ለ200 ቀናት ብቻ አሜሪካንን በፕሬዝዳንት የመሩት ጄምስ ጋርፊልድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በ19ኛው ክፍለ ዘመን የአሜሪካ 20ኛው ፕሬዝዳንት ጄምስ ጋርፊልድ ለአገራቸው ዕድገትን እና ተሃድሶን ለማምጣት ቃል ገቡ።
ነገር ግን ቃለመሃላ ፈጽመው መንበረ ሥልጣኑን ከተረከቡ ከአራት ወራት በኋላ በተተኮሰባቸው ጥይት ተገደሉ።
በርካቶች 20ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት አገሪቱ ካፈራቻቸው ምርጥ መሪዎች መካከል አንዱ ይሆናሉ ብለው ያምኑ ነበር።
በአሜሪካ የፕሬዝዳንቶች ታሪክ ውስጥ ስማቸው እምብዛም ሲነገር የማይሰማው አኚህ ግለሰብ ወደ ሥልጣን የመጡበት ወቅት በአሜሪካ ታሪክ ውስጥ ወሳኝ የሚባል ነው።
ነገር ግን በሥልጣን ላይ የቆዩት ለአጭር ጊዜ በመሆኑ ታሪካቸው ብዙ ሊሰነድላቸው እና ሊወራላቸው አልቻለም።
በአውሮፓውያኑ 1880 አሜሪካ መስቀለኛ መንገድ ላይ ቆማ ነበር።
በባርነት ተሽጠው የነበሩ ሰዎች ነጻነታቸውን ይጎናፀፉ ይሆን?
ለረዥም ጊዜ የቆየው የመንግሥት ሥራን ብቃት ካላቸው ባለሙያዎች ይልቅ ለታማኝ ደጋፊዎች የሚሰጠው ሥርዓት ይቀየር ይሆን?
በሪፐብሊካን ዓመታዊ ጉባዔ ላይ ጄምስ ጋርፊልድ እነዚህን ጥያቄዎች አንስተው ምላሽ ሰጥተዋል። የገቡትን ቃል ለመፈጸም ለሕዝቡ ቃል ገብተው ነበር።
የጄምስ ጋርፊልድን መሳጭ ንግግር የሰሙት የፓርቲው አባላት እኚህ ከኦሃዮ የመጡ የኮንግረስ አባል ዕጯቸው እንዲሆኑ ከመምረጣቸው በፊት ቆመው በማጨብጨብ ድጋፋቸውን ገልጸዋል።ጋርፊልድ ፓርቲው ያደረገውን ምርጫ ተቃውመዋል።
ለፕሬዝዳንትነት ለመወዳደር ፍላጎት አንደሌላቸውም አስታውቀዋል።
ነገር ግን ልክ እንደ አብርሃም ሊንከን ከድህነት ተነስተው ለከፍተኛ የፖለቲካ ሥልጣን መብቃታቸው፣ በሲቪል ጦርነት ወቅት በአንድነት ኃይሎች ወገን በመሆን የፈጸሟቸውው የጀግና ተግባራት ብቁ ዕጩ እንደሚሆኑ በብዙዎች ላይ እምነት አሳድረዋል።
በኅዳር 1880 የአሜሪካ 20ኛው ፕሬዝዳንት በመሆን ተመረጡ።
ከዚያ ቀጥሎ የሆነው ግን በአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ታሪክ ውስጥ እጅግ አዘሳዛኙ ነው።
ቃለ መሃላ ፈጽመው በሥልጣን ላይ አራት ወራት ወይም ለ200 ቀናት ብቻ እንደቆየ ጥይት ተተኩሶባቸው ሕይወታቸው አልፏል።
በእርግጥ ጋርፊልድ በተተኮሰባቸው ጥይት ሕይወታቸው ያለፈ የመጀመሪያው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት አይደሉም።
አብርሃም ሊንከን (በ1865) ዊሊያም ማክኪንሊ (በ1901) ጆን ኤፍ ኬኔዲ (በ1963) በተተኮሰባቸው ጥይት የተገደሉ የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች ናቸው።
ጋርፊልድ ባለ ብሩህ አእምሮ፣ ትሁት እና በመርኅ የሚመሩ ሙስናን የተዋጉ እና አገሪቱን ለማዘመን የታገሉ በመባል ይታወሳሉ።
በሕይወት ኖረው ቢሆን ኖሮ ከዚህ የበለጠ ያሳኩ ነበር ሲሉ የታሪክ ምሑራን ይከራከራሉ።
የጄምስ ጋርፊልድ ግድያ ምክንያት
በአውሮፓውያኑ ሐምሌ 2/1881 ጄምስ ጋርፊልድ ከቤተሰባቸው ጋር ወደ እረፍት ከመሄዳቸው በፊት በተማሩበት ኮሌጅ በተዘጋጀ የመልሶ መገናኛ መርሃ ግብር ላይ ተገኝተው ንግግር ለማድረግ ባልቲሞር እና ዋሺንግተን ዲሲ ወደሚገኘው ፖቶማክ የባቡርጣቢያ ሄደው ነበር።
ሁለት ሚኒስትሮቻቸው ብቻ ናቸው አብረዋቸው የነበሩት።
ከ16 ዓመታት በፊት ቀደም ብሎ የተፈጸመው ከአብርሃም ሊንከን ግድያ በኋላ እንኳ የደኅነንት ሠራተኞች አጀብ ለአሜሪካ ፕሬዝዳንት የተለመደ አልነበረም።
ወደ መቆያ ክፍል ሲገቡ ቻርለስ የተባለ ግለሰብ ከጀርባው በመምጣት ሁለት ጊዜ ተተኮሰባቸው። የመጀመሪያው ጥይት የጋርፊልድን እጅ ሲመታ "የፈጣሪ ያለህ ምንድ ነው?" ሲሉ ጮኹ።
ከዚያ ሁለተኛው ጥይት ወደ ጣፊያቸው ዘልቆ ገባ።
ጋርፊልድ ወደ ሆስፒታል በፍጥነት ሲወሰዱ ፖሊስ ጥቃት አድራሹን በቁጥጥር ስር አዋለ።
ቻርለስ ጋርፊልድን ተኩሶ ከመግደሉ በፊት መረጋጋት የራቀው ሰው ነበር።
ነገር ግን ለሚያሳያቸው አእምሮ መታወኮች በወቅቱ ወደነበሩ የአእምሮ ጤና ሕክምና ተቋማት ሄዶ አልታከመም።
ተኳሹ በተደጋጋሚ የሚሞክራቸው ሥራዎች ሁሉ ስኬት የተራቃቸው ነበሩ። የመጨረሻ ሙከራው ደግሞ በፖለቲካው መስክ ላይ ተንጠላትሎ ለመውጣት ያደረገው ጥረት ነበር።
ጋርፊልድ ለፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ሲወዳደሩ ደጋፊያቸው የነበረ ሲሆን፣ በዚህም የተነሳ እሾማለሁ እሸለማለሁ ብሎ ያስብ ነበር።
ምንም እንኳ የነበረው አስተዋጽኦ የድጋፍ ወረቀቶችን ከመበተን እና አነስተኛ ሰዎች በተሰበሰቡበት ጉባዔ ላይ ንግግር ከማድረግ ያለፈ ባይሆንም እርሱ ግን ለጋርፊልድ መመረጥ ወሳኝ ሰው እንደሆነ ራሱን ይቆጥር ነበር።
ስለዚህም ጋርፊልድ ዋይት ሐውስ ሲገቡ በአስተዳደራቸው ውስጥ ቦታ አገኛለሁ ብሎ ይጠብቅ ነበር።
ለወራት በቪየና ወይንም በፓሪስ የአሜሪካ ቆንስላ ውስጥ ቦታ ለማግኘት ጥሯል።
ሁለቱም ምኞቶቹ ሳይሳኩ ሲቀሩ ጋርፊልድ መሞት አለባቸው ሲል ወሰነ። ፈጣሪ ጋርፊልድ ለአገሪቱ ሲባል "መወገድ" አለባቸው ብሎ አንደነገረው አሰበ።
ለሳምንታት የፕሬዝዳንቱን አንቅስቃሴ ሲከታተል ከቆየ በኋላ በባቡር ጣቢያው መቆያ ክፍል ተገጣጠሙ።
ከጥቃቱ በኋላ ጋርፊልድ በቂ የሆነ ሕክምና ክትትል አላገኙም የሚል ቅሬታ የቀረበ ሲሆን ሕይወታቸውም በጥቃቱ የተነሳ አልፏል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ጄምስ ጋርፊልድ ማን ነበሩ?
ጄምስ ጋርፊልድ ከድሃ ቤተሰብ የተወለዱት በአውሮፓውያኑ ኅዳር 19/1831 ነው። በገጠራማው ኦሃዮ ያደጉት ጋርፊልድ አባታቸው የሞቱት ልጅ ሳሉ ነው።
ቤሳ ቤስቲን ያልነበራቸው እናታቸው ኤሊዛ ሁለት እህቶቻቸውን እና አንድ ወንድማቸውን ለብቻቸው አሳድገዋል።
ወጣቱ ጋርፊልድ ጠንካራ፣ ብሩህ፣ ታታሪ እና ራሱን ለማሻሻል ዘወትር የሚተጋ ነበር።
ከጉርምስና ዕድሜው ጀምሮ ራሱን ለማስተማር ሲል የተለያዩ ሥራዎችን ሠርቷል።
በስተመጨረሻም በ1856 ከዊሊያምስ ኮሌጅ ተመርቋል።
በኤክሌክቲክ ኢንስቲትዩት መምህር ሆነው ከማገልገል ጀምሮ በ26 ዓመታቸው ፕሬዝዳንቱ ለመሆን በቅተዋል።
በተለያዩ የትምህርት ዓይነቶች ልሂቅ የነበሩተ ጋርፊልድ በተመሳሳይ ሰዓት በአንድ እጃቸው ላቲን በሌላ እጃቸው ጥንታዊ ግሪክ መጻፍ ይችሉ ነበር ይባላል። በኋለኛው ሕይወታቸወም ፓይታጎረስ ቴረምን ያረጋገጡበትን ሥራቸውን አሳትመዋል።
ጋርፊልድ በመምህርነቱ ላይ ብዙም ሳይቆዩ ጠበቃ ከሆኑ በኋላ ፀረ ባርነት አቋም ያራምድ የነበረውን ሪፐብሊካን ፓርቲን በመቀላቀቀል ወደ ፖለቲካው ዓለም ገብተዋል።
በ1861 የእርስ በርስ ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ ወታደር ሆኑ።
ባርነትን አጥብቀው ከሚቃወሙ መካከል የሆኑት ጋርፊልድ ከአንድነት ኃይሎች ጋር ተሰልፈው ተዋጋ።
ከዚያ በኋላ ፕሬዝዳንት ሊንከን በአውደ ውጊያው ላይ በቂ ወታደራዊ መሪዎች መኖራቸውን እና በኮንግረስ ውስጥ ጠንካራ ሰዎች እንዲመጡ አንደሚፈልጉ በመግለጽ ስላበረታቷቸው የተወካዮች ምክር ቤት አባል ሆነው ተመርጠዋል።
ከ30ዎቹ የዕድሜቸው መጀመሪያ አንስቶ ለ17 ዓመታት ያህል የኮንግረስ አባል ሆነወ አገልግለዋል።
የበርካቶችን ቀልብ መሳብ የሚችሉ፣ ጥሩ ተናጋሪ የሆኑት ጋርፊልድ ሁለቱንም የፖለቲካ ጎራዎች ያለችግር አነጋግሮ መግባባት የሚችሉ ፖለቲከኛ ነበር ይባላሉ።
በ1870ዎቹ ጋርፊልድ የምክር ቤቱ የሪፐብሊካን መሪ የነበሩ ሲሆን በ1880 ደግሞ ለሴኔት ተመርጠዋል።
ለሴኔት እንደተመረጡም የሪፐብሊካን ፓርቲ አባላት ፕሬዝዳንታዊ ዕጩ ሆኖ አንዲወዳደሩ ድጋፋቸውን ሰጧቸው። ከዚያም የአሜሪካ 20ኛው ፕሬዝዳንት ሆኖ ለመመረጥ ቻሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የጄምስ ጋርፊልድ አሟሟት
ጋርፊልድ ላይ የተተኮሰው ጥይት ወዲያውኑ አልገደላቸውም።
በጥይት ከተመቱ በኋላ በዋይት ሐውስ ሕክምና ባለሙያዎች ክትትል ስር ለ11 ሳምንታት ቆይተዋል።
ሕክምና ባለሙያዎች ከሕመማቸው አንዲያገግሙ ከማድረግ ይልቅ እንዲባባስ አድርገዋል በሚል ይከሰሳሉ።
በጀርባቸው በኩል የገባውን ጥይት ለማውጣት የሞከሩበት መንገድ ጀርሞችን ወይንም መበከልን ከግምት ያላስገባ ነበር ተብሏል።
በዚህም የተነሳ ጋርፊልድ በኢንፌክሽን ተጠቅተው ራሳቸውን እንዲስቱ ምክንያት ሆኗል።
ከጊዜ ወደ ጊዜም ቁስላቸው እየሰፋ መጣ። የሕክምና ቡድኑ ከሞቃታማዋ ዋሺንግተን ወደ ቀዝቃዛዋ ኒው ጀርሲ ወስደው ሕክምናቸውን ቀጠሉ።
በዚያም በጥይት ከተመቱ ከ80 ቀናት በኋላ መስከረም 19/1881 በተወለዱ በ49 ዓመታቸው ሕይወታቸው አለፈች።
ገዳዩም ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ ሰኔ 1882 በስቅላት እንዲቀጣ ተደርጓል።















