የጠቅላላ ዕውቀት እና የሂሳብ ምዘናን ያላለፉ እናቶች ልጆች ለማሳደ�� ብቁ አይደሉም በሚል ልጆቻቸውን የሚነጠቁበት አገር

ኪራ
የምስሉ መግለጫ, ኪራ

የ39 ዓመቷ ኪራ ልጇን እንደወለደች አብራት የቆየችው ለሁለት ሰዓት ብቻ ነበር።

"ገና እንደተወለደች ደቂቃውን እቆጥር ጀመር። ምን ያህል ጊዜ እንዳለን ለማወቅ የግድግዳ ሰዓቱን እያየሁ ነበር" ትላለች።

ልጇ ዛሚ ከእቅፏ ስትነጠቅ "አዝናለሁ፣ አዝናለሁ" እያለች አነባች። "ነፍሴን እንደተነጠቅኩ ተሰማኝ" ስትል ቅጽበቱን ትገልጻለች።

በግሪንላንድ ኪራን ጨምሮ በርካታ ወላጆች ልጆቻቸውን ለማስመለስ እየታገሉ ነው።

የወላጆችን ብቃት ለማረጋገጥ ኤፍኬዩስ (FKUs) የተባለ ምርመራ ይካሄዳል። የማኅበራዊ አገልግሎት ተቋም ወላጆች ብቁ አይደሉም ብሎ ካመነ ልጆቹን ይወስዳቸዋል።

በግሪንላንድ የዴንማርክ ግዛት ውስጥ የሚደረገው የብቃት ምርመራ ላይ መንግሥት እገዳ ጥሏል።

ይህ ምርመራ በበርካቶች ሲተች ቆይቷል። ወራት የሚወስደው ምርመራው ልጆች ለአደጋ ተጋልጠው እንደሆነ ለማወቅ የሚደረግ ነው።

ምርመራው ከልጆች እና ከወላጆቻቸው ጋር የሚደረግ ቃለ ምልልስን ያካትታል። ቁጥርን ከኋላ ወደፊት መጥራት፣ የጠቅላላ ዕውቀት ምዘና እንዲሁም የስሜት እና የማንነት ፈተናም ይሰጣቸዋል።

ምርመራው የሚካሄደው የወላጆችን ብቃት ለመፈተሽ ነው በሚል የሚከራከሩ ቢኖሩም አካሄዱን የሚነቅፉም አሉ።

ኪራ እና ልጇ
የምስሉ መግለጫ, ኪራ እና ልጇ

ምርመራው በትክክል የወላጆችን ብቁነት ለመመዘን አይሆንም በሚል የሚተቹም አሉ።

ምዘናው የሚደረገው በግሪንላንድ ቋንቋ ሳይሆን በዴኒሽ መሆኑ ክፍተት ይፈጥራል ብለው የሚከራከሩም በርካታ ናቸው።

የግሪንላንድ ነዋሪዎች የዴንማርክ ዜግነት ስላላቸው በዴንማርክ ሥራ መቀጠር ይችላሉ። ሆኖም ግን ፈተናው በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው አለመሰጠቱ ክፍተት ይፈጥራል።

በዴንማርክ ከሚኖሩ ወላጆች አንጻር ግሪንላንድ የሚኖሩ ወላጆች ልጆቻቸውን የመነጠቅ ዕድላቸው በ5.6 በመቶ ይጨምራል።

መንግሥት ወደ 300 የሚጠጉ የምርመራ ውጤቶችን እንደሚፈትሽ አስታውቋል።

ሆኖም እስካሁን ምርመራ የተደረገባቸው ጉዳዮች 10 ብቻ መሆናቸውን ቢቢሲ ለማወቅ ችሏል። ከምርመራ በኋላ ለወላጆቻቸው የተመለሱ ሕጻናት የሉም።

የኪራ ጉዳይ በ2024 ነበር የተመረመረው። ያኔ ነፍሰ ጡር ነበረች።

"ብቁ እናት አይደለችም፤ ልጇን መንከባከብም አትችልም" የሚል ብይን ተሰጠ።

ኪራ በወቅቱ ከቀረቡላት ጥያቄዎች መካከል ማዘር ቴሬሳ ማናት? የፀሐይ ብርሃን መሬት ላይ ለመድረስ ምን ያህል ጊዜ ይወስድበታል? የሚሉት ይጠቀሳሉ።

የኪራ ልጅ ልብሶች

የሥነ ልቦና ባለሙያዎች እንደሚሉት ከሆነ እነዚህ ጥያቄዎች የወላጆችን የጠቅላላ ዕውቀት በመመዘን በማኅበረሰቡ ውስጥ የሚኖራቸውን ሚና ለማወቅ ይረዳሉ።

"ከአሻንጉሊት ጋር ተጫወች አሉኝ እና በበቂ መጠን የአሻንጉሊቱን ዐይን አልተመለከትሽም ብለው ተቹኝ" ትላለች ኪራ።

"ፈተናው ምን ያህል ሥልጡን እንደሆንን ለማወቅ ይመስላል።"

የአካባቢው አስተዳደር እንደሚለው፤ ልጆች ከወላጆቻቸው እንዲነጠሉ የሚወሰነው ብቁ አይደሉም ተብሎ ከታመነ ነው። ስለ ኪራ ጉዳይ አስተያየት መስጠት እንደማይችልም ለቢቢሲ ገልጿል።

ዩልሪክ እና ጆአን
የምስሉ መግለጫ, ዩልሪክ እና ጆአን
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በአወሮፓወያኑ 2014 ሌሎች የኪራ ሁለት ልጆችም በማኅበራዊ አገልግሎት ተቋም ተወስደዋል። ያኔ ዕድሜያቸው ዘጠኝ ዓመት እና ስምንት ወራት ነበር።

የበኩር ልጇ ዞዊ አሁን 21 ዓመት ሆኗታል። 18 ዓመት ሲሞላት ወደ እናቷ ቤት ተመልሳለች።

ኪራ ልጇ ዛሚ እንደምትመለስላት ተስፋ አላት።

መንግሥት የሚያደርገው ምርመራ የወላጅነት ብቃት ምዘና ሲካሄድ ስህተት ተሠርቶ እንደሆነ ያጣራል።

ልጇን ለመጠየቅ ስትሄድ የግሪንላንድን ባህላዊ ምግብ እና አበባ ትወስድላታለች።

ዩልሪክ እና ጆአን ልጃቸው በማደጎ የተሰጠው በ2020 ነበር። ጆአን በ43 ዓመቷ ነፍሰ ጡር ሳለች ነበር የወላጅነት ምዘናውን የወሰደችው።

ልጃቸው 17 ቀን ሲሞላው ነበር የተወሰደው።

"እኔ እና አባቷ በ17ቱ ቀናት ደስታችን ወደር አልነበረውም። ልብሱን ስንቀይርነት፣ ሳጠባው በደስታ ነበር" ትላለች።

ድንገት ሁለት የማኅበራዊ አገልግሎት ሠራተኞች እና ፖሊስ በራቸውን አንኳኩ። ልጃቸው እንዳይወሰድ ቢማጸኑም ሰሚ አላገኙም።

"ልጄን ከመውሰዳቸው በፊት አንዴ ላጥባው ብዬ ለመንኳቸው። ለመጨረሻ ጊዜ ልብሱን ስቀይርለት ልቤ ክፉኛ ተሰበረ።"

ጆአን የወላጅነት ምዘናው ሲሰጣት የሁለት ልጆች እናት ነበረች።

በ2019 የተደረገላት ምርመራ ውጤት "ራስ ወዳድ እና የአእምሮ ዝግመት ያላት" ሲል ገልጿታል።

ሁለቱም አገላለጽ እሷን እንደማይወክል ትናገራለች።

የሥነ ልቦና ባለሙያ ኢሳክ ኔልማን እንደሚሉት፤ የምርመራው ውጤት ጥሩ ካልሆነ 90 በመቶ የሚሆኑት ወላጆች ልጆቻቸውን ይነጠቃሉ።

ምርመራው የወላጅነት ብቃትን እንዲሁም የሥነ ልቦና ሁኔታን ለመረዳት የሚያስችል እንዳልሆነ ይገልጻሉ።

ቱሪ ፍሬድሪክሰን የተባሉ ሌላ የሥነ ልቦና ባለሙያ በበኩላቸው የወላጅነት ምዘናውን ይደግፋሉ።

"ምርመራው ፍጹም ላይሆን ይችላል። ግን ጠቃሚ ነው" ይላሉ።

የወላጆች ተቃውሞ

ሰዎች ውስብስብ ምሥልን ተመልክተው የሚረዱትን እንዲገልጹ የሚጠይቀው የሥነ ልቦና ምዘና ለጆአን የተሰጣት በ2019 ነበር።

አንዲት ሴት ዓሣ ስትበልት መመልከቷን ገለጸች። ዓሣ መበለት በግሪንላንድ የሚዘወተር ነው። መርማሪዎቹ ግን "ኋላ ቀር ነሽ" ብለው የምርመራውን ውጤት ሰጧት።

የአካባቢው አስተዳደር ስለ ምርመራው ውጤት በቀጥታ ምላሽ አልሰጠም። ሆኖም ውጤቱ "ወላጅ ለመሆን ብቁ አለመሆናቸውን" እንደጠቆመ ገልጿል።

ጥንዶቹ እስካሁን ድረስ ልጃቸውን አላገኙም።

"ልጄ ድክ ድክ ሲል ሳላይ ቀረሁ፤ ጥርሱን ሲነቅል አላየሁም፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ትምህርት ቤት ሲሄድ አላየሁም" ትላለች ጆአን።

ልጃቸው እንደተወለደ ክርስትና ስላስነሱት በልጁ አገር አቀፍ ምዝገባ ሰነድ ላይ የወላጆቹ ስም ሰፍሯል።

ጠበቃቸው ጃኔት ጎራት ጉዳዩን ወደ አውሮፓ ኅብረት ሰብአዊ መብቶት ፍርድ ቤት እንደምትወስደው ተናግራለች።

ፒሊንጉክ ከልጇ ጋር
የምስሉ መግለጫ, ፒሊንጉክ ከልጇ ጋር

የዴንማርክ ማኅበራዊ ጉዳዮች ሚኒስትር ሶፊ ሀስቶርፕ አንደርሰን እንደሚሉት በማደጎ የተሰጡ ልጆች ጉዳይ ዳግመኛ አይከፈትም።

ልጆቹ "ለሚወዳቸው እና ለሚንከባከባቸው ቤተሰብ" እንደተሰጡ ይናገራሉ።

ልጆችን ከማደጎ ወላጆቻቸው መነጠል ረዥም እና ከባድ ሒደት መሆኑንም ገልጸዋል።

የማኅበራዊ አገልግሎት ሠራተኛዋ ቶርዲስ ጃኮብሰን እንደምትለው፤ ቅድሚያ የሚሰጠው ለልጆች ደኅንነት ነው።

ትምህርት ቤቶች አልያም ሆስፒታሎች ስለ ልጆች ደኅንነት ጥያቄ ሲያነሱ የወላጆች ብቃት ምዘና እንደሚካሄድ ታስረዳለች።

የ39 ዓመቷ ፒሊንጉክ በጣም ውስን ከሆኑ እና ልጃቸውን ካስመለሱ እናቶች አንዷ ናት።

ልጇ አንድ ዓመቷ ሳለች ነበር የተወሰደችባት። አሁን ስድስት ዓመት ሞልቷታል። ልጇን እንድትወስድ የስልክ ጥሪ ሲደርሳት ማመን አልቻለችም ነበር።

"እያለቀስኩ እስቅ ጀመር። ልጄ ወደ ቤቷ ልትመለስ ነው የሚለውንማመን አቃተኝ።"

ሦስቱም ልጆቿ በማኅበራዊ አገልግሎት ተቋም የተወሰዱት በ2021 ነው። በወቅቱ ሁለቱ ልጆቿ የስድስት እና ዘጠኝ ዓመት ታዳጊዎች ነበሩ።

ለልጆቿ ምቹ መኖሪያ እስክታገኝ ድረስ በማኅበራዊ አገልግሎት ተቋም ሥር እንዲሆኑ ተወሰነ።

"አደገኛ የፍቅር ግንኙነቶች ትጀምራለች" በሚል ነበር ልጆቿን የተቀማችው።

አንደኛዋ ልጇ ከተመለሰች በኋላ የተቀሩት ሁለቱ ልጆቿም እንደሚመለሱላት ተነግሯታል።

ከልጇ ጋር ለአራት ዓመታት መነጣጠል ቀላል አልነበረም። የእናት እና ልጅ ግንኙነታቸውን ለማደስም ጊዜ ወስዶባታል።

"ሽንት ቤት ስገባ ትደነግጣለች። እማዬ የት ሄደሽ ነው? ብላ ታለቅሳለች። አሁንም መልሰው ሊወስዱብኝ ይችላሉ።"

ልጇን መልሳ ያላገኘችው ኪራ እቅፏ ውስጥ የሌለችው ልጇን አንደኛ ዓመት ልደት ለማክበር እየተዘጋጀች ነው።

ኪራ አሁንም ተስፋ አልቆረጠችም። የልጇን አልጋ አሰናድታ እስከምትመለስ ትጠብቃለች።

"ልጆቼን አስመልሳለሁ። እኔ ባላሸንፍ እንኳን ለልጆቼ ትግሉን አወርሳለሁ።"

ባነር