የሆርሞኖች መዋዠቅ የሚያስከትለው የስሜት ነውጥ ለምን በሴቶች ላይ ይበረታል?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሰውነታችን በአግባቡ የሚሠራው በሆርሞኖች አማካኝነት ነው። አንዳንዴ ግን አካላዊ እና አእምሯዊ ጤናችን ላይ ጫና ያሳድራሉ።
አእምሮ ላይ በዋነኛነት ተጽዕኖ የሚያሳድሩት ኒውሮትራንስሚተርስ (neurotransmitters) የተባሉ ኬሚካሎች ናቸው።
ሆርሞኖችም አእምሮ ላይ ጫና እንደሚያሳድሩ ሳይንቲስቶች ደርሰውበታል።
እንደ ድባቴ እና ጭንቀት ላሉ ሕመሞች መድኃኒት ለመስጠት ሙከራዎች መደረጋቸውን ቀጥለዋል።
ሆርሞን የሚመነጨው ከሰውነት ክፍሎች፣ ከዕጢ እና ከስብ ነው። የደም ሕዋስ ውስጥ ገብቶ በመላው ሰውነት ይዘዋወራል።
ለሰውነት አንድን ተግባር እንዲፈጽም ትዕዛዝ የሚተላለፈው በዚህ መንገድ ነው።
ለምሳሌ ኢንሱሊን ሆርሞን ጉበት እና ጡንቻ ከልክ ያለፈ ግሉኮስን አምክነው በግላኮጅን መልክ እንዲያከማቹ መልዕክት ያስተላልፋል።
ሳይታይ ሰውነትን የሚቆጣጠረው ሆርሞን
በሰውነታችን ውስጥ ከ50 በላይ ሆርሞኖች በሳይንቲስቶች ተገኝተዋል።
እነዚህም ዕድገት፣ ልጅ መውለድ እና መተኛትን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ የሰውነት እንቅስቃሴዎችን ይቆጣጠራሉ።
በካናዳው ኦቶዋ ዩኒቨርስቲ የሥነ ልቦና መምህር ናፊሳ ኢስማኤል "ሆርሞን ስሜት ላይ ጫና ያሳድራል" ይላሉ።
በአእምሮ ውስጥ ከሚመረቱ ኒውሮትራንስሚተሮች ጋር በመሆን ሆርሞኖች ሰውነታችንን ይቆጣጠራሉ።
ሕዋሳት ሲሞቱ እና አዲስ ኒውሮን ሲፈጠርም የሚቆጣጠሩት ሆርሞኖች ናቸው።
ድባቴ፣ ጭንቀት እና አስደንጋጭ ሁኔታን ተከትሎ የሚመጣ የስሜት መናወጥ (ፒቲኤስዲ) የሆርሞን ዝውውር ከፍ ሲል ይባባሳሉ።
ይህም በይበልጥ በሴቶች ላይ ይስተዋላል።
የታዳጊ ሴቶች እና ወንዶች የድባቴ ተጋላጭነት መጠን እኩል ነው።
ዕድሜ ሲጨምር ግን የሴቶች ተጋላጭነት በእጥፍ ይጨምራል።
ሆርሞን በሴቶች ስሜት ላይ የሚያመጣው ለውጥ ጉልህ ነው።
የወር አበባ ከመምጣቱ ከቀናት እና ከሳምንታት አስቀድሞ የኤስትሮጅን እና ፕሮጀስትሮን መጠን ይቀንሳል።
በዚህ ምክንያት ድካም፣ ሐዘን፣ ጭንቀት እና ቁጣ ይጨምራል።
ከወር አበባ ጋር የተያያዘ የስሜት መዋዠቅ (premenstrual dysphoric disorder ወይም PMDD) የሚበረታባቸው ሴቶችም አሉ።
ከወር አበባ መምጣት ሁለት ሳምንት በፊት ያለው የስሜት ወዋዠቅ ከጭንቀት እና ከድባቴ አልፎ ራስን ለማጥፋት እስከማሰብ ይደርሳል።
በጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ ኦፍ ሜድስን የሥነ ልቦና ባለሙያ ሊሳ ሀንትሶ "ፒኤምዲዲ ያለባቸው ሴቶች በየወሩ ይፈተናሉ። በሕይታቸው ላይ ከፍተኛ ጫና ያሳድራል" ይላሉ።
ከማሕጸን እንቁላል በሚለቀቅበት ወቅት (ovulation) ጤናማ እና ደስተኛ መሆን የተለመደ ነው።
ፕሮጀስትሮን ሲሰባባር የሚፈጠረው ኬሚካል (allopregnanolone) የማረጋጋት ሚናን ይጫወታል።
"አሎፕሬግኖሎን በመርፌ የሚሰጠው ሰው ይዝናናል" ይላሉ ባለሙያዋ።
በእርግዝና፣ በማረጥ እና በቅድመ ማረጥ ወቅትም የሆርሞን መዋዠቅ የስሜት ነውጥ ያስከትላል።
ልጅ ከወለዱ ሴቶች 13 በመቶ ድባቴ ይገጥማቸዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ልጅ እንደተወለደ የፕሮጀስትሮን እና ኤስትሮጅን ሆርሞኖች መጠን ይቀንሳል።
ቅድመ ማረጥ ላይ ያሉ ሴቶችም የሆርሞን መዋዠቅ ይገጥማቸዋል።
በቶሮንቶ ዩኒቨርስቲ የሥነ ልቦና ባለሙያ የሆኑት ሊሳ ጋይሊያ "ዋናው ነገር የሆርሞን መጠን ሳይሆን አንደኛው ሆርሞን ከፍ ብሎ ሌላኛው ሆርሞን ዝቅ ሲል ያለው ለውጥ ነው። አንዳንዶች በቀላሉ በሆርሞን መዋዠቅ ይጎዳሉ። አንዳንድ ሴቶች ደግሞ ያለ ምንም ለውጥ ቅድመ ማረጥን ያልፉታል" ይላሉ።
ወንዶች ዕድሜያቸው ሲገፋ የቴስቴስትሮን መጠን መቀነስ ይገጥማቸዋል።
ለውጡ እንደ ሴቶች በአንዴ የሚስተዋል ሳይሆን ቀስ በቀስ የሚከሰት ነው።
አንዳንድ ወንዶች በዚህ መጠነኛ ለውጥ ምክንያት የስሜት መዋዠቅ ይታይባቸዋል።
"ከቴስቴስትሮን መጠን ጋር በተያያዘ በአንዳንድ ወንዶች ላይ የስሜት ለውጥ ይታያል። ጉዳዩ እምብዛም ትኩረት አልተሰጠውም" ሲሉ ባለሙያዋ ያስረዳሉ።
እነዚህ ሆርሞኖች የሴሮቶኒን እና የዶፓሚን መጠን ላይ ለውጥ ስለሚያመጡ ነው የስሜት መዋዠቅ የሚከሰተው።
ሴሮቶኒን ዝቅ ሲል ድባቴ ይከሰታል። መድኃኒት በመውሰድ የሆርሞኑን መጠን ማስተካከል የተመደ የሕክምና ስልት ሆኗል።
አንዳንድ የኤስትሮጅን ዓይነቶች ሴሮቶኒን በፍጥነት ምላሽ እንዲሰጥ ያስችላሉ። የዶፓሚን መጠንንም ይጨምራሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሆርሞን እና የሰውነት ትስስር
ትውስታን በሚቆጣጠረው ሂፖካምፐስ የተባለው የአእምሮ ክፍል ኒውሮኖች ሲሞቱ ሆርሞን ይዛባል።
ሆርሞኖች የሚዘዋወሩበት አጠቃላይ ሥርዓት ሰውነት ሲጨነቅ የሚሰጠውን ምላሽ ይወስናል።
በሰውነት የሚሠራጩ የአብዛኞቹ ሆርሞኖች መነሻ የሆነው የአእምሮ ክፍል ሃይፖታለመስ ለሰውነት መልዕክት ያስተላልፋል።
"አንድ ሰው ሲጨነቅ ሆርሞኖቹ ይለቀቃሉ። ሰውነት ጭንቀትን እንዲቆጣጠር ይረዳሉ" ሲሉ ባለሙያዋ ያስረዳሉ።
ሰውነት ጭንቀትን እንዲያስወግድ መልዕክት ቢተላለፍም የበረታ ጭንቀት ሲከሰት ከሰውነት ቁጥጥር ውጪ ይሆናል።
ለምሳሌ ሰዎች ጥቃት ሲደርስባቸው በሰውነታቸው ላይ የሚከሰተውን ጭንቀት መቆጣጠር የማይቻለውም ለዚህ ነው።
በሰውነት ውስጥ የሚዘዋወረው ኮርቲሶል (cortisol) ጭንቀት ሲባባስ አእምሮ ውስጥ በብዛት ይመጫል።
ኮርቲሶል ደግሞ ኒውሮኖችን እና ሌሎችም እንደ አሜግዳላ (amygdala) እና ፕሪፍሮንታል ኮርቴክስ (prefrontal cortex) ያሉ የአእምሮ ክፍሎችን ያጠቃል።
እነዚህ የአእምሮ ክፍሎች ትውስታን፣ ትኩረትን እና ስሜትን ይቆጣጠራሉ።
አሜግዳላ ስሜትን የሚቆጣጠር የአእምሮ ክፍል ስለሆነ ማንኛውም መዋዠቅ ሲገጥመው የስሜት መናወጥ፣ ቁጣ እና ከቁጥጥር የወጣ አሉታዊ ስሜት ይከሰታሉ።
ፕሪፍሮንታል ኮርቴክስ ላይ የሚደርስ መዋዠቅ ደግሞ መዘንጋት እና ትክክለኛ ውሳኔ ላይ ለመድረስ መቸገርን ያስከትላል።
ኮርቲሶል ሲበዛ ጭንቀት ይከተላል። በተለምዶ 'የፍቅር ሆርሞን' የሚባለው ኦክሲቶሲን (oxytocin) ደግሞ በተቃራኒው ያረጋጋል።
ልጅ ሲወለድ፣ ልጅ ጡት ሲጠባ እንዲሁም በወሲበ ፈንጠዚያ ወቅት ሆርሞኑ ይበራከታል።
"ኦክሲቶሲን በሰዎች መካከል ትስስር እንዲፈጠር ያደርጋል። ደኅና እንደሆንን እና የሚደግፉን ሰዎች እንደከበቡን ሲሰማን የኮርቲሶል መጠን ይቀንሳል" ሲሉ የሥነ ልቦና ባለሙያዋ ያስረዳሉ።
ሰዎች ኦክሲቶሲን በአፍንጫቸው ቢስቡ ደግ፣ ሰው አማኝ፣ ቀና እና ገራገር እንደሚሆኑ ጥናቶች ያሳያሉ።
በጉሮሮ አካባቢ የሚመረቱ ሁለት ዋነኛ ሆርሞኖች አለመመጣጠን ከድባቴ እና ከጭንቀት ጋር ትስስር እንዳላቸው ጥናቶች ያሳያሉ።
እነዚህ ሁለት ሆርሞኖች (triiodothyronine (T3) እና thyroxine (T4) የሚባሉት) የልብ ምት እና የሰውነት ሙቀትን ይቆጣጠራሉ።
መጠናቸው ከፍ ሲል የጉሮሮ ችግር የሚያስከትሉ ሲሆን፣ መጠናቸው ዝቅ ሲል ደግሞ ድባቴ እና ጭንቀት ይገጥማል።
አዳዲስ ሕክምናዎች
ሰዎች የስሜት መዋዠቅ ሲገጥማቸው የመጀመሪያው ሕክምና የሆርሞን መጠናቸውን ማስተካከል ነው።
ስለ ሆርሞኖች ተጨማሪ መረጃዎች ሲገኙ ለአእምሮ ሕክምና መሻሻል ይረዳሉ። አዳዲስ ሕክምናዎች እንዲገኙም ያግዛሉ።
ከድንገተኛ አደጋ በኋላ የሚገጥም ድባቴን (post-partum depression) ለማከም የአሎፕርግኖሎን ሆርሞንን በሰውነት ውስጥ የሚፈጥረው መድኃኒት (Brexanolone) ተጠቃሽ ምሳሌ ነው።
የቴስቴስትሮን መጠንን ከፍ ለማድረግ የሚወሰዱ መድኃኒቶች አሉ።
እነዚህ መድኃኒቶች ከፀረ ድባቴ ሕክምና ጋር አብረው ይሄዳሉ።
ሆርሞንን ወደ ሰውነት የማስገባት ሕክምና (hormone replacement therapy ወይም HRT) በማረጥ እና ቅድመ ማረጥ ወቅት ላሉ ሴቶች ሕክምና የሚሰጥበት መንገድ ነው።
የወር አበባ የስሜት መዋዠቅ የሚበረታባቸው ሴቶች ሆርሞን ያላቸው የወሊድ መቆጣጠሪያ መድኃኒቶችን ይወስዳሉ። በአንዳንድ ሴቶች ላይ ግን የጎንዮሽ ጉዳት ያስከትላል።
"ሆርሞኖች ስሜትን እና የአእምሮ ጤናን እንደሚያዛቡ እናውቃለን። እንዴት ይሄንን እንደሚያደርጉ በትክክል ስናውቅ ተገቢውን ሕክምና እናገኛለን" ሲሉ የሥነ ልቦና መምህሯ ናፊሳ ይናገራሉ።
የሴሮቲን መጠንን የሚቆጣጠሩ የፀረ ድባቴ መድኃኒቶች ሁሌም ውጤታማ አይሆኑም። በተለይም ዕድሜ ሲገፋ ውጤታማነታቸው ይቀንሳል። ስለዚህም አዳዲስ አማራጮች መፈለጋቸው አይቀርም።















