በሜኒሶታ የሚኖሩ ሶማሊያዊ-አሜሪካውያን፡ "እኔን የሚመስሉ ሰዎች በፍርሃት ተሸብበዋል"

ሶማሊያዊ-አሜሪካዊት ቃውሰር መሐመድ

የፎቶው ባለመብት, Abdilatif Hassan

የምስሉ መግለጫ, ቃውሰር መሐመድ

በሜኒሶታ የሚኖሩ ሶማሊያዊ-አሜሪካውያን የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ንግግርን ተከትሎ ስጋት ውስጥ ገብተዋል።

ትራምፕ ሶማሊ-አሜሪካውያንን በሚነቅፉ ንግግሮቻቸው ቀጥለዋል። ቢቢሲ ያነጋገራቸው የማኅበረሰብ መሪዎች እነዚህን ንግግሮች ተከትሎ "ፍርሃት መንገሡን" ገልጸዋል።

ትራምፕ፤ ሶማሊያውያን ስደተኞች በአሜሪካ እንዲኖሩ እንደማይፈልጉ እና አገራቸው "ቆሻሻ መቀበል ከቀጠለች ወደተሳሳተ መንገድ እንደምትገባ" ተናግረዋል።

በሜኒሶታ የሚገኘው ሲዳር-ሪቨርሳይድ ሰፈር የማኅበረሰብ ኮሚቴ ዋና ዳይሬክተር አጅ አወድ "በአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዒላማ መደረግ ጥሩ ስሜት አይፈጥርም" ብለዋል።

የሚኖሩበት ሰፈር የሚገኝበት ከተማ የበርካታ ሶማሊያውያን መኖሪያ በመሆኑ 'ትንሿ ሞቃዲሹ' በመባል ይታወቃል።

በሜኒሶታ ሰነድ አልባ ስደተኞች ላይ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑ መሰማቱ የማኅበረሰቡን ስጋት አባብሶታል።

መንግሥት እየወሰደ ባለው እርምጃ ምክንያት በቀጣይ ሳምንት የማኅበረሰብ ኮሚቴው ሊያካሂድ ያቀደውን ዓመታዊ ጉባዔ ሊሰርዝ ይችላል።

አጅ አወድ "ለዓመታት የአሜሪካ ዜጋ ሆነው ብዙም እንግሊዘኛ የማይችሉ ሰዎች የበለጠ ተጋላጭ ናቸው። የተለየ የንግግር ቅላጼ ስላለን ብቻ አሜሪካዊነታችን አይፋቅም" ይላሉ።

ትራምፕ ሶማሊያውያንን የሚያጣጥሉ አስተያየቶች ሰጥተዋል። "እውነቱን ልንገራችሁ. . . እዚህ አገር እንዲኖሩ አልፈልግም። አገራቸው የማትረባ የሆነችው ያለ ምክንያት አይደለም" ብለዋል።

የማኅበረሰብ መሪው እንደሚሉት፤ እነዚህ አስተያየቶች "አደገኛ" ሲሆኑ "ፕሬዝዳንት አሜሪካውያን ላይ ጥቃት ይሰነዝራል" ተብሎም አይጠበቅም።

ትራምፕ በዋይት ሐውስ ንግግር ሲያደርጉ የሜኒሶታ አገረ ገዢ ቲም ዋልዝ በማኅበራዊ ድጋፍ ፕሮግራም አማካኝነት መጠነ ሰፊ ማጭበርበር ፈጽመው እንደሆነ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ ሶማሊያውያንን በጽኑ ተችተዋል።

በሜኒሶታ የሚገኘው ሲዳር-ሪቨርሳይድ ሰፈር የማኅበረሰብ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አጅ አወድ

የፎቶው ባለመብት, Aj Awer

የምስሉ መግለጫ, በሜኒሶታ የሚገኘው ሲዳር-ሪቨርሳይድ ሰፈር የማኅበረሰብ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አጅ አወድ
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በኮቪድ-19 ወቅት ለልጆች ምግብ ለማቅረብ በሚል የሜኔሶታን መንግሥት አጭበርብረዋል የተባሉ ሰዎችን የፌደራል ዐቃቤ ሕግ ከስሷል።

የቀድሞው የሜኔሶታ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ መርማሪ ኬሽ ሜጋን እንዳሉት፤ በዚህ የማጭበርበር ክስ ብዙ ሶማሊያዊ ስደተኞች ስማቸው ተነስቷል። ተፈጽሟል በተባለው ማጭበርበር የሜኔሶታ ግዛት በሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ ማጣቱም ተገልጿል።

በማጭበርበሩ ስማቸው የተነሳው ሰዎች ከአጠቃላዩ የሜኔሶታ ሶማሊያዊ ነዋሪዎች አንጻር ውስን ቁጥር ነው ያላቸው።

ሆኖም ግን ትራምፕ ማኅበረሰቡን በጅምላ በመፈረጃቸው ተወቅሰዋል።

የሜኔሶታ ግዛት "ሕገ ወጥ ገንዘብን ሕጋዊ መስመር የማስገባት ወንጀል ማዕከል ሆናለች። በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሶማሊያውያን አገራችንን እየመዘበሩ ነው" ሲሉ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ጽፈዋል።

የአሜሪካ መንግሥት፤ የሜኒሶታ ግዛት የሕዝብ ገንዘብ ለሶማሊያው ታጣቂ ቡድን አልሻባብ ይሸጋገራል በሚል በቀረበው ክስ ላይ ምርመራ መጀመሩን አስታውቋል።

የአሜሪካ ግምጃ ቤት እንዳለው፤ ከአሜሪካዋ ግዛት የሚላከው የሕዝብ ገንዘብ ወደ ታጣቂው ቡድን መሻገሩን በተመለከተ ምርመራ ከፍቷል።

ግምጃ ቤቱ በኤክስ ገጹ ላይ ባወጣው ጽሑፍ እንዳመለከተው ምርመራው የተጀመረው ትራምፕ በሰጡት ትዕዛዝ ነው።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንን እና አገረ ገዢው ቲም ዋልዝን "የአሠራር ክፍተት" በመፍጠር ከስሷል።

ትራምፕ ከቀናት በፊት የአሜሪካው ወግ አጥባቂ ሚዲያ 'ጀስት ዘ ኒውስ' ያወጣውን ዘገባ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው አጋርተዋል።

ዘገባው "ሊበራል ፕሮግራሞችን ለማስተግበር በሜኒሶታ በሶማሌ ስደተኞች የተፈጸመ ትልቅ ምዝበራ በዴሞክራት ፓርቲ ከሽፏል" ይላል።

የተመዘበረው ገንዝብ ወደ ኬንያ እና ሶማሊያ እንደተላከ እና ይህም ከአል ቃይዳ ጋር ትስስር ወዳለው አል ሸባብ እንደደረሰ ዘገባው ይጠቁማል።

አገረ ገዢው ቲም ዋልዝ ስለቀረቡት ክሶች ተጠይቀው "አንድ ማኅበረሰብ ባጠቃላይ በተመሳሳይ መንገድ አትፈርጁ። ማስረጃ በሌለው ክስ እነሱን ሰይጣናዊ ገጽታ ማላበስ ለአደጋ የሚያጋልጥ ነው" ብለዋል።

"ልትረዱን፣ ወንጀለኞቹን ልታጋልጡ እና ገንዘቡ የት እንደገባ ልታጋልጡ ከፈለጋችሁ ግን ጥያቄያችሁን እንቀበላለን" ሲሉም አክለዋል።

"እኔን የሚመስሉ ሰዎች በፍርሃት ተሸብበዋል"

ጀማል ኦስማን የሚኒያፖሊስ ከተማ ካውንስል አባል ናቸው።

በ14 ዓመታቸው አሜሪካ የገቡት ጀማል አሜሪካዊ ሲሆኑ፤ ከሲቢኤስ ጋር ባደረጉት ቆይታ "እኔን የሚመስሉ ሰዎች አሁን ላይ በፍርሃት ተሸብበዋል" ብለዋል።

የትራምፕ አስተዳደር ሶማሊያዊያንን በተመለከተ ስለ ሰነዘሩትን ክስ የተጠየቁት ጀማል "ማኅበረሰባችን ተበሳጭቷል። ሰዎች ወንጀል ቢሠሩም ለግለሰቦች ጥፋት አጠቃላይ ማኅበረሰቡ መወቀስ የለበትም" ብለዋል።

የትራምፕ አስተዳደር ቀውስ ውስጥ ናቸው ካላቸው አገራት ለመጡ ጥገኝነት ጠያቂዎች በጊዜያዊነት ለስደተኞች ከለላ የሚሰጠውን አሠራር (Temporary Protected Status ወይም TPS) አቋርጧል።

ውሳኔው የሚመለከተው ከአሜሪካ እንዲባረሩ የተወሰነባቸው ሰዎችን እንደሆነ አስተዳደሩ ገልጿል።

ከ80 ሺህ በላይ ሶማሊያውያን በሚኖሩባት ደቡብ ሚኒያፖሊስ የምትገኘው ቃውሰር መሐመድ፤ የአሜሪካ የስደት እና ጉምሩክ መሥሪያ ቤት (አይስ) ሠራተኞች "እየመጡ ነው" ብላለች።

"እንቅስቃሴ ጀምረዋል። መንገድ ላይ ሰዎችን እያስቆሙ ስለ መኖሪያ ፈቃዳቸው ይጠይቃሉ። እየተፈጸመ ስላለው ነገር መረጃም አልተሰጠም" ስትልም አክላለች።

አብዛኞቹ ነዋሪዎች አስፈላጊው መታወቂያ እንዳላቸው የጠቀሰችው ነዋሪዋ "ፍርሃታችን ስህተት እንዳይፈጠር ነው" በማለት ስጋቷን ገልጻለች።

የስደት እና ጉምሩክ መሥሪያ ቤትን የሚያስተዳድረው የአገር ውስጥ ደኅንነት ቃል አቀባይ፤ ሰዎች በዘራቸው ምክንያት ዒላማ መደረጋቸውን አስተባብለዋል።

የተቋሙ ተባባሪ ጸሐፊ ቲሪሻ ማጉሊን "የአይስ ባልደረቦች በየቀኑ በመላው አገሪቱ ሕግ ያስከብራሉ። አንድ ሰው ዒላማ የሚደረገው በዘሩ ወይም በማንነቱ ሳይሆን እዚህ አገር በሕገ ወጥ መንገድ መግባቱ ነው" ብለዋል።

ቃውሰር እንደተናገረችው፤ የትራምፕን ንግግር ተከትሎ የማኅበረሰብ መሪዎች ስደተኞችን ለመከላከል የሚያደርጉትን ጥረት ከፍ አድርገዋል።

ሞናራካ የተባለው ተቋም ሰዎች እንዴት መብታቸውን ማስከበር እንደሚችሉ ሥልጠና እየሰጠ ነው።

የድንገተኛ ጊዜ ስልክ ቁጥር በማዘጋጀት እና የጽሑፍ መልዕክት መለዋወጫ ቡድን በመፍጠርም ቅድመ ጥንቃቄ እያደረጉ ይገኛሉ።

"ሁሉም ሰው በጥንቃቄ ነው የሚንቀሳቀሰው። ፍርሃት አለ ወይ? ምንም ጥያቄ የለውም። ግን ማናችንም ፈርተን አንደበቅም" ስትል ቃውሰር ተናግራለች።