በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ አንድ ወጣት የኤሌክትሪክ ትራንስፎርመር ላይ ወጥቶ አልወርድም በማለቱ ለመብራት መቋረጥ ምክንያት ሆነ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ማሻ ከተማ አንድ የ22 ዓመት ወጣት የኤሌክትሪክ ትራንስፎርመር ላይ ወጥቶ አልወርድም በማለቱ ለከተማዋ የመብራት አገልግሎት ምክንያት ሆኖ በቁጥጥር ስር መዋሉን የከተማዋ ፖሊስ አዛዥ ለቢቢሲ ገለፁ።
ድርጊቱ የተፈፀመው ረቡዕ ኅዳር 17/2018 በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሸካ ዞን፣ ማሻ ከተማ ውስጥ ነው።
በዕለቱ በግምት ከቀኑ 7፡00 ሰዓት ላይ አንድ "የአእምሮ ጤና እና ሌላ ተጓዳኝ ችግር" አለበት የተባለ ወጣት በከተማዋ በሚገኝ የኤሌክትሪክ ትራንስፎርመር ላይ ወጥቶ ለመውረድ ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል።
የአካባቢው ማኅበረሰብ እና የአገር ሽማግሌዎች ተሰብስበው የወጣቱን ሕይወት ለመታደግ ከፍተኛ ኃይል ካለው ትራንስፎርመር ላይ እንዲወርድ መለመን ጀመሩ።
ነገር ግን ወጣቱ የአገር ሽማግሌዎችን እና የአካባቢውን ማኅበረሰብ ልመናና ማሳመን ችላ ብሎ ትራንስፎርመሩ ላይ ተቀምጦ ቀርቷል።
የማሻ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ረዳት ኢንስፔክተር ብሩክ ታደሰ "የአካባቢው ሽማግሌዎች እና ነዋሪዎች ልጁ እንዲወርድ ቢጠይቁትም አሻፈረኝ ብሏል" ይላሉ።
ከዚያ በኋላ ከአቅማቸው በላይ በመሆኑ ፖሊስ መጠራቱን የከተማዋ ፖሊስ አዛዥ ተናግረዋል።
ፖሊስ ከከተማዋ ነዋሪ ጥሪ ከደረሰው በኋላ አባሎቹን ወደ ቦታው ቢልክም ግለሰቡ ግን "አልወርድም" ብሎ ማስቸገሩን ተናግረዋል።
"ከ20 እና 30 ደቂቃ" ማግባባት እና ማባበል በኋላ ፖሊስ ግለሰቡን ማውረዱን እና በቁጥጥር ስር ማዋሉን አዛዡ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ረዳት ኢንስፔክተር ብሩክ ታደሰ "ፖሊስ ከመጣ በኋላም 'አልወርድም' እያለ ነበር" በማለት በአካባቢው የኤሌክትሪክ አገልግሎት በዚህ የተነሳ መቋረጡንም ተናግረዋል።
ልጁ ለምን አልወርድም እንዳለ ሲጠየቁም "ተስፋ ቆርጫለሁ፤ ከእንግዲህ በኋላ ሕይወቴን ማጥፋት አለብኝ" እያለ ይናገር ነበር ሲሉ ሁኔታውን አስረድተዋል።
ወጣቱን ከትራንስፎርመሩ ላይ እንዲወርድ ከተደረገ እና ከተረጋጋ በኋላ የፖሊስ አባላት ወደ ፖሊስ ጣቢያ ወስደው ምርመራ ማካሄዳቸውንም ተናግረዋል።
"ልጁን ተይዘን ወደ ፖሊስ ጣቢያ ወስደነዋል፤ ምርመራም ተጀምሯል፤ ሕጋዊ ሂደቶችን ተከትሎ ውሳኔ ይሰጣል።"
ፖሊስ ግለሰቡን ካወረደ እና በቁጥጥር ሥር ካዋለ በኋላ ምርመራ በማድረግ ዛሬ ሐሙስ ኅዳር 18 2018 ዓ.ም. "የክስ ሂደት ተጀምሯል" ሲሉ ተናግረዋል።
"ለሰው ልጅ ቅድሚያ መስጠት አስፈላጊ በመሆኑ ወደ ጤና ተቋም እንዲላክ ከሚመለከተው ክፍል ጋር እየተነጋገርን ነው" ሲሉም አክለዋል።
ረዳት ኢንስፔክተር ብሩክ "በአካባቢው አደጋ ሊፈጠር ይችላል በሚል ስጋት ኤሌክትሪክ ወዲያውኑ አልተለቀቀም" በማለት ችግሩ በተከሰተበት ከተማ የመብራት አገልግሎት "እስከ ምሽቱ ሁለት ሰዓት" ከተቋረጠ በኋላ ዳግም መለቀቁን ተናግረዋል።















