". . . ከምድሩ ይልቅ የሰማዩን መንገድ ለመምረጥ ተገደናል" እገታ ያሰጋቸው መንገደኞች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አቶ ይበልጣል* ባሕር ዳር ከተማ ወደሚገኘው በላይ ዘለቀ አውሮፕላን ማረፊያ ሲያቀኑ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። ለአዲስ አበባ እንግዳ ባይሆኑም የሰማይ ላይ መንገዱን ግን አያውቁትም። ከዚህ ቀደም ወደ መዲናዋ የሚጓዙት በአውቶብስ ነበር። ያውም 'ታታ' በሚባለው አገር አቋራጭ አውቶብስ።
አሁን ግን ይህ ለእርሳቸው የማይታሰብ ሆኗል። በክልሉ በተከሰተው ግጭት ምክንያት ከሚኖሩበት መርዓዊ ከተማ ወደ ባሕር ዳር ያቀኑትም ዙሪያ ገባውን አጥንተው፣ ስለመንገዱ ሰላም መረጃ አሰባስበው ነው።
አቶ ይበልጣል ወደ አዲስ አበባ ለመጓዝ የተነሱት ላለቻቸው አነስተኛ ሱቅ ዕቃ ለማስጫን ነበር።
የአውሮፕላን ትኬቱ ዋጋ ከእርሳቸው አቅም አንጻር የሚቀመስ ባለመሆኑ ከዚህም ከዚያም ብለው ነው ትኬት የገዙት።
እርሳቸው እንደሚሉት ከሁለት ዓመት ገደማ በፊት 'ታታ' ባሉት አውቶብስ አዲስ አበባ ለመድረስ የከፈሉት 420 ብር ነበር። በተሻለ ዘመናዊ አውቶብስ ለመጓዝም ክፍያው ከ 1 ሺህ 600 ብር አይበልጥም።
አሁን ግን አቶ ይበልጣል ከአንድ ወር በፊት ወደ አዲስ አበባ ላደረጉት የአውሮፕላን ጉዞ 3500 ብር ለመክፈል ተገደዋል።
እርሳቸው ብቻም ሳይሆን ሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሚማረውን የእህታቸውን ልጅ እህል ሸጠው ባገኙት ገንዘብ የአውሮፕላን ትኬት ገዝተው እንደላኩት ይገልጻሉ።
"ይህም ቀድሞ ታቅዶ ካልሆነ ትኬት ማግኘቱ አስቸጋሪ ነው" ይላሉ።
ሆኖም በተደጋጋሚ በሚሰሙ የሰላማዊ ሰዎች እገታ፣ ግድያ እና ዘረፋ እንዲሁም በክልሉ ባለው ግጭት ምክንያት ከአውሮፕላን ጉዞ ውጪ ሌላ አማራጭ እንደሌለ ይናገራሉ።
ሁለት ዓመት ባለፈው በፋኖ እና ��ፌዴራል ኃይሎች መካከል እየተካሄደ ባለው ግጭት በክልሉ የሚገኙ ከተሞችን አቆራርጦ ወደ መዲናዋ መድረስ ፈተና ሆኗል። በክልሉ ያሉ ትናንሽ ከተሞችም እርስ በእርስ ያላቸው የየብስ ቁርኝት ላልቷል።
እነርሱን የሚያገናኝ ሰላማዊ መንገድም አንዴ ሲገኝ አንዴ ሲታጣ ሆኗል።
ከግጭቱ ባሻገርም በየጊዜው በተለይም ከአዲስ አበባ ወደ ጎጃም በሚወስደው መንገድ የሚፈፀመው እገታ በርካቶችን ስጋት ላይ ጥሏል።
ከአማራ ክልል ጋር በሚዋሰነው የኦሮሚያ ክልል፣ በተለምዶ 'አሊ ዶሮ' በሚባለው አካባቢ ሰላማዊ መንገደኞች እና አሽከርካሪዎች ላይ በተደጋጋሚ እገታ እና ግድያ ተፈፅሟል።
ሐምሌ ወር ላይ ከደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ወደ አዲስ አበባ ሲያቀኑ የነበሩ ከ100 በላይ ተማሪዎች ገርበ ጉራቻ ላይ ታግተው ከፍተኛ የማስለቀቂያ ገንዘብ ሲጠየቅባቸው የነበረ ሲሆን፣ የተወሰኑት የተጠየቀው ገንዘብ ከተከፈለ በኋላ ሊለቀቁ እንደቻሉ ቢቢሲ በወቅቱ ዘግቦ ነበር።
የኦሮሚያ ክልል የኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ሐምሌ 3/2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫም ተማሪዎቹ መታገታቸውን አረጋግጦ፣ ከታገቱት 167 ተማሪዎች መካከል 160 የሚሆኑት እንደተለቀቁ ገልጿል።
በዚያው መስመር ላይ በዚህ ዓመት መጋቢት ወር መጨረሻ ላይም በሁለት የሕዝብ ማመላላሻ አውቶብሶች ላይ እገታ ተፈፅሟል።
የኢትዮጵያ ትራንስፖርት አሠሪዎች ፌዴሬሽን ፕሬዚደንት ብርሃኔ ዘሩ፣ ጥቃት የተፈፀመበት አንደኛው አውቶብስ የፌደሬሽኑ አባል የሆነ ማኅበር ንብረት እንደሆነ ጠቅሰው፣ 'ቱሉ ሚልኪ' በተባለ አካባቢ በታጣቂዎች በተፈፀመበት ጥቃት ቢያንስ ስድስት መንገደኞች መጎዳታቸውን እና የአውቶብሱ ረዳት ሕይወት ማለፉን ለቢቢሲ ገልጸዋል።
እንደ አቶ ብርሃኔ ከሆነ የአውቶብሱ አሽከርካሪ ማምለጥ የቻለ ሲሆን፣ ሌሎች ታግተው የተወሰዱ መንገደኞችን የፌደራል የፀጥታ አካላት በሥፍራው ደርሰው ታድገዋቸዋል።
አውቶብሱ ከ50 በላይ መንገደኞችን አሳፍሮ ከባሕር ዳር ከተማ ወደ አዲስ አበባ እየተጓዘ ሳለ ነበር ድንገተኛ ጥቃቱ የተፈፀመበት።
የእገታ እና የታጣቂዎች ጥቃት በብዛት የሚፈፀምባቸው ገርበ ጉራቻ፣ ቱሉ ሚልኪ እና አሊ ዶሮ አካባቢዎች ከአዲስ አበባ በስተሰሜን 200 ኪሎሜትር በማይሞላ ርቀት ላይ የሚገኙ ናቸው።
በቅርቡ ወደ ዘርፉ የገባ 'ፈለገ ግዮን' የተባለ አውቶብስ 50 መንገደኞችን አሳፍሮ ከአዲስ አበባ ወደ ደብረ ማርቆስ እየተጓዘ ሳለ 'አሊ ዶሮ' በተባለ አካባቢ ሹፌሩ በጥይት ተመትቶ ተሳፋሪዎች ታግተው መወሰዳቸውን የጠቆሙት አንድ የትራንስፖርት ኅብረት ባለሥልጣን በበኩላቸው የየብስ ትራንስፖርቱ ዘርፍ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል ይላሉ።
በአማራ ክልል ባለው ግጭት እና በመንገድ ላይ በሚፈፀም እገታ ምክንያት በጎጃም መስመር የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብሶች ከደብረ ማርቆስ ማለፍ እንደማይችሉ እና ወደዚያ የሚያቀኑትም ከአንድ በመቶ እንደማይበልጡ ባለሥልጣኑ ይገልጻሉ።
"ከአራት ዓመት በፊት በዚያ መስመር በቀን ቢያንስ ከ30 እስከ 35 አውቶብሶች ይሰማሩ ነበር፤ አሁን ግን ደብረ ማርቆስ ድረስ ብቻ በቀን 5 አውቶብሶች ብቻ ናቸው የሚሄዱት። ይህም እንደ ሁኔታው ነው" ሲሉም ቁጥር ያጣቅሳሉ።
ታጣቂዎቹ በአንድ ጊዜ በርካታ ሰዎችን ለማገት ሲሉ የሕዝብ ማመላለሻዎችን ዒላማ እንደሚያደርጉ ይነገራል።
ታጋቾቹን ለመልቀቅም ከመቶ ሺዎች እስከ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ የሚጠይቁ ሲሆን፣ በአንዳንድ ሁኔታዎችም የመንገደኞችን ብሔር በመለየት ዒላማ እንደሚያደርጉ ከእገታ በሕይወት የተረፉ መንገደኞች ተናግረዋል።
ከመዲናዋ ወደ ጎጃም የሚወስደው አውራ መንገድ የአማራ እና የኦሮሚያ ክልሎችን የሚያገናኝ በመሆኑ የአማራ ክልል መንገደኞችን ዒላማ በማድረግ የብሔር ፖለቲካ ውጥረት ለመፍጠር ሲሉ ታጣቂዎቹ ድርጊቱን እንደሚፈፅሙ ፖለቲከኞች ሲናገሩ ይሰማል።
በአካባቢው በተለያዩ ጊዜያት ለተፈፀሙ እገታዎች እስካሁን ኃላፊነቱን የወሰደ አካል የለም።
ሆኖም በአካባቢው መንግሥት ኦነግ ሸኔ ሲል በሽብርተኝነት የፈረጀው እና ራሱን የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን እንደሚንቀሳቀስ ይነገራል። ታጣቂ ቡድኑ ከዚህ ቀደም የቀረበበትን ውንጀላ ያስተባበለ ሲሆን፣ መንግሥት ያደራጃቸው አካላት ድርጊቱን ይፈጽማሉ ሲል ከስሷል።
መንግሥት ለዚህ የሰጠው ምላሽ ባይኖርም በታጣቂዎቹ ላይ እርምጃ እየወሰደ እንደሆነ እንዲሁም ታጣቂዎቹ ለንግግር ወደ ጠረጴዛ እንዲመጡ በተደጋጋሚ ጥሪ አቅርቧል። ሆኖም ችግሩ አሁንም አልባት አላገኘም።

የፎቶው ባለመብት, SM
ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተለያዩ የአገሪቷ ትላልቅ ከተሞች ከመዲናዋ ጋር በምድር ለመገናኘት ፈተና ሆኖባቸዋል።
አሕመድ* የተባሉ የአሶሳ ከተማ ነዋሪ "በሰማይ ካልሆነ በምድር መገናኘት ቅንጦት ከሆነ ቆየ" ይላሉ።
በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከተማዋን ከአዲስ አበባ ጋር በሚያገናኙት ዋና አውራ ጎዳናዎች ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶች እና እገታዎች ነዋሪውን ከየብስ ጉዞ እንዳራቀ ይናገራሉ። አስገዳጅ ጉዞ ያለባቸው ነዋሪዎችም "ለአውሮፕላን ትኬት ለምነው፣ አሊያም ተበድረው" እንደሚንቀሳቀሱ እኝሁ ነዋሪ የታዘቡትን ገልጸዋል።
በቀን አንድ ጊዜ የነበረው የአውሮፕላን በረራ አሁን ላይ ስድስት እና ሰባት መድረሱንም ነዋሪው ይጠቅሳሉ።
በዚህም ላይ ከሰሜኑ ጦርነት በፊት ለአንድ ጉዞ ከ2 ሺህ እስከ 2 ሺህ 500 ብር የነበረው የአውሮፕላን ትኬት ዋጋ አሁን ከ7 ሺህ ብር በላይ ማሻቀቡንም ያክላሉ።
"አንድ ከፍተኛ የመንግሥት ሠራተኛ በወር 12 ሺህ ብር የተጣራ ደመወዝ ነው የሚያገኘው። ይህ ግለሰብ አስገዳጅ ሁኔታ ገጥሞት አንድ ጊዜ አዲስ አበባ መሄድ ቢኖርበት የደርሶ መልስ የትኬት ዋጋው ከደመወዙ በላይ ነው።" ሲሉም ነዋሪዎች ያሉበትን ሁኔታ ያስረዳሉ።
ግዮን ባስ፣ ልዩ ባስ እና ገዳ ባስን ጨምሮ ከ19 በላይ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብስ ተቋማትን በሥሩ የያዘው የልዩ ባስ ትራንስፖርት ኅብረት ባለሥልጣንም ባለፉት አራት ዓመታት ወደ በርካታ የአውቶብስ መዳረሻዎች መድረስ አዳጋች እንደሆነ ይናገራሉ።
"ከአራት ዓመት በፊት በአገር ውስጥ ቀርቶ እስከ ሱዳን መዲና - ካርቱም ድረስ የትራንስፖርት አገልግሎት ይሰጥ ነበር" የሚሉት ባለሥልጣኑ፣ አሁን ግን ባለንብረቶች አውቶብሶቻቸውን አንጻራዊ ሰላም ወዳለባቸው እንደ ጂማ፣ አርባ ምንጭ እና ጂግጅጋ ያሉ ከተሞች ማዞራቸውን ይገልጻሉ።
"መንግሥት 'ሂዱ' ሲለን እንሄዳለን . . . "
የፀጥታ ችግር ሲፈጠር የመጀመሪያው ተጠቂ ትራንስፖርት ነው የሚሉት የኢትዮጵያ ትራንስፖርት አሰሪዎች ፌዴሬሽን ፕሬዚደንት ብርሃኔ ዘሩ፣ መንግሥት በሚሰጣቸው አቅጣጫ መሠረት እንደሚሰማሩ ይገልጻሉ።
በአገር አቀፍ ደረጃ ወደ 12 የሚጠጉ የትራንስፖርት ማኅበራት ያሉ ሲሆን፣ ወደ ስምንት የሚጠጉት አቶ ብርሃኔ በሚመሩት ፌዴሬሽን ውስጥ አባል ናቸው።
በእነዚህ ማኅበራት ውስጥ ደግሞ 600 የሚሆኑ 'ደረጃ አንድ' እና 'ደረጃ ሁለት' የሕዝብ ማመላላሻ አውቶብሶች በክልል እና በዞን ዋና ዋና ከተሞች አገልግሎት ይሰጣሉ።
እነዚህ አውቶብሶች የሚሰማሩትም ከመንግሥት በሚደርሳቸው የፀጥታ ሁኔታ መረጃ ላይ ተመሥርቶ መሆኑን አቶ ብርሃኔ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
"መንግሥት በሚሰጠን አቅጣጫ መሠረት 'ሂዱ' ሲለን እንሄዳለን፤ 'የፀጥታው ሁኔታ አስጊ ነው' ሲለን ደግሞ እንቆማለን፤ በዚህ ደረጃ ነው ስንሠራ የቆየነው።" ይላሉ።
"ጦርነት ባለበት አካባቢ እንዲሁም መንግሥት ያረጋገጠው የፀጥታ ችግር ካለ 'ጥንቃቄ አድርጉ እና ሂዱ' ይላል፤ ካልሆነ ግን አጃቢ ያዘጋጃል" የሚሉት አቶ ብርሃኔ፣ ይህም ሆኖ ችግሮች እንደሚያጋጥሙ ያስረዳሉ።
ካለፉት ሁለት ዓመታት ገደማ ወዲህ በኦሮሚያ ክልል ያለው የፀጥታ ሁኔታ መሻሻሉን የሚጠቅሱት አቶ ብርሃኔ፣ ወደ ዞን እና ወደ ክልሉ ዋና ዋና ከተሞች አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
"መንግሥት 'በእኔ ሥር ነው፤ እኔ አለሁ' ወደሚላቸው ቦታዎች እንሄዳለን። በኦሮሚያ ክልል ግን እስካሁን የማንሄድበት ቦታ የለም" ይላሉ።
እርሳቸው ይህን ይበሉ እንጂ በክልሉ ባለው የታጣቂዎች እንቅስቃሴ እና የፀጥታ ችግር ምክንያት የትራንስፖርት እንቅስቃሴዎች መቋረጥ እና መስተጓጎል አሁንም የቀረ አይደለም።
ከአዲስ አበባ ወደ ድሬዳዋ በሚወስደው መንገድ 'መተሃራ' እና 'አውራ ጎዳና' በተባሉ አካባቢዎች የመንገደኞች እገታ እና ግድያ ዜናዎች ሲሰሙ ቆይተዋል።
ለደኅንነቱ ሲል ስሙን መግለጽ ያልፈለገ አንድ አሽከርካሪም ከአዲስ አበባ - ነቀምት - ጋምቤላ አውቶብሶች እንደማይሰማሩ፤ ነገር ግን አንዳንዶች እያቆራረጡ አጫጭር ርቀቶችን አገልግሎት እንደሚሰጡ ይናገራል።
አሁን ላይ አቅማቸው የፈቀደ ነዋሪዎች የአውሮፕላን ጉዞ እንደሚመርጡ የሚገልጸው አንድ ስሙን መጥቀስ ያልፈለገ የአካባቢው ነዋሪ፣ አየር ማረፊያ ወዳለባቸው ደንቢዶሎ እና ነቀምት ከተሞች መጓዝም ፈተና ስላለው ነዋሪዎች የግድ ካልሆነባቸው አለመንቀሳቀስን እንደሚመርጡ አስረድቷል።
"አባቴ ለእህቱ ቀብር ለመሄድ ለወትሮው በአውቶብስ አንድ ቀን ከግማሽ የሚወስደው መንገድ ከከተማ ከተማ በማቆራረጥ አንድ ሳምንት ፈጅቶበት ያውቃል" ይላል።
ቢቢሲ ያነጋገረው አንድ የአውቶብስ ስምሪት ባለሙያም ክልሉን አቋርጦ ጋምቤላ የሚደርስ የትራንስፖርት አገልግሎት ቢኖርም፣ ቀድሞ አንድ ቀን ይወስድ የነበረው መንገድ አሁን ላይ በሁለት ቀን ነው የሚገባው ይላል።
ምክንያቱም የፀጥታ ስጋት እና በየመንገዱ ላይ በሚደረጉ ፍተሻዎች ምክንያት የሚያጋጥም መጓተት እንደሆነ ያስረዳል።
ወደ ድሬዳዋ፣ መቀለ እና ሞያሌ አገልግሎት በሚሰጥ የአውቶብስ ድርጅት ውስጥ የሚሠራው የስምሪት ባለሙያው እንደሚለው በእነዚህ መስመሮች ላይ አሁን ላይ አንጻራዊ ሰላም ቢኖርም ከዚህ ቀደም ግን 'አውራ ጎዳና' የምትባል ቦታ ላይ ችግር ያጋጥማቸው እንደነበር ያስታውሳል።
ሆኖም አሁንም ቢሆን "የመንገድ ደኅንነቱን ሳያጣራ የሚሳፈር መንገደኛ የለም፤ ስጋቱ እንዳለ ነው" ይላል።
ወደ ትግራይ የሚደረገው የአውቶብስ ጉዞም አሁን ላይ ሰላም ቢሆንም አልፎ አልፎ ችግሮች እንደሚያጋጥሙ ይሰማል።
አቶ ብርሃኔ እንደሚሉትም ወደ መቀለ በየቀኑ ይሰጥ የነበረው የአገር አቋራጭ አውቶብሶች አገልግሎት በተሳፋሪ እጦት ምክንያት አሁን ላይ አገልግሎት የሚሰጠው በሁለት ወይም በሦስት ቀን አንድ ጊዜ ሆኗል። ይህም ቢሆን ሁልጊዜ የሚሆን አይደለም።
" 50 መንገደኞችን አሳፍሬ እያሽከረከርኩ ነው የተተኮሰብን"
በቅርቡ አንድ አሽከርካሪ ከአዲስ አበባ 50 መንገደኞችን አሳፍሮ ወደ መቀለ እየተጓዘ ሳለ በታጣቂዎች በተተኮሰበት ጥይት ጉዳት ደርሶበታል።
"መጋቢት 03/20217 ዓ.ም. መንገደኞችን አሳፍሬ ስጓዝ ከቀኑ 4፡00 ሰዓት ገደማ ገዋኔ አካባቢ 'አምቡሌ' ቀበሌ ውስጥ ነው ጥቃቱ የተፈፀመብኝ፤ ጥቃቱ የተፈፀመው በድንገት ነው። ምክንያቱን አላወቅንም" ይላል ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገው አሽከርካሪ።
"እዚያ አካባቢ መሣሪያ ይዞ መንቀሳቀስ የተለመደ ነው" የሚለውና ሆስፒታል ተኝቶ ሕክምና እየተከታተለ ሳለ ያነጋገርነው አሽከርካሪ፣ "ቀኝ እጄ ላይ ጉዳት ከደረሰ በኋላ እንደምንም መኪናውን አቁሜ ተሳፋሪዎችን አውርጀ በሌላ ተሽከርካሪ ወደ ከተማ አስጠጋናቸው" ይላል።
ከሰሜኑ ጦርነት በፊት ከአዲስ አበባ ወደ መቀለ የሚወስደው መደበኛ መንገድ አሁን ላይ ዙሪያ ጥምጥም ሆኗል።
በአማራ ክልል፣ ሰሜን ሸዋ ዞን በሚገኙት አጣዬ፣ ሰንበቴ እና ሸዋ ሮቢት ከተሞች በድንገት የሚፈጠረው ግጭት እና የመንገድ መዘጋት ወደ መቀለ የሚያቀኑ የሕዝብ ማመላ���ሻዎች ሌላ አማራጭ እንዲጠቀሙ አስገድዷል።
አሁን የሕዝብ ማመላለሻዎች ወደ ትግራይ የሚያቀኑት በአፋር ክልል በኩል አድርገው ነው። ጉዞው ረጅም በመሆኑ አሽከርካሪዎች በአንድ ቀን ለመግባት በሚያደርጉት ጥረት ምክንያት ለአደጋ ከማጋለጡ ባለፈ ደኅንነቱ የተጠበቀ አለመሆኑንም ቢቢሲ ያነጋገራቸው አሽከርካሪዎች እና የትራንስፖርት ማኅበር ባለሥልጣናት ይናገራሉ።
የትራንስፖርት አሠሪዎች ፌዴሬሽን ፕሬዚደንት አቶ ብርሃኔ እንደሚሉትም አሽከርካሪዎች ስጋት ባለባቸው አካባቢዎች ላለመመደብ ጥያቄ ያቀርባሉ።
ሆኖም "አገልግሎት ሰጭ ስለሆንን በተመደቡበት አልሄድም ማለት አይቻልም" በማለት በተመደቡበት እንዲሰሩ እንደሚደረጉ ይናገራሉ።
የሕዝብ ማመላለሻ አሽከርካሪዎች የሚመደቡት በየወሩ በሚወጣ የተሽከርካሪ ስምሪት መርሃ ግብር መሠረት ነው።
"ከመሃል አገር ጋር በምድር ተቆራርጠናል"
አሕመድ የተባሉት የአሶሳ ከተማ ነዋሪው ለቢቢሲ እንደገለጹት በግለሰብ ደረጃ የሚገጥማቸውን ለመቀበል ቆርጠው በመንግሥት መኪኖች እና ሚኒባሶች የሚንቀሳቀሱ ነዋሪዎች ቢኖሩም ይህንንም ማድረግ የሚችሉት መንገዱን በደንብ የሚያውቁ እና የዚያን አካባቢ ቋንቋ [ ኦሮምኛ] መናገር የሚችሉ ናቸው።
"ከአዲስ አበባ ወደ አሶሳ በቀጥታ ከመናኸሪያ ተነስተው የሚሄዱ አውቶብሶች የሉም። እነ ገዳ ባስ፣ ኦዳ ባስ፣ ሰላም ባስ አሁን አይሠሩም። የትኬት ቢሮዎቻቸውም ዝግ ናቸው" ብለዋል ነዋሪው።
ቢቢሲ ይህንን ዘገባ ሲያጠናቅር የኦዳ ባስ የኦንላይን የትኬት መሸጫ ገጽን የተመለከተ ሲሆን፣ ወደ አሶሳ ሥምሪት እንደሌለው ከገጹ መረዳት ችሏል።
በዚህም ምክንያት በመንገዶች ላይ በታጣቂዎች በሚፈፀሙ ጥቃቶች ምክንያት ነዋሪዎች ለሕክምና፣ ለንግድም ሆነ ለሥራ ወደ መዲናዋ ለመሄድ ውድ የሆነውን የአየር ትራንስፖርት ለመጠቀም መገደዳቸውን ይናገራሉ።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከአዲስ አበባ ወደ አሶሳ ለመጓዝ ከአውሮፕላን ውጪ የተሻለ አማራጭ የለም የሚሉት ነዋሪው፣ "ከመሃል አገር ጋር በምድር ተቆራርጠናል" ይላሉ።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ዋና ከተማ የሆነችውን አሶሳን ከአዲስ አበባ ጋር የሚያገናኙ ሁለት መንገዶች አሉ።
አንደኛው የወለጋ መስመር ሲሆን፣ ሌላኛው በመተከል - ጎጃም መስመር ወደ አዲስ አበባ የሚወስዱ ናቸው።
የወለጋው መንገድ ሲዘጋ ነዋሪዎች የመተከሉን መንገድ አማራጭ አድርገው የነበረ ቢሆንም፤ አሁን ግን አማራ ክልልን ተሻግሮ በሚገኘው የኦሮሚያ ክልል የሚፈፀሙ እገታዎች እና ጥቃቶች ይህም አማራጭ እንዳይኖር እንዳደረገው አቶ አሕመድ ይገልጻሉ።
በወለጋ መስመር መንዲ፣ ነጆ እና ጊምቢ፤ በመተከል መስመር ደግሞ በአዲስ አበባ አቅራቢያ የሚገኘው ገርበ ጉራቻ አስጊ ቦታዎች መሆናቸውንም ነዋሪው ይጠቅሳሉ።
"በአገሪቱ ያለው የፀጥታ ችግር ውጥረት ፈጥሯል፤ የሰዎችን የመንቀሳቀስ መብት ገድቧል" የሚሉት የትራንስፖርት አሠሪዎች ፌደሬሽን ፕሬዚደንቱም ዜጎች በየብስ ከመሄድ ይልቅ በአውሮፕላን እንደሚመርጡ እና አቅም የሌለው ብቻ ኃላፊነቱን ወስዶ እንደሚንቀሳቀስ ይገልጻሉ።
የመንገድ ሰላም እጦቱ የየብስ ትራንስፖርቱን እያዳከመ እና የመንገደኞችን ሕይወት አደጋ ላይ እየጣለ ቢሆንም፤ የአየር ትራንስፖርቱን ንግድ ያደራው ይመስላል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአገር ውስጥ በረራ ካለፈው ዓመት በ6 በመቶ መጨመሩን ለቢቢሲ ገልጿል።
ባለፈው ዓመት [ከአውሮፓውያኑ ሐምሌ 1/2023 እስከ መጋቢት መጨረሻ 2024] ባሉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ ወደ 2.6 ሚሊዮን የአገር ውስጥ መንገደኞች በአየር መንገዱ የተጓጓዙ ሲሆን፣ ይህ ቁጥር ከዘንድሮው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ወደ 2.8 ሚሊዮን ከፍ ብሏል።
የአየር መንገዱ የንግድ ዘርፍ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ለማ ያዴቻ፣ መቀለ እና ባሕር ዳር ከፍተኛ የበረራ ምልልስ ያለባቸው ከተሞች መሆናቸውንና በቀን በአማካይ ከ10 እስከ 12 በረራዎች እንደሚደረጉ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
አቶ ለማ እንዳሉት ከዚህ ቀደም በቀን አንድ እና በሳምንት ሦስት ወይም አራት ጊዜ በረራ ይደረግባቸው የነበሩ ጣቢያዎችም (ከአዳዲሶቹ በስተቀር) አሁን ላይ በቀን አንድ በረራ ያስተናግዳሉ።
ሆኖም ግን የበረራ ቁጥር ጭማሪው ከየብስ ትራንስፖርት መስተጓጎል ጋር የተገናኘ እንዳልሆነ አቶ ለማ ይገልጻሉ።
የአገር ውስጥ በረራ ላይ የታየው ጭማሪ ምክንያት ለማወቅ ጥናት እንደሚያስፈልግ የሚናገሩት አቶ ለማ፣ ምን አልባት የመሠረተ ልማቶች መሻሻል፣ መካከለኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች መበራከት፣ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ምልልስ እንዲሁም የንግድ እንቅስቃሴዎች መኖር ምክንያት ሊሆኑ እንደሚችሉ ይዘረዝራሉ።
ከዚህም በተጨማሪ እንደ ነቀምት እና ደምቢዶሎ ያሉ አዳዲስ የበረራ መዳረሻዎች ሥራ መጀመራቸው ለአገር ውስጥ በረራ እድገት አስተዋፅኦ ማድረጋቸውን ያክላሉ።
በአገር ውስጥ በረራ ላይ የታየው እድገት ከዓመት ዓመት የተለመደ እንደሆነ እና በአንድ ጊዜ የመጣ አለመሆኑን የሚገልጹት አቶ ለማ፣ ወደፊትም የአየር ምልልሱ ይጨምራል ተብሎ እንደሚጠበቅ ይናገራሉ።
"አንድ ጊዜ በአየር መጓዝ የለመደ ሰው፣ ገንዘብም ባይኖረው ወደ የብስ ትራንስፖርት የመመለስ ዕድሉ ከፍተኛ አይደለም" ይላሉ የአየር መንገዱ የንግድ ዘርፍ ኃላፊ።
ለጎንደር ነዋሪው አቶ ዳንኤል ግን አቶ ለማ የጠቀሷቸው ምክንያቶች አይዋጥላቸውም።
ነዋሪው "ሳንወድ በግድ ለአውሮፕላን ጉዞ ያለ አቅማችን ወጪ ለማውጣት ተገደናል" ይላሉ። ይህ ከሆነ ወደ ሁለት ዓመት እየተጠጋ ነው የሚሉት መንገደኛው፤ የመንቀሳቀስ መብታቸው ከመነጠቁም በላይ ገቢያቸው ከትራንስፖርት ሊዘል እንዳልቻለ ያስረዳሉ።
"ድሮ ድሮ አውሮፕላን የሚጠቀመው ገንዘብ ያለው ነበር፤ አሁን ግን ከገንዘብ ነፍስ ስለሚበልጥ ነፍስን ለማቆየት ሲባል ያለውም የሌለውም በአውሮፕላን እየተጠቀመ ነው" ይላሉ።
እርሳቸው እንደሚሉት ከጎንደር - አዲስ አበባ በአውቶብስ እስከ 2000 ብር ከፍሎ መጓዝ ቢቻልም በደኅንነት እጦት ምክንያት በአውሮፕላን እስከ 5 ሺህ 500 ብር ለማውጣት ተገደዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአገር ውስጥ በአጠቃላይ 22 መዳረሻዎች ያሉት ሲሆን፣ ከሁመራ ውጭ ወደ ሁሉም መዳረሻዎች ይበራል።
በዚህ ዓመት መጨረሻ ላይም መዳረሻዎቹ ወደ 28 ሊያድጉ ይችላሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም አቶ ለማ ለቢቢሲ በሰጡት ቃለ ምልልስ ጠቁመዋል።
የእገታ እና የመንገድ ፀጥታ ችግር ያለባቸው መንገዶች የትኞቹ ናቸው ?
ከአዲስ አበባ ተነስተው ወደ ሌሎች የአገሪቷ ክፍሎች የሚወስዱ አምስት በሮች ያሉ ሲሆን እነዚህም የጂማ፣ የአምቦ፣ የደብረ ብርሃን፣ የጎጃም እና የአዳማ መስመሮች ናቸው።
ከእነዚህ መካከል በተለይ ከመዲናዋ በሚወጡ ሦስት አቅጣጫዎች ላይ [ጎጃም፣ አዳማ፣ እና ደብረ ብርሃን] በሚያጋጥሙ ግጭቶች፣ እገታዎች፣ በአሽከርካሪዎች ጥቃት እና በዘረፋዎች ምክንያት መንገደኞች እና አሽከርካሪዎች ስጋት ላይ ወድቀዋል።
ቢቢሲ ከአሽከርካሪዎች፣ ከትራንስፖርት ማኅበራት ባለሥልጣናት እና ከመንገደኞች መረጃ አሰባስቦ የመንገድ ደኅንነት ችግር ያለባቸውን ቦታዎች ለመለየት ሞክሯል።
በዚህም ከአዲስ አበባ ወደ ጎጃም፣ አሶሳ እና ጋምቤላ የሚወስዱ መንገዶች ላይ የሚገኙ የተወሰኑ አካባቢዎች ለሕዝብ ማመላለሻ አውቶብሶች አደገኛ በመሆናቸው ተለይተዋል።
እንደ ቢቢሲ ምንጮች ከሆነ ከላይ ባለው ካርታ ላይ የተጠቀሱት አካባቢዎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መሻሻል የታየባቸው፤ ነገር ግን ሄድ መጣ በሚል ግጭት እና ጥቃት ምክንያት ለሕዝብ ማመላለሻ አውቶብሶች አስጊ የሆኑ አካባቢዎች ናቸው።
በአስጊነታቸው የተለዩት መንገዶች መዲናዋን ከሌሎች የአገሪቷ ዋና ዋና ከተሞች ጋር የሚያገናኙ ሲሆኑ፣ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብሶች ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ላይ ብቻ ትኩረት ተደርጎ የተለዩ ናቸው።
ዘገባው በአንዳንድ አካባቢዎች ከሥራ ቦታቸው እና ከመኖሪያ ቤታቸው በታጣቂዎች አሊያም 'ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች' ታግተው ስለሚወሰዱ ሰላማዊ ሰዎች እንዲሁም በተለይ ግጭት ባለባቸው ክልሎች ውስጥ አነስተኛ ከተሞችን በሚያገናኙ በመለስተኛ የሕዝብ ማመላለሻዎች ላይ ስለሚፈፀሙ የእገታ ወንጀሎች በቀጥታ አይዳስስም።
የመንገድ ደኅንነት ችግር የመንገደኞችን ሕይወት አደጋ ላይ ከመጣሉ ባሻገር በየብስ ትራንስፖርት ዘርፉ ላይ ከፍተኛ ኪሳራ እያስከተለ ሲሆን ለዋጋ ንረትም እንደ አንድ ምክንያትነት ይጠቀሳል።
በዘርፉ ላይ የደረሰውን ኪሳራ በአሃዝ ለማስቀመጥ ጥናት እንደሚያስፈልግ የሚገልጹት የትራንስፖርት ማኅበር ባለሥልጣኑ፣ የትራንስፖርት ዘርፉ የባንክ ዕዳውን ለመክፈል እና ለሠራተኞቹ ደመወዝ ለመክፈል እየተንገዳገደ እንደሚገኝ ይናገራሉ።
የትራንስፖርት አሠሪዎች ፌደሬሽን ፕሬዚደንቱም የተደራጀ ጥናት አለመኖሩን ጠቅሰው፣ ነገር ግን የየብስ ትራንስፖርቱ ዘርፍ ንግድ መቀነሱን ይገልጻሉ።
ከዚህም ባሻገር "የሰዎችን በነጻነት የመንቀሳቀስ መብት ገድቧል" የሚሉት ፕሬዚደንቱ፣ "ኢንደስትሪው ሰላማዊ እንዲሆን እና ኢኮኖሚው እንዳይጎዳ ትኩረት ሰጥተን ከመንግሥት ጋር እየሠራን ነው" ብለዋል።
ቢቢሲ አሁን ላይ ስላለው የመንገዶች ደኅንነት በተመለከተ ከፌደራል መንገዶች ባለሥልጣን መረጃ ለማግኘት ጥረት ያደረገ ሲሆን ባለሥልጣኑ የመንገድ ፀጥታ ችግር እንደማይመለከተው ገልጿል።
ሆኖም ከሁለት ዓመት በፊት የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳዳር በመንገድ ፕሮጀክቶቸ ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶች፣ የሠራተኞች እገታ ፕሮጀክቶቹን እያስተጓጎሉበት እንደሆነ መግለጹን ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቧል።
በ2015 ዓ.ም. የመጀመሪያ ዘጠኝ ወራት 17 የመንገድ ፕሮጀክቶች በፀጥታ ምክንያት የዲዛይን ሥራቸው ሙሉ በሙሉ መቋረጡን ተቋሙን ጠቅሶ ዘገባው አስነብቧል።
ከእነዚህ ፕሮጀክቶች መካከልም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚገኙ እንዳሉበት ተጠቅሷል። ለዚህም ዋነኛ ምክንያቱ በኦሮሚያ ክልል ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት ዕቃ ለማጓጓዝ ከነቀምት ማለፍ ባለመቻሉ እንደሆነ ተገልጿል።
ቢቢሲ መዲናዋን ከአገሪቷ የተለያዩ ክፍሎች የሚያገናኙ አውራ ጎዳናዎችን ደኅንነት የመጠበቅ ኃላፊነት ያለበትን የፌዴራል ፖሊስ አስተያየት ለማካተት የጠየቀ ቢሆንም የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊን አቶ ጄይላን አብዲ "የኦሮሚያ ክልል መንግሥትን ጠይቁ" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
የኦሮሚያ መንገድ ትራንስፖርት ባለሥልጣናትን እንዲሁም የፀጥታ ኃላፊዎችን አግኝተን ለማነጋገር ያደረግነው ጥረትም አልተሳካም።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን መስከረም ወር ላይ ባወጣው መግለጫ ማዕከላዊው መንግሥት በአማራ እና በኦሮሚያ የሚፈፀሙ እገታዎችን እንዲያስቆም ጥሪ አቅርቧል።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችም የዜጎች ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብት እንዲከበር መንግሥት ኃላፊነቱን እንዲወጣ እየጠየቁ ነው።
"የዜጎች የመንቀሳቀስ መብት በእገታ እና በግጭት ምክንያት ተገድቧል" የሚሉት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ያሬድ ኃይለማሪያም፣ ዜጎች አገሪቷ ውስጥ በነጻነት መዘዋወር የማይችሉበት አደገኛ ሁኔታ መፈጠሩን ይናገራሉ።
ይህም ጠንካራ የሆነ መንግሥታዊ መዋቅር አለመኖሩንና አገሪቷ አደገኛ ሁኔታ ላይ መሆኗን ማሳያ ነው ይላሉ።
"የአገሪቷን የንግድ እንቅስቃሴ፣ ዜጎች ተዘዋውረው የመሥራት መብታቸው አደጋ ላይ ወድቋል። ከዚህም ባሻገር በሚቀጥለው ዓመት ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀውን ምርጫ ማሰብም የሚቻል አይመስልም" ሲሉም ስጋታቸውን ይገልጻሉ።
በየቦታው ያሉ ታጠቂ ኃይሎች ተደራጅተው በዚሁ የሚቀጥሉ ከሆነም አንዳንድ የአፍሪካ አገራት ላይ እንደሚታየው ሁሉ ኢትዮጵያም ታጣቂ ኃይሎች የሚፈነጩበት አገር መሆኗ አይቀሬ እንደሆነ አቶ ያሬድ ያስጠነቅቃሉ።
____________
* ለደኅንነታቸው ሲባል ስማቸው የተቀየረ














