመጀመርያዋ የሆነው መርከብ ጠፍጣፋ መንደርደሪያ ያለው ግዙፍ አውሮፕላኖች በቀላሉ እንዲያንሱ እና እንዲያርፉ የሚያስችል የኤሌክትሮማግኔቲክ ካታፑልት የተገጠመለት ነው።

ይህ አቅም ያላት ሌላኛዋ አገር አሜሪካ ብቻ ነች።

የታይዋን ብሔራዊ መከላከያ እና ደህንነት ምርምር ኢንስቲትዩት ባልደረባ የሆኑት ዶ/ር ዊልያም ሲ ቹንግ "ይህ የቻይናን አውሮፕላን ተሸካሚ መርከብ ብዛት ወደ አዲስ ደረጃ ከፍ ያደርገዋል" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"በእርግጥ የመርከቧ ንድፍ እና የኤሌክትሮማግኔቲክ ካታፑልት የአውሮፕላኖቹን መነሳት እና የማረፊያ ቅልጥፍናን በእጅጉ ያሻሽላሉ። ስኪ ጃምፕ የተሰኘ መንደርደሪያ ያላቸው አውሮፕላን ተሸካሚ መርከቦች [ጠፍጣፋ የበረራ ወለል ካላቸው ይልቅ] አብራሪዎችን በክብደት የተነሳ ለማረፍ እና ለመነሳት ፈተና ይገጥማቸዋል። ይህም አቅማቸውን ይገድባል።"

በቻያና ሁለተኛው የአውሮፕላን ተሸካሚ መርከብ ሻንዶንግ ላይ ተዋጊ አውሮፕላኖች እና ሂሊኮፕተሮች በተለምዶ 'ስኪ ጃምፕ" በሚባለው መንደርደሪያ ባለው መርከብ ላይ ተቀምጠው ይታያሉ

የፎቶው ባለመብት, CCTV

የምስሉ መግለጫ, የቻይና ሁለተኛው አውሮፕላን ተሸካሚ መርከብ፣ ሻንዶንግ በተለምዶ 'ስኪ ጃምፕ' እየተባለ የሚታወቀው ማኮብኮቢያ እና ማረፊያ ሜዳ ያለው ነው

የመንግሥት ሚዲያዎች ፉጂያንን በቻይና የባሕር ኃይል ውስጥ "ትልቅ ምዕራፍ " ሲሉ አወድሰዋል።

ቻይና አሁን ከአሜሪካ ጋር እኩል የሆነ "የጦር ኃይል ዲፕሎማሲ" ልታካሄድ ትችላለች ሲሉ ዶ/ር ቹንግ ለቢቢሲ ኒውስ ቻይኒዝ ተናግረዋል።

ኒውዮርክ ታይምስ በበኩሉ ከ"መከላከያ ዘመናዊነት" ወደ "አጥቂ ኃይል" እየተሸጋገረች ነው ሲል ዘግቧል።

የቻይናው ፕሬዝዳንት ጂንፒንግ ዢ "ፓስፊክ ውቅያኖስ ለአሜሪካ እና ለቻይና በጣም ሰፊ ነው" በማለት የተናገሩት ይህንን የሁለቱ አገራት በአቻነት የመቆም ፍጥጫ ጠቅልሎ ያስቀምጣል።

ቻይና በ ዢ አመራር ሥር የባሕር ኃይሏን በከፍተኛ ፍጥነት እያስፋፋች ትገኛለች። በዚህም የተነሳ አሁን ከማንም በላይ ብዙ መርከቦች አሏት፤ ይህም በአሜሪካ እና በተባባሪዎቿ ላይ ጫና ፈጥሯል።

ፉጂያን የኤሌክትሮማግኔቲክ ካታፑልቶችን እንዲጠቀም "ፕሬዚዳንቱ ራሳቸው ወስነዋል" ሲል የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

በደቡባዊ ደሴት ሃይናን ግዛት በመገኘት የጦር ጄት ተሸካሚ መርከቦችን በመጎብኘት ካፒቴኖችን፣ አብራሪዎቻቸውን እንደ አገሪቱ ጀግኖች አመስግነዋል።

የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ዢ የመከላከያ ሠራዊት የደንብ ልብስ ለብሰው የተደረደሩት የበረራ ባልደረቦችን ሰላምታ በመስጠት "የፓርቲውን ትዕዛዝ አክብሩ፣ ለማሸነፍ ተዋጉ፣ እና ጥሩ ሥነምግባርን ይኖራችሁ!" በማለት ንግግር አድርገዋል።

የአሜሪካ ባሕር ኃይል ንብረት የሆ��ው የጦር ጄቶች ተሸካሚ መርከብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የአሜሪካ ባሕር ኃይል ንብረት የሆነው እና የኒውክሌር ሚሰዔሎችን ጨምሮ በርካታ የጦር ጄቶችን የሚሸከመው የጦር መርከብ

የአውስትራሊያ የስትራቴጂክ ፖሊሲ ኢንስቲትዩት ፉጂያንን ተዋጊዎችን እና የውሃ ውስጥ ጦር መሣሪያዎችን በውጊያ ወቅት ማጓጓዝ የሚችል "ፈጣን መከላከያ" በማለት ጠርቶታል።

ዶ/ር ቹንግ ለቢቢሲ ኒውስ ቻይኒዝ እንደተናገሩት "በሠላም ጊዜ ፉጂያን ከአሜሪካ የጦር አውሮፕላን ተሸካሚ ጋር ተመሳሳይነት ያለው መከላከያን ያመቻቻል። ለረዥም ጊዜ፣ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ፣ አፍሪካ ወይም አውሮፓ ሊሰማራ የሚችል ዓለም አቀፍ ተደራሽነት እንዲኖር ያስችላል።"

ቤጂንግ ራሷን በራሷ የምታስተዳድረዋን ታይዋንን የግዛቷ አካል አድርጋ ስትመለከት የቆየች ሲሆን አንድ ቀን በኃይልም ቢሆን "እንደገና ልትቀላቀል" እንደምትችል ገልጻለች።

መቀመጫውን በዋሽንግተን ያደረገው የሃድሰን ኢንስቲትዩት የጥናት ቡድን አባል የሆኑት ዶ/ር ሳቶሩ ናጋኦ፣ ፉጂያን በፓስፊክ ውቅያኖስ የታይዋን ምሥራቃዊ የመከላከያ ምሽግ ላይ ስጋት የመፍጠር አቅም እንዳለው ጠቁመዋል።

ምንም እንኳን በኦኪናዋ፣ ጃፓን፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ጉዋም እና ፊሊፒንስ የሚገኙ የአሜሪካ የባሕር ኃይል በቀላሉ ጥቃት ሊያደርሱ ቢችሉም "ፉጂያንን እዚያ ማሰማራት በእነዚህ መከላከያዎች ላይ የሚሰነዘር ጥቃትን ይደግፋል" ሲሉ ለቢቢሲ ኒውስ ቻይኒዝ ተናግረዋል።

11 የአሜሪካ የጦር ጄት ተሸካሚ መርከቦች እያንዳንዳቸው 100,000 ቶን ግዙፍ የሚመዝኑ እና የኒውክሌር ጦር መሣሪያ የታጠቁ ናቸው።

 የቻይና ሁለተኛው ጦር ጄቶች ተሸካሚ መርከብ፣ ሻንዶንግ፣ የመርከቦች ላይ ጥቃት የምትፈፍም ጀልባን አጅቦ ሲንቀሳቀስ

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ልክ እንደ ሁለት የጦር ጄት ተሸካሚ መርከቦች ሁሉ ሻንዶንግም በናፍጣ የሚንቀሳቀስ ነው

ዶ/ር ቹንግ ፉጂያን የናፍጣ ሞተሮች ያላት መሆኑ እና ቻይና በአቅራቢያው ትላልቅ የባሕር ወደቦች የሌላት መሆኑ በድጋፍ ሰጪ መርከቦች በተደጋጋሚ አቅርቦት እንደሚያስፈልጋት እና ይህም የውጊያ አቅሟን በእጅጉ እንደሚገድበው ጠቁመዋል።

በጥቅምት 2025 በታተመው የፉጂያን ግምገማ ላይ የጃፓን ብሔራዊ የመከላከያ ጥናት ተቋም ባልደረባ አይታ ሞሪኪ "ብዙ የቴክኖሎጂ እና የሠራተኞች ፈተናዎች አሁንም አሉ" ሲሉ ጽፈዋል።

"በሌላ አነጋገር የፉጂያን እና የሌሎች የቻይና አውሮፕላን ተሸካሚዎች አጠቃላይ የውጊያ አቅም እና ልምድ አሁንም በተጨባጭ ጦርነት ውስጥ ተሳትፎ ከሚያውቀው የአሜሪካ ጦር ሠራዊት የተለየ ነው" ሲሉ ዶክተር ቹንግ ለቢቢሲ ኒውስ ቻይኒዝ ተናግረዋል።

የአሜሪካ ሪር አድሚራል ብሬት ሚትስ ለዋሽንግተን ፖስት በመስከረም 2025 "እነርሱ ሦስት (አውሮፕላን ተሸካሚዎች) አሏቸው፤ እኛ 11 አለን፤ እና ለአስርተ ዓመታት ያህል ይህ ኖሮን ያውቃል።"

የአሜሪካ ግዙፉ የጦር አውሮፕላን ተሸካሚ ዩኤስኤስ ጄራልድ አር ፎርድ በዓለም ላይ እጅግ ዘመናዊ የሆነ መርከብ ነው

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የአሜሪካ ግዙፉ የጦር አውሮፕላን ተሸካሚ ዩኤስኤስ ጄራልድ አር ፎርድ በዓለም ላይ እጅግ ዘመናዊ የሆነመርከብ ነው

የከፍተኛ የቴክኖሎጂ ሚሳኤሎች አቅምን ማሳደግ የአውሮፕላን ተሸካሚዎችን አጠቃላይ ወታደራዊ ጠቀሜታ እንዲቀንስ አድርጎታል።

በኤሌክትሮማግኔቲክ ካታፑልቶች የሚታገዙ መርከቦች ላይም ቢሆን አብራሪዎች አሁንም በማረፍ እና በመነሳት ወቅት በማዕበል ላይ በሚወዛወዝ የመርከቧ ወለል ላይ ለማረፍ አደገኛ የበረራ ክህሎቶችን መፈጸም ይጠበቅባቸዋል።

ዶክተር ናጋኦ "[ሰው አልባ] አውሮፕላኖች በኤአይ [ሰው ሠራሽ-አስተውሎት] ቴክኖሎጂ ከዘመኑ ሰው አልባ አውሮፕላኖች ተሸካሚዎች የበለጠ ወጪ ቆጣቢ እና ዋና ኃይል ይሆናሉ።"

ሆኖም ቻይና አራተኛውን የአውሮፕላን ተሸካሚ እየገነባች መሆኑን የሳተላይት ምስሎች ይጠቁማሉ።

መርከቦቹን ለማስፋፋት እና ባለሙያዎች እንደሚናገሩት የኒውክሌር ኃይል ተሸካሚዎች ለማምረት ዕቅድ ተይዟል።

ባለሙያዎቹ የአሜሪካ እና ቻይና የባሕር ላይ የጦር መሣሪያ ውድድር በቅርቡ እንደሚሆን ይተነብያሉ።

በታይፔ የሚገኘው የብሔራዊ መከላከያ እና ደህንነት ጥናት ተቋም ባልደረባ ጂያንግ ህሲን-ቢያኦ ለኒውዮርክ ታይምስ እንደተናገሩት "ዩናይትድ ስቴትስ አዳዲስ አውሮፕላን ተሸካሚዎችን እየገነባች ነው። ለረዥም ጊዜ የሚያገለግሉበትንም መንገድ እየፈተሸች ነው።"

አክለውም "ስጋቶቹ አንጻራዊ እና በሁለቱም ወገኖች በኩል ያሉ ናቸው፤ ቻይናም ሆነ አሜሪካ።"