ከሐማስ ጋር የተፋጠጡት የጎሳ ታጣቂዎች እና ያልለየለት የጋዛ ቀጣይ ዕጣ ፋንታ

የፎቶው ባለመብት, Anadolu via Getty Images
"ጦርነት አብቅቷል።"
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለሁለት ዓመታት በጋዛ ሰርጥ ሲካሄድ የቆየውን ጦርነትን ለመቋጨት ያለመው የተኩስ አቁም ስምምነት በእስራኤል እና ሐማስ መካከል መፈረሙን በኩራት ይፋ ሲያደርጉ ተጠቀሙት አገላለጽ ነው።
ስምምነቱ እስራኤል ከጋዛ አካባቢዎች እንድትወጣ ማድረግን እንዲሁም የታጋቾች እና የታሳሪዎች ልውውጥን ያካተተ ነው።
ነገር ግን በትራምፕ የሰላም ዕቅድ ውስጥ የተካተቱ እና የተኩስ አቁሙን ሊያፈርሱ የሚችሉ ወሳኝ ጉዳዮች አሁንም መፍትሔ አላገኙም።
የጋዛ ወደፊት ምን ሊመስል ይችላል? ሐማስስ ትጥቅ ይፈታል?
በትራምፕ ዕቅድ መሠረት ጋዛን ማን ይመራል?
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ጋዛ በጊዜያዊነት ከየትኛውም ቡድን ያልሆኑ "በቴክኖክራቲክ፣ የፍልስጤም የፖለቲካ ኮሚቴ" መመራት እንዳለበት ተናግረዋል። ኮሚቴው "የዕለት ተዕለት የህዝብ እና የማዘጋጃ ቤት አገልግሎቶችን የመስጠት ኃላፊነት" እንደሚኖረውም ገልጸዋል።
በሌላ አነጋገር ወገንተኛ ያልሆነ ድርጅት በግዛቱ የሚሰጠውን አገልግሎት ያከናውናል ማለት ነው።
ኮሚቴው ብቁ ከሆኑ ፍልስጤማውያን እና ዓለም አቀፍ ባለሞያዎች ይዋቀራል። "ቦርድ ኦፍ ፒስ" የተባለ አዲስ ዓለም አቀፍ የሽግግር አካልም ኮሚቴውን እንደሚቆጣጠር የዕቅዱ ይፋዊ ሰነድ ያመለክታል።
የቀድሞው የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌር ይህን ኃላፊነት እንደሚረከቡ የሚጠበቅ ሲሆን፣ የሌሎች አገራት መሪዎችም ይፋ ይደረጋሉ።
ዕቅዱ አሜሪካ ከአረብ እና ከዓለም አቀፍ አጋሮቿ ጋር በትብብር ጊዜያዊ ዓለም አቀፍ የማረጋጊያ ኃይል እንድታቋቁም ጥሪ ያቀርባል።
ይህ ኃይል በፍጥነት ጋዛ ውስጥ በመሰማራት ለተፈቀደለት የፍልስጤም የፖሊስ ኃይል ሥልጠና እና ድጋፍ ይሰጣል።
ኃይሉ ከዮርዳኖስ እና ግብፅ ጋር የቅርብ ትብብር እንዲያደርግ እና በዘላቂነት የጋዛን የውስጥ ፀጥታን እንዲያስጠብቅ ዕቅድ ተይዞለታል።
ዩናይትድ ኪንግደም እና ፈረንሳይ ከተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ምክር ቤት ጋር በመሆን ይህንን ኃይል ለማቋቋም እየሠሩ ነው።

የፎቶው ባለመብት, PA Media
ሐማስ ትጥቅ ይፈታል?
እስራኤል ሐማስ ትጥቅ መፍታት አለበት በሚለው አቋሟ እንደጸናች ነው።
ትራምፕ በመካከለኛው ምሥራቅ ከነበራቸው ቆይታ በኋላ ባደረጉት ንግግር፤ "ትጥቅ የማይፈቱ ከሆነ፤ እኛ እናስፈታቸዋለን። በፍጥነት፣ ምናልባትም በጉልበት ይከናወናል" ብለዋል።
"ከሐማስ ጋር ተነጋገ�� ነበር። ትጥቅ ልትፈቱ ነው አይደለም? [አልኳቸው]፤ አዎ፤ አለቃ ትጥቅ ልንፈታ ነው [አሉኝ]። ይህንን ነው የነገሩኝ" ሲሉም ተደምጠዋል።
የፈረንሳዩ የዜና ወኪል ኤኤፍፒ ያነጋገራቸው አንድ የሐማስ ባለሥልጣን ግን መሳሪያን ማስረከብ "ከጠረንጴዛው እና ከጥያቄ ውጪ" መሆኑን ተናግረዋል።
ኤኤፍፒ፤ የተኩስ አቁሙ ገቢራዊ መሆን ከጀመረ በኋላ ያነጋገራቸው ስማቸው ያልተጠቀሰ የሐማስ ባለሥልጣን፤ ቡድኑ በሽግግሩ ወቅት ጋዛን በማስተዳደር ውስጥ እንደማይሳተፍ ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ ባለሥልጣኑ ሐማስ "የፍልስጤም ስሪት ዋነኛ አካል" ሆኖ እንደሚቀጥል አስረግጠዋል።
ሐማስ ዓለም አቀፍ አካል ተሳትፎን፤ በተለይም ደግሞ ቶኒ ብሌር ሊኖራቸው የሚችለውን ሚና በተመለከተ አቋሙን ከመግለጽ ተቆጥቧል።

የፎቶው ባለመብት, Bashar Taleb / AFP via Getty Images
የሐማስ ተዋጊዎች አሁን ያሉት የት ነው?
እስራኤል ጋዛን ለቅቃ መውጣቷን ተከትሎ የሐማስ ተዋጊዎች በጎዳናዎች ላይ እንደተሰማሩ ሚያሳዩ ቪዲዮዎች እና ፎቶዎች እየወጡ ነው።
ሐማስ እስራኤል የለቀቀቻቸውን ስፍራዎች ለመቆጣጠር በሺዎች የሚቆጠሩ ፀጥታ ኃይሎቹን ማሰማራቱን የአካባቢው ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ሐማስ በበኩሉ ጋዛን መልሶ ሙሉ በሙሉ የመቆጣጠር ሀሳብ አለው መባሉን አስተባብሏል።
ከሐማስ ጋር ሚዋጉት የጎሳ አባላት እነማን ማናቸው?
በጦርነት ሲናጥ የከረመው የጋዛ ሰርጥ ከባድ የሰው እና የንብረት ውድመት አስተናግዷል።
ከጦርነቱ መቆም በኋላ በሐማስ ተዋጊዎች እና በታጣቂ የጎሳ አባላት መካከል ግጭት ተቀስቅሶ ከ20 በላይ ሰዎች ተገድለዋል።
ትራምፕ ወደ መካከኛው ምሥራቅ በተጓዙበት ወቅት፤ ሐማስ ጋዛ ውስጥ "የውስጥ የፀጥታ ኦፕሬሽን" እንዲያከናውን ፈቃድ እንደተሰጠው ተናግረዋል።
ቡድኑ "ችግሮችን ለማስቆም" እንደሚፈልግ የጠቀሱት ትራምፕ፤ ይህንንም "ለተወሰነ ጊዜ እንዲያከናውኑ እንደተፈቀደላቸው" ገልጸዋል።
ሐሙስ ዕለት ትራምፕ ትሩዝ ሶሻል በተሰኘው የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ "ሐማስ ከስስምነቱ ውጪ ጋዛ ውስጥ ሰዎችን መግደል የሚቀጥል ከሆነ፤ እነሱን [ሐማስን] ሄዶ ከመግደል ውጪ ሌላ አማራጭ አይኖረንም" ብለዋል።
ቆየት ብለውም በጽሁፋቸው ላይ "እኛ" በማለት የጠቀሱት የአሜሪካ ወታደሮችን እንዳልሆነ አብራርተዋል።
ፍልስጤማዊው ተንታኝ ጂሃድ ሃርብ የጋዛ ዕጣ ፈንታን በተመለከተ "ሁለት አማራጮች" መኖራቸውን ያስረዳል።
"ወይ የተዳከመው እና በጦርነት ተጎዳው ሐማስ በእስራኤል ፈቃድ ሰርጡን እንዲቆጣጠር መፍቀድ አልያም በሂደት ሥልጣኑን ወደ ፍልስጤም አስተዳደር ማስተላለፍ [ነው]፤ ይህን አማራጭ [የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን] ኔታንያሁ አይቀበሉትም" ይላል።
የፍልስጤም አስተዳደር በእስራኤል በተወረረው ዌስት ባንክ የተወሰነ ቁጥጥር አለው።

የፎቶው ባለመብት, Anadolu via Getty Images
ኔታኒያሁ፤ ለሐማስ ምላሽ ለመስጠት እስራኤል ጋዛ ውስጥ "ጎሳዎችን ማንቀሳቀሷን" ሰኔ ላይ ተናግረው ነበር። ሐማስ ጎሳዎቹ ከእስራኤል ጋር ይተባበራሉ በማለት ይከስሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በያስር አቡ ሻባብ ለሚመራው ፀረ ሐማስ ቡድን መሳሪያ እንዲሰጥ መፍቀዳቸውን የተመለከተ ዘገባ ከወጣ በኋላ በኤክስ ገጻቸው በለጠፉት ቪዲዮ፤ "ይህንን ማድረግ ምን ችግር አለው" ሲሉ ተደምጠዋል። "የእስራኤላዊ ወታደሮችን ሕይወት ይታደጋል...[ይህንን] ይፋ ማድረግ የሚያግዘው ሐማስን ብቻ ነው" ብለዋል።
ሐማስ በቅርቡ ዶሙሽ ከተባለ ሌላ የጎሳ ቡድን ጋር ግጭት ውስጥ ግብቷል። ሐማስ የጎሳው አባላት ለእስራኤል ታማኝ ከሆነ ታጣቂ ቡድን ጋር ግንኙነት አላቸው በማለት ይከስሳል።
የእስራኤል ውስጥ ያለው አመለካከት ምንድነው?
እስራኤላዊው ጋዜጠኛ ኢል ኒሳን፤ በጋዛ አስተዳደር ውስጥ ሐማስ ሚና ይኖረዋል ብሎ እንደማይጠብቅ ለቢቢሲ አረብኛ ተናግሯል።
"እስራኤል ስለምትቃወመው ብቻ ሳይሆን ከሁለት ዓመቱ ጦርነት በኋላ በጋዛ ነዋሪዎች ዘንድ በተፈጠረው ቅሬታ ምክንያትም ነው" ሲል ሃሳቡን ያብራራል።
የኔታኒያሁ መንግሥት የያዘው ይፋዊ አቋም ሐማስ በጋዛ አስተዳደር ውስጥ የሚፈቅድ አይደለም። በተጨማሪም እስራኤል የፍልስጤም አስተዳደር ጋዛን እንዲመራ የማድረግ ሃሳብንም አትቀበልም።
ሐማስ መስከረም 2016 ዓ.ም. በፈጸመው ጥቃት 1,200 ሰዎች ከተገደሉ በኋላ ተጠናክሯል። እስራኤል ከዚህ ጥቃት በኋላ በከፈተችው ዘመቻ ቢያንስ 67 ሺህ ሰዎችን ተገድለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Jalaa Marey / POOL / EPA / Shutterstock
የተኩስ አቁሙ ከመፈረሙ አስቀድሙ ነሐሴ ላይ ከፎክስ ኒውስ ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት ኔታኒያሁ፤ እስራኤል ጋዛን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር እና ቀጥሎም ላልታጠቀ "የአረብ አስተዳዳሪ ኃይል" ለማስተላለፍ ማቀዷን ገልጸው ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጋዛን አስተዳደር ይረከባል ያሉትን ቡድን የገለጹት "በአግባቡ የሚንቀሳቀስ፣ ለእኛ ስጋት የማይጋርጥ፣ የጋዛ ነዋሪዎች ጥሩ ሕይወት እንደሚኖሩ የሚያረጋገጥ የአረብ ኃይል" በማለት ነው።
ጋዜጠኛው ኒሳን፤ የኔታኒያሁ መንግሥት የፍልስጤም አስተዳደር ጋዛን እንዳይቆጣጠር የሚቃወመን በዌስት ባንክ እና በሰርጡ መካከል ግዛታዊ ግንኙነት እንዳይኖር ስለሚፈልግ ነው የሚል እምነት አለው።
ይሁን እንጂ ኔታኒያሁ ከትራምፕ በሚመጣ ጫና ምክንያት የፍልስጤም አስተዳደር ጋዛ ውስጥ የተገደበ ተሳትፎ እንዲኖረው ሊፈቅዱ እንደሚችሉ ይናገራል።
የፍልስጤም ባለሥልጣን
የፕሬዝዳንት ትራምፕ ዕቅድ፤ በእስራኤል በተወረረው ዌስት ባንክ የተወሰኑ ቦታዎችን የሚቆጣጠረው የፍልስጤም ባለሥልጣን በሂደት ጋዛን እንደሚቆጣጠር ያስቀምጣል።
በዕቅዱ መሠረት፤ ይሄ የሚሆነው ባለሥልጣኑ የተሃድሶ ሪፎርም ካጠናቀቀ በኋላ ነው።ይህ ሪፎርም፤ "የትራምፕ 2020 የሰላም ዕቅድ እና የሳውዲ - ፈረንሳይ የሰላም ንግግርን ጨምሮ በተለያዩ የዕቅድ ሰነዶች ውስጥ የተጠቀው" ነው።
አሜሪካ የምትፈልገው ሪፎርም ይካሄዳል የምትለውን ሙስናን መቀነስንም ያካተተ ነው።
እስራኤል ጋዛን የወረረችው በአውሮፓውያኑ 1967 ከተካሄደው ጦርነት በኋላ ነው። በፋታህ እንቅስቃሴ ተጽዕኖ ስር ያለው የፍልስጤም ባለሥልጣን አካባቢውን ተቆጣጠረው እስራኤል በ2005 መውጣቷን ተከትሎ ነው። በ2007 የተካሄደውን አስከፊ የውስጥ ግጭት ተከትሎ ግን ቁጥጥሩን በሐማስ ተነጥቋል።
የፋታህ እንቅስቃሴ በተለያዩ ሰዎች የተመሠረተ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥም የቀድሞው የፍልስጤም ባለሥልጣን ፕሬዝዳንት ያሲር አረፋት ይገኙበታል።
በአውሮፓውያኑ 1990ዎቹ በፋታህ የሚመራው የፍልስጤም ነጻነት ድርጅት በእስራኤል ላይ የሚያካሂደውን የትጥቅ ትግል በይፋ አቁሟል።
ድርጅቱ የ1967ቱ ድንበርን መሠረት በማድረግ አገረ ፍልስጤም እንድትመሠረት በር የከፈተውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ስምምነት ተቀብሏል።
የፍለስጤም ባለሥልጣን የትራምፕን የሰላም ዕቅድ በበጎ ተቀብሎታል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ መሐመድ ሙስጠፋ፤ "እኛ አሁንም እዚያው [ጋዛ ውስጥ] ነን" ሲሉ ለሮይተርስ ዜና ወኪል ተናግረዋል። "እገዛ እና ቁጥጥር የሚያደርግ ጊዜያዊ ዓለም አቀፍ መዋቅር አንድ ነገር ነው፤ ትክክለኛ መንግሥት እና ይህንን መፈጸም ደግሞ ሌላ ጉዳይ ነው" ብለዋል።
የአረብ አገራትን ጨምሮ ብዙ አገራት "ነገሮችን ለማከናወን ብቸኛው ተግባራዊው መንገድ" ይህ በመሆኑ የፍልስጤም ባለሥልጣን የጋዛን "ኃላፊነት" መቀበል አለበት ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል።

የፎቶው ባለመብት, AP
ፕሬዝዳንት ትራምፕ
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጦርነቱን ለማስቆም ሐማስ መሸነፍ አለበት የሚል አቋማቸውን በተደጋጋሚ ሲገልጹ ቆይተዋል። ነገር ግን ጋዛ በድኅረ ጦርነት ሚኖራትን ዕጣ ፋንታ በተመለከተ በጊዜ ሂደት አቋማቸውን ቀይረዋል።
ከወራት በፊት ነዋሪዎችን ወደ ግብፅ እና ዮርዳኖስ በማስፈር እንዲሁም የመዝናኛ ቦታዎችን በመገንባት ጋዛን "የመካከለኛው ምሥራቅ ሪቬራ" የማድረግ ውጥናቸውን ገልጸው ነበር።
በአሁኑ ዕቅዳቸ�� ውስጥ ግን ይህ የለም።
በትራምፕ የዕቅድ ሰነድ ውስጥ ጋዛን ስልሚያስተዳድረው ዓለም አቀፍ አካል ዝርዝር መረጃ አልተካተተም። የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች ግን የቡድኑ አባል ይሆሉ ተብለው የሚጠበቁ ፍልስጤማዊ ያልሆኑ ታዋቂ ግለሰቦችን ስም ይዘው ወጥተዋል።
እስካሁን ግን ይፋዊ ማረጋገጫ አልተሰጠም። ትራምፕ ቶኒ ብሌር "ኃላፊነቱን ለመረከብ በቂ ተቀባይነት" ያላቸው ስለመሆኑ እርግጠኛ ለመሆናቸውን በቅርቡ ተናግረዋል።
ትራምፕ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ጉዞ ላይ እያሉ ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄ ቀጥተኛ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
ይሁን እንጂ ዓለም አቀፉ ኃይል "ትልቅ፣ ጠንካራ ኃይል ይሆናል። ሰዎች በሥርዓት መንቀሳቀስ ስለሚጀምሩ ለረጅም ጊዜ አይቆይም" ብለዋል።
የጋዛን የሽግግር ጊዜ የሚቆጣጠረው "የሰላም ቦርድ"፤ "በተቻለ ፍጥነት ዝግጁ እንደሚሆን" አክለዋል።
ከጉዞ በተመለሱበት ወቅት ስለ የሁለት አገር መፍትሔ ለቀረበላቸው ጥያቄ ደግሞ፤ "ብዙ ሰዎች አንድ አገርን ይመርጣሉ፤ የተወሰኑት ሁለት አገርን ይመርጣሉ። እናያለን። እስካሁን ድረስ በዚህ ላይ አስተያየት አልሰጠሁም" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Julien De Rosa / AFP via Getty Images
አሸማጋዮች
ዋነኛዎቹ አሸማጋዮች ግብፅ እና ኳታር፤ የኒው ዮርክ ስምምነት ተብሎ ለሚጠራው ዓለም አቀፍ ማዕቀፍ ድጋፋቸውን ሰጥተዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ስምምነቱን ያጸደቀው የእስራኤል እና ፍልስጤም ግጭትን ለማስቆም እንዲሁም የሁለት አገር መፍትሔን ለማጠናከር ነው።
'ዘ ኒው ዮርክ ዲክላሬሽን' ጋዛ ውስጥ በፍልስጤም ባለሥልጣን ስር የሚሆን የሽግግር አስተዳደር ኮሚቴ እንዲቋቋም ይጠይቃል።
ጋዛን ጨምሮ በሁሉም የፍልስጤም ግዛት ውስጥ የሚኖረው መንግሥታዊ አስተዳደር እና ሕግ ማስከበር ለፍልስጤም ባለሥልጣን ሊተው እንደሚገባም አስፍሯል።
ይህ ዕቅድ የጋዛን ዕጣ ፈንታ ከፍልስጤም አገርነት መቋቋም ጋር ከሚያስተሳስሩት የግብፅ እና የኳታር ባለሥልጣናት መግለጫ ጋር የሚጣጣም ነው።
አሁንም ቢሆን ግን የፍልስጤም ባለሥልጣን ጋዛን እንደገና በተሳካ ሁኔታ ማስተዳደር እንደሚችል ለማሳየት ዕድሉን ያገኝ ይሆን ወይ የሚለው የሚወሰኑት ከባለሥልጣኑ ቁጥጥር ውጪ የሆኑ ሌሎች በርካታ ጉዳዮች ናቸው።











