ቤቢ ሻርክ፡ እንዴት የ90 ሴኮንድ ቪዲዮ የ400 ሚሊዮን ዶላር ኩባንያን ፈጠረ?

የፒንክፎንግ ኩባንያ አሻንጉሊቶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ኪም ሚን-ሶክ በሰኔ 2008 ዓ.ም. የ90 ሴኮንድ ርዝማኔ ያለው የሕጻናት መዝሙር ዩቲዩብ ላይ እንዲጫን ሲያደርግ ምን ዓይነት ስኬት ላይ ሊያደርሳቸው እንደሚችል ምንም ግምት አልነበረውም።

መዝሙሩ በመላው ዓለም የሚገኙ ሕጻናት በጋራ ተስማምተው ያዘጋጁት ዝማሬ እስኪመስል ድረስ እጅጉን ተደምጧል። መዝሙሩ 16 ቢሊዮን እይታ በማግኘት ዩቲዩብ ላይ ከፍተኛ ተመልካች ያገኘ ቪድዮ ሆኗል።

ይሄ መዝሙር አስደናቂው 'ቤቢ ሻርክ' ነው።

የቤቢ ሻርክ ስኬት የሕጻናትን ቀልብ መግዛቱ እና በመላው ዓለም የሚገኙ አዋቂ ሰዎች እስከሚሰለቻቸው ድረስ እንዲያዳምጡት መገደዳቸው ብቻ አይደለም። የመዝሙሩ ፈጣሪ የሆነው 'ፒንክፎንግ' የተባለው ኩባንያ በመቶ ሚሊዮን ዶላሮች ዋጋ የሚያወጣ የሚዲያ ተቋም እንዲሆንም አስችሎታል።

የፒንክፎንግ ዋና ስራ አስፈጻሚ ኪም፤ "ከለቀቅናቸው ሌሎች ይዘቶች በተለየ መልኩ ይወጣል ብለን አልጠበቅንም ነበር" ሲል በደቡብ ኮርያ መዲና ሴኡል በሚገኘው የድርጅቱ ዋና መስሪያ ቤት ለቢቢሲ ተናግሯል።

"መለስ ብዬ ሳየው ግን፤ የዓለም አቀፍ ጉዟችንን መንገድ ጠረገ ትልቅ ምዕራፍ ነበር" ይላል።

በቤቢ ሻርክ ስኬት የተቃናው የፒንክፎንግ ጉዞ ማክሰኞ ዕለት መዳረሻውን በደቡብ ኮርያ የአክስዮን ሽያጭ ገበያ አድርጓል። የኩባንያው አክስዮን ለሽያጭ በቀረበበት መጀመሪያው ዕለት ዋጋው በ9 በመቶ ጨምሯል። ይህም የኩባንያው አጠቃላይ ዋጋ ከ400 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንዲሆን አድርጓል።

የፒንክፎንግ ዋና ስራ አስፈጻሚ ኪም ሚን-ሶክ የኩባንያው አክስዮን ለገበያ መቅረቡን ሲያበስር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የፒንክፎንግ ዋና ስራ አስፈጻሚ ኪም ሚን-ሶክ የኩባንያው አክስዮን ለገበያ መቅረቡን ሲያበስር

'ደመወዝ ይከፈለናል ብለን አልጠበቅንም'

'ስማርትስተዲ' በሚል ስያሜ በ2002 ዓ.ም. የተመሰረተው ኩባንያው፤ እስከ 12 ዓመት ዕድሜ ላላቸው ሕጻናት የዲጂታል ይዘቶችን ሲሰራ ቆይቷል።

የነበሩት ሠራተኞች ሦስት ብቻ ነበሩ። ከዚህ ውስጥ ሁለቱ ዋና ስራ አስፈጻሚው ኪም እና የቴክኖሎጂ ዘርፍ ዋና አስፈጻሚው ዶንግዉ ሰን ናቸው።

"ቢሮው በጣም ጠባብ ነበር፤ ከዚህም እንኳ ያንስ ነበር" ሲል ቃለ መጠይቁን በስልክ ለማድረግ ቁጭ ካለበት የኮንፈረንስ ክፍል ጋር አነጻጽሮታል።

ኩባንያው ትንሽ የነበረ ከመሆኑ የተነሳ "በወቅቱ ደመወዝ እንኳ [ይከፈለናል ብለን] አልጠበቅንም ነበር" ሲል አነሳሳቸውን አስታውሷል።

ኩባንያው በ2014 ዓ.ም. ስያሜውን የቀየረው ከዚህ ቀደም በተለቀቀ ይዘት ላይ ካለ ተጫዋች የቀበሮ ገጸ ባህሪ በመነሳት ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ኩባንያው በ2014 ዓ.ም. ስያሜውን የቀየረው ከዚህ ቀደም በተለቀቀ ይዘት ላይ ካለ ተጫዋች የቀበሮ ገጸ ባህሪ በመነሳት ነው

ፒንክፎንግ እዚህ የደረሰው በርካታ ዋና ዋና ማሻሻያዎች እየተገበረ ነው። ትኩረቱን ሕጻናት ላይ ማድረግ ከእነዚህ አንዱ ነበር።

እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሱት የሠራተኞች ብዛት ወደ 100 ገደማ በደረሰበት ጊዜ ነው። በዚህ ወቅት የድርጅቱ ዋነኛ ትኩረት ቀላል፣ ትምህርትን መሠረት ያደረጉ ጨዋታዎች እና ይዘቶችን መፍጠር ሆነ። "የዛኔ ነበር ቤቢ ሻርክ መጣው" ሲል ኪም ይናገራል።

ኩባንያው አሁን የሚጠራበትን ፒንክፎንግ የሚል ስያሜ የያዘው በ2014 ዓ.ም. ነው። ስያሜው የመጣው ቀደም ብለው ለቅቀውት የነበረ የካርቱን ቪዲዮ ላይ ካለ አንድ ተጫዋች እና ነገሮችን የሚመረምር የቀበሮ ገጸ ባህሪ ነው።

ፒንክፎንግ በአሁኑ ሰዓት በቶኪዮ፣ ሻንጋይ እና ሎስ አንጀለስ በከፈታቸው ቢሮዎቹ 340 ገደማ ሠራተኞች አሉት።

ያልታሰበው ቤቢ ሻርክ

ቤቢ ሻርክ የሚለው መዝሙር በአውሮፓውያኑ 1970ዎቹ አሜሪካ ውስጥ እንደተፈጠረ ይታመናል። ልጆች ትምህርት በሚዘጋበት ወቅት ጫካ መሰል ቦታዎች ውስጥ እየተጫወቱ እና የተለያዩ ተግባራትን እየፈጸሙ በሚያሳልፉበት 'ሰመር ካምፕ' ውስጥ ሕጻናት ይዘምሩት እንደነበር ይነገራል።

"ቤቢ ሻርክ ዱ ዱ ዱ ዱ ዱ ዱ" የሚለው የመዝሙሩ ክፍል "ለሕጻናት ማራኪ" እንደሆነ ሲንጋፖር በሚገኘው ናንያንድ ቴክኖሎጂካል ዩኒቨርሲቲ የሚዲያ ተንታኝ የሆኑት ኬቨን ቺው ይናገራሉ። ለአዋቂዎች ደግሞ "አናዳጅ" ሊሆን እንደሚችልም ያክላሉ።

የኩባንያው ዋና ስራ አስፈጻሚ ኪምም መዝሙሩ ምን ያህል ቀልብን እንደሚገዛ ይረዳል። "የኬ-ፖፕ ዘፈን ዓይነት ነው። በጣም ፈጣን፣ የሙዚቃ ምቱን የጠበቀ (rhythmical) እና ሱስ የሚያሲዝ ነው" ይላል። የዜማ ቅኝቱ ላይ ያለው "የድግግሞሽ ድምጽ" ልጆች በቀላሉ እንዲያስታውሱት እንደሚያደርግም ያክላል።

አሁን የዓለም ሕጻናትን ቀልብ የገዛ ቤቢ ሻርክ ግን እንደተለቀቀ ተወዳጅነትን አላገኘም ነበር። ትኩረት የተሰጠው በደቡብ ምሥራቅ እስያ በተካሄደ የሕጻናት ኹነት ላይ የመዝሙሩ ዳንስ ከቀረበ በኋላ ነው።

ከዚህ በኋላ ሕጻናት እና አዋቂዎች እየደነሱበት የሚያሳዩ ቪዲዮች መሰራጨት ጀመሩ፤ የዛኔ 'ቫይራል' ወጣ።

ከቤቢ ሻርክ መዝሙር የተወሰደ ምስል

የፎቶው ባለመብት, Pinkfong / YouTube

የኩባንያው ሠራተኞች በዚህ ተነሳ የመዝሙሩ የተመልካቾች ቁጥር በፍጥነት እየጨመረ መምጣቱን በተመለከቱበት ወቅት ፒንክፎንግ ቢሮ ውስጥ የነበረው ሁኔታ "የፌስቲቫል ዓይነት ስሜት" ያለው እንደነበር ያስታውሳል።

በኅዳር 2013 ዓ.ም. ደግሞ ቤቢ ሻርክ በዩቲዩብ ከፍተኛ ዕይታ ያለው ቪዲዮ የሚለውን ስያሜ ያዘ።

መዝሙሩ በተለቀቀባቸው የመጀመሪያዎቹ ዓመታት ላይ ከኩባንያው ገቢ ግማሽ ያህሉ ይመጣ የነበረው ከቤቢ ሻርክ ነበር። ይህም አዲስ ይዘቶችን እንዲሰሩ እንዲሁም ቤቢ ሻርክን ከመዝሙር ውጪ በሌሎች መንገዶችም ለገበያ እንዲያቀርቡ (merchandise) አስችሏቸዋል።

በ2011 ዓ.ም. ግን ፒንክፎንግ የቤቢ ሻርክ ሲሰራ አንዲት አሜሪካዊ የሙዚቃ አቀናባሪ ስራን አስመስሎ በመቅዳት ክስ ተመስርቶበታል።

ኩባንያው መዝሙሩ የተገኘው ከድሮ የሕዝብ መዝሙር እንደሆነ ከተከራከረ በኋላ የደቡብ ኮርያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ክሱን ውድቅ አድርቅ አድርጎታል።

በፍርድ ቤት አሸናፊ መሆናቸው የኩባንያው አክስዮን ለሽያጭ በቀረበበት ወቅት ዋጋው ከፍ እንዲል ምክንያት መሆኑን ይናገራል። አክስዮኑን ለመሸጥ የሚያስችላቸውን ማመልከቻ የሞሉት የፍርድ ውሳኔው ከመነገሩ በፊት እንደነበረም አክሏል።

ኩባንያው ከቤቢ ሻርክ ውጪ ለሌላ ተወዳጅ መዝሙር መስራት ይችል ይሆን?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ፒንክፎንግ በስሩ ያስጀመራቸው 'ቤቢፊን' እና 'ሲሉክ' የተሰኙት የሕጻናት ይዘቶች በፍጥነት እያደጉ ነው። ይህም ቢሆንም ኩባንያው የስኬቱ መሠረት የተንጠለጠለው ቤቢ ሻርክ ላይ እንዳልሆነ ማስመስከር እንደሚጠበቅት በኮርያ ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስ መምህር የሆኑት ሚን ጀንግ ኪም ያብራራሉ።

የኩባንያው ዒላማ አንድ ቪዲዮን ደጋግመው የማየት ልምድ ያላቸው ሕጻናት መሆናቸው ትልቅ እድል መሆኑንም ያስረዳሉ።

ኪም ሚን-ሶክ፤ ኩባንያው ከቤቢ ሻርክ ባሻገር ማደግ እንደሚችል ይከራከራል። በአሁኑ ሰዓት ከፒንክፎንግ ገቢ ውስጥ ሩብ ያህሉ የሚመጣው ከቤቢ ሻርክ ነው። ኋላ የተጀመረው ቤቢፊን በፍጥነት ተወዳጅነት በማግኘቱ የኩባንያውን 40 በመቶ ገቢ እያስገኘ ነው።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው አንድ ወላጅ ስለ ፒንክፎንግ ቪዲዮዎች የሚሰማቸው ስሜት ድብልቅ እንደሆነ ገልጸዋል።

የሁለት ልጆች አባት የሆኑት ሳሌም ናሽፍ፤ የኩባንያው ቪዲዮዎች የአስተማሪነት ይዘት ያለውን ጥራት እንደሚያደንቁ ይናገራሉ። ባለቤታቸው ግን ቤቢ ሻርክ "ለልጆች እጅጉን አነቃቂ ነገር የበዛበት" ነው ብላ ታስባለች።

ወደዱም ጠሉ ግን ቤቢ ሻርክ የሚያመልጡት መዝመር አልሆነም። በቅርቡ ሦስተኛ ዓመቷን የምትይዘው ልጃቸው ልደቷ የሚከበረው የቤቢ ሻርክ ምስሎች፣ ቅርጾች እና አልባሳት ባሸበረቀ ድግስ ነው።

ፒንክፎንግ ከዚህ በኋላ የቤቢ ሻርክ አይነት የንግድ ስኬት የሚያስገኙ ገጸ ባህሪዎችን መፍጠር ይችል እንደሆነ ግልጽ አለመሆኑን ኪም ይናገራል።

ኩባንያው "ቴክኖሎጂን መሠረት" ያደረገው ይዘት ፈጣሪ የመሆን ዕቅድ አለው። ወደፊት የሚቀርጻቸውን ፕሮጀክቶች ተመልካቾች ምን ዓይነት ይዘቶችን እንደሚወዱ በመመልከት እና ሌሎች ዳታዎችን በመጠቀም እንደሚነድፍ ጠቅሰዋል።

እንደ ኪም ገለጻ ከሆነ ፒንክፎንግ "በርካታ ይዘት ፈጣሪዎች የሚያልሙትን" ግብ አሳክቷል። አሁን ደግሞ ኩባንያው በአንድ ስራ ታይቶ የሚጠፋ እንዳልሆነ አክስዮኑን ለገዙት ባለሀብቶች ማረጋገጥ ይጠበቅበታል።