የኒውክሌር ጦር መሳሪያ የነበራት አፍሪካዊት አገር ማን ናት? መሳሪያውን የት አደረሰችው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቃት በኋላ የተከሰተው ቀዝቃዛው ጦርነት በኃያላኑ አገራት መካከል የነበረው ፍጥጫ ወደ ኒውክሌር ጦርነት አምርቶ እልቂት ይከተላል የሚል ስጋትን አስከትሎ ነበር።
በአሜሪካ እና በሶቪየት ኅብረት መካከል የነበረው የኒውክሌር ፉክክር እና ጠላትነት ባለበት ይህ አደገኛ የጦር መሳሪያ ወደ ሌሎች አገራት ሊስፋፋ ይችላል የሚል ፍርሃትንም ፈጥሮ ነበር። ቦምቡ ከአገራት አልፎ መንግሥታዊ ወዳልሆኑ ቡድኖች ሊገባ ይችላል የሚለው ስጋት ደግሞ ኃያላኑን ጭምር ያሳሰበ ጉዳይ ነበረ።
ይህንን ስጋት ለመቆጣጠር በወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የነበሩት ዲዋይት አይዘንአወር በአውሮፓውያኑ 1953 የኒውክሌር ቦምብ እንዳይኖራቸው የተከለከሉ አገራት የኒውክሌር ኃይልን ለሰላማዊ አገልግሎት እንዲጠቀሙ የሚፈቅድ "አተምስ ፎር ፒስ" የተባለ እንቅስቃሴ ጀመሩ።
በ1957 ደግሞ ዓለም አቀፉ የአውቶሚክ ኃይል ተቆጣጣሪው ኤጀንሲ (አይኤኢኤ) የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አካል ሆኖ የተቋቋመ ሲሆን፤ ከአስር ዓመት በኋላ ደግሞ በ1968 የኒውክሌር መስፋፋት ስጋትን ለማስወገድ የሚያስችል ስምምነት ይፋ ሆነ።
ነገር ግን ይህ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ መስፋፋትን ለመግታት የተደረሰው ስምምነት እንደታሰበው በሁሉም የዓለም ክፍል የሚገኙ አገራት የኒውክሌር ጦር መሳሪያን እንዳይገነቡ ለማድረግ ሳይችል ቀርቷል።
የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ምንድን ነው?
የኒውክሌር ቦምቦች እጅግ በጣም ኃይለኛ ፈንጂዎች ናቸው።
በዚህ የፍንዳታ ሂደት ውስጥ ቦምቡ ኃይልን የሚያገኘው ከአቶም እና ከአይሶቶፕ ሲሆን፣ ለዚህም ነው አንዳንድ ጊዜ አውቶሚክ ቦምብ የሚባለው።
የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎች ከፍተኛ መጠን ያለው ጨረር ስለሚረጩ በጨረር ምክንያት ሕመምን ያስከትላሉ፤ በዚህም የተነሳ መሳሪያው የሚያስከትለው ጉዳት ከፍንዳታው በኋላም ለረጅም ጊዜ ይቀጥላል።
ነገር ግን በዓለም ታሪክ ይህ መሳሪያ ጥቅም ላይ የዋለው ሁለት ጊዜ ብቻ ነው።
ይህም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ላይ በጃፓን ከተሞች ሂሮሺማ እና ናጋሳኪ ላይ ነው። በዚህም ከባድ ዕልቂት እና ውድመት መድረሱ አይዘነጋም።
በሂሮሺማ ከተማ ላይ በተጣለው ቦምብ ምክንያት የተፈጠረው ጨረር ለበርካታ ወራት ቆይቶ 80 ሺህ የሚደርሱ ሰዎችን ለሞት ዳርጓል። በናጋሳኪ ደግሞ ከ70 ሺህ በላይ ሰዎች ሞተዋል።
ምንም እንኳን ይህንን ቦምብ ሩሲያ፣አሜሪካ፣ዩናይትድ ኪንግደም፣ፈንሳይ፣ቻይና፣ሕንድ፣ፓኪስታን፣ እስራኤል እና ሰሜን ኮሪያ የታጠቁ ቢሆንም ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ጥቅም ላይ አልዋለም።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኒውክሌር ጦር መሳሪያ የነበራት አፍሪካዊት አገር ማን ናት?
ይህንን አውዳሚ የጦር መሳሪያ በቀዳሚነት የታጠቁት የወቅቱ ኃያላን አሜሪካ እና ሶቪየት ኅብረት ሲሆኑ፤ በተከታይነት ከአውሮፓ ዩናይትድ ኪንግደም እና ፈረንሳይ፣ከእስያ ቻይና፣ሰሜን ኮሪያ፣ሕንድ እና ፓኪስታን፣ ከመካከለኛው ምሥራቅ ምንም እንኳን መሳሪያው እንዳላት በይፋ ባታምንም እስራኤል እንዲሁም ከአፍሪካ በአፓርታይድ ስር የነበረችው ደቡብ አፍሪካ ይጠቀሳሉ።
በጥቂት ነጮች የዘር መድልዎ ሥርዓት ሥር የነበረችው ደቡብ አፍሪካ ከአውሮፓውያኑ 1960ዎቹ እስከ 1990ዎቹ የኒውክሌር፣ባዮሎጂካል እና የኬሚካል ጦር መሳሪያዎችን ጨምሮ ጅምላ ውድመትን በሚያደርሱ መሳሪያዎች ላይ ምርምር ስታካሂድ ቆይታለች።
እንደሚነገረው በደቡብ አፍሪካ እና በአካባቢዋ የሚካሄዱ የነጻነት እንቅስቃዎች የአፓርታይድ ሥርዓትን ስጋት ላይ ስለጣሉት ከሶቪየት ኅብረት እና በእሷ በሚደገፉ የአካባቢው ኃይሎች ፈተና ከገጠማት አሜሪካ ከጎኗ እንድትሰለፍ ለማድረግ የኒውክሌር መሳሪያን መጠቀሚያ ማድረግን ዓላማዋ አድርጋ ነበር የተነሳችው።
ደቡብ አፍሪካ አደገኛውን የጦር መሳሪያ በጦር ሜዳ ላይ ለመጠቀም ሳይሆን ከየአቅጣጫው በዘር መድልዎ ሥርዓቷ ላይ የሚደርስባትን ጫና ለማርገብ እንደ መከላከያ ይዛው ነበር።
በዚህም እስከ ስድስት የሚደርሱ የኒውክሌር አረሮችን በድብቅ አዘጋጅታ ነበር።
ደቡብ አፍሪካ የኒውክሌር ጦር መሳሪያውን በመገንባት ሂደት ውስጥ የአሜሪካ፣ የፓኪስታን፣ የእስራኤል እና የታይዋን ባለሙያዎች በተለያየ ሁኔታ ተሳትፈዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ለኒውክሌር ጦር መሳሪያ ግብአትነት የሚውለው ዋነኛው ማዕድን ዩራኒየም ባለቤት የሆነችው ደቡብ አፍሪካ የጦር መሳሪያውን በእጇ ካስገባች በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሯ የነበሩት ፒ ደብሊው ቦታ.. የመሳሪያውን ጠቀሜታ በተመለከተ ወታደራዊ ሳይሆን በዋናነት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚኖራትን የመደራደር አቅም ከፍ የሚያደርግ "ፖለቲካዊ መሳሪያ ነው" ብለውታል።
ደቡብ አፍሪካ አቅሟ በዙሪያዋ ባሉ አገራት በሶቪየት እና በኩባ በሚደገፉት የነጻነት እንቅስቃሴዎች እየተፈተነ በመጣበት ጊዜ በእጇ ያሉት ኒውክሌር አረሮች አስፈላጊነት እያከተመ ለሥርዓቱም አደጋ የሚያመጣ መሆኑን በመገንዘቧ ለማስወገድ ማሰብ ጀመረች።
የአፓርታይድ ፍጻሜ ሲቃረብ የደቡብ አፍሪካ መንግሥት በራሱ ተነሳሽነት ቀድሞ አውዳሚዎቹን የጦር ማሰሪያዎች ማስወገዱ፣ በቀጣናው እና በዓለም አቀፍ ፖለቲካ ውስጥ መተማመን ለመገንባት እና ተቀባይነትን ለማግኘት ወሳኝ እርምጃ ነበር።
በዚህም የአፓርታይድ ሥርዓት አብቅቶ የብዙኃኑ የጥቁሮች መንግሥት በደቡብ አፍሪካ ከመቋቋሙ በፊት ያሏትን የኒውክሌር ቦምቦች አስወግዳ ስታካሂድ የነበረውን የጦር መሳሪያውን ግንባታ ፕሮግራም በፈቃዷ አቆመች።
ከዚያም በአውሮፓውያኑ 1991 የኒውክሌር ጦር መስፋፋት መከላከል ስምምነት ፈራሚ ሆና ዓለም አቀፉ የአውቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ በአገሪቱ ውስጥ ያካሄደውን ፍተሻ በ1994 አጠናቆ ደቡብ አፍሪካ በእጇ ላይ ያሉ የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎች መወገዳቸውን አረጋግጧል።
በዚህም በአፍሪካ ውስጥ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ በመታጠቅ ቀዳሚ የነበረችው ደቡብ አፍሪካ ለዓመታት ያካሄደችውን መርሃ ግብር ሙሉ ለሙሉ በማቆም በዓለም የአውዳሚው መሳሪያ ባለቤት ከሆኑ አገራት ዝርዝር ውስጥ ወጣች።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዩራኒየም በየትኞቹ የአፍሪካ አገራት ይመርታል?
አፍሪካ በምድራችን ላይ በተለያዩ የተፈጥሮ ማዕድናት እና ሀብቶች ከበለጸጉ አህጉራት መካከል በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት ውስጥ ናት።
ለኒውክሌር ጦር መሳሪያ ወሳኝ የሆነው ዩራኒያም በበርካታ የአፍሪካ አገራት ውስጥ ይገኛል።
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ወቅት አሜሪካ የመጀመሪያውን የኒውክሌር ቦምብ ጥቃት በጃፓን ከተሞች ላይ ስትፈጽም ለቦምቦቹ መሥሪያ የዋለው ዩራኒየም ከዲሞክራቲክ ኮንጎ የተገኘ መሆኑ ይነገራል።
የዩራኒየም ማዕድን በተለያየ ደረጃዎች ተጣርቶ ለኒውክሌር ጦር መሳሪያ የሚውል ሲሆን፣ የተለያዩ አገራት ማዕድኑ እንዳላቸው ይታመናል። ይህንን ማዕድን ከሚያመርቱ አስር ዋነኛ አገራት መካከል ሦስቱ የአፍሪካውያኑ ናሚቢያ፣ኒጀር እና ደቡብ አፍሪካ ናቸው።
ማዕድኑ ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውል ቢሆንም ለአውዳሚ ተግባር ጥቅም ላይ እንዳይውል በዓለም አቀፉ የአውቶሚክ ኃይል ኤጀንሲ አማካኝነት ቁጥጥር ይደረግበታል።

የትኞቹ አገራት ኒውክሌር ሊታጠቁ ይችላሉ?
በንድፈ ሀሳብ ደረጃ ትኛውም ቴክኖሎጂው፣ ዕውቀቱ እና ተቋሙ ያለው አገር የኒውክሌር ጦር መሳሪያን ሊታጠቅ ቢችልም፣ የኒውክሌር መስፋፋትን የሚገድበው ዓለም አቀፍ ስምምነት እዚህ ጋር ይመጣል።
ይህ በዓለም አገራት መካከል የኒውክሌር ጦር መሳሪያን መስፋፋት ለመከላከል የተደረሰው ስምምነት አውዳሚው መሳሪያ በሁሉም እጅ እንዳይገባ እንዲሁም ያሉትም እንዲወገዱ የሚያደርግ ነው።
ከአውሮፓውያኑ 1970 ወዲህ አሜሪካ፣ ሩሲያ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ፈረንሳይ እና ቻይናን ጨምሮ 191 አገራት ይህንን ስምምነት ፈርመዋል።
እነዚህ አምስት አገራት ከስምምነቱ በፊት የጦር መሳሪያውን ገንብተው እና ሞክረው ስለጨረሱ የኒውክሌር ጦር መሳሪያው እንዲኖራቸው ተፈቅዶላቸዋል።
ነገር ግን እነዚህ አገራት የኒውክሌር ጦር መሳሪያ እንዲኖራቸው ቢፈቀድላቸውም በስምምነቱ መሠረት እስከ መጨረሻው ይዘውት ለመዝለቅ ሳይሆን ያሏቸውን የኒውክሌር አረሮች ቀስ በቀስ እየቀነሱ እንዲያስወግዱ ይጠበቅባቸዋል።
የኒውክሌር ጦር መሳሪያ እንዳላት ያላረጋገጠችው ወይም ያላስተባበለችው እስራኤል፣ሕንድ እና ፓኪስታን ስምምነቱን አልፈረሙም እንዲሁም ሰሜን ኮሪያ ከ20 ዓመታት በፊት ከስምምነቱ ራሷን አግልላለች።















