የአንገታችን መጠን ስለ ጤናችን ምን ይነግረናል?


የአንድን ሰው ከአገጭ እስከ አንገት ድረስ የሚያሳይ ምስል። የአንገት ቆዳው የላላ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የአንገታችን መጠን ከተለመደው በተለየ ከቀጠነ ወይም ከወፈረ ያለንበትን የጤና ሁኔታ ሊያመለክት ይችላል

ብዙውን ጊዜ ክብደት እንደጨመርን የምናስተውለው የሆዳችን ክፍል መጠን ሲጨምር አሊያም ልብሶቻችን መጥበብ ሲጀምሩን ነው።

ነገር ግን አብዛኛው ሰው የማያስተውለውና ስለ ጤናችን ሁኔታ ፍንጭ የሚሰጠን አንድ የአካል ክፍል አለን። እርሱም አንገታችን ነው።

አንገታችን ከተለመደው በተለየ ከወፈረ አሊያም ከቀጠነ የተወሰነ የጤና ችግር ማስጠንቀቂያ ሊሆን ይችላል።

አንገታችን ምን ያህል ሊወፍር ይገባል?

በሰውነታችን ውስጥ ያለን የስብ መጠን የምንገምተው ክብደታችን ለቁመታችን በማካፈል የምናገኘው (ቢኤምአይ) ስሌት ነው።

ይህ ጥሩ ቢሆንም አካላቸውን እንደሚገነቡ [ቦዲ ቢዩልደር ) ላሉ በርካታ ሰዎች አይሰራም። ምክንያቱም ስሌቱ የስብ እና የጡንቻ መጠናቸውን ለይቶ ስለማያስቀምጥ ጡንቻዎቻቸው ከባድ ክብደት እንዲኖራቸው ስለሚያደርግ ነው።

ለዚህም ነው የአንገታችንን ዙሪያ መጠን መለካት ስለጤናችን ተጨማሪ ፍንጭ ለማግኘት የሚረዳን። ለመሆኑ የአንገታችን መጠን ምን ያህል ሊሆን ይገባል?

የደልሒ የአይኤልቢኤስ ሆስፒታል ዳይሬክተር እና የብሔራዊ የጤና ሳይንስ አካዳሚ ፕሬዚደንት የሆኑት ዶ/ር ሺቭ ኩማር ሳሪን፣ "የሴቶች የአንገት መጠን ከ33 እስከ 35 ሴንቲሜትር ሲሆን የወንዶች ደግሞ ከ37 እስከ 40 ሴንቲሜትር ሊሆን ይገባል" ይላሉ።

የአንገታችን ውፍረት ጠቃሚ የሚሆነው ለምንድን ነው?

አንዳንድ ሰዎች አንገታቸው ጠንካራ እንዲሆን ክብደት ያነሳሉ። እንደ ቦክሰኞች እና ራግቢ ተጫዋቾች ያሉ ስፖርተኞች ወፍራም አንገት መገንባት ይችላሉ። ሆኖም ከጂምናዚየም ውጭ ይህ ማድረግ ሁልጊዜም ጥሩ አይደለም።

በሕንድ ፑን ከተማ በሚገኘው ዲዋይ ሜዲካል ኮሌጅ ፕሮፌሰር የሆኑት አሚታቭ ባነርጅ " የአንድ ሰው አንገት ከተለመደው ውጭ ወፍራም ከሆነ፣ ከልክ ወዳለፈ ውፍረት እየተሸጋገረ እንደሆነ እና የጤና ችግር እንዳለበት ያመለክታል" ብለዋል።

በአንገታችን ዙሪያ የሚገኝ ስብ፣ 90 በመቶ ከሆነው የሰውነታችን ስብ ከሚገነባውና በዳሌያችን አካባቢ እንዳሉ የሰውነት ክፍላችን ቆዳ ሥር ከሚገኝ ስብ የተለየ ነው።

በመሆኑም ከልክ ያለፈ ክብደት ካለን ሰውነታችን በሆዳችን አካባቢ እና በውስጣዊ የሰውነት ክፍሎቻችን ድብቅ ስቦችን ያከማቻል። ይህም በጉበት፣ በጨጓራ እና በአንጀት ላይ የሚከማች (ቪሴራል) ስብ ይባላል።

ይህ ስብ ዝም ብሎ የተከማቸ አይደለም። የሜታቦሊዝም ሥርዓትን ያስተጓጉላል። ሜታቦሊዝም ወደ ሰውነታችን የሚገባውን ምግብ ወደ ኃይል የሚቀየርበት ሥርዓት ነው።

በመሆኑም የተከማቸው ስ��� በዚህ ሥርዓት ውስጥ ንቁ በመሆን በደም ውስጥ በሚገኝ የስኳር፣ የኮሌስትሮል እና የደም ግፊት መጠን ላይ ተፅእኖ ያሳድራል።

"አንገታችን ደግሞ ይህ ከሚታይባቸው የሰውነት ክፍላችን መካከል ሲሆን በሰውነታችን ውስጥ ምን ያህል አላስፈላጊ ስብ እንዳለ ያመለክታል" ይላሉ በለንደን በሚገኘው ኪንግስተን ዩኒቨርሲቲ ባዮኬሚስትሪ ትምህርት ክፍል ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር አሕመድ ኢልቤዲውይ።

"ከልክ በላይ ክብደት ሲኖረን የአንገታችን መጠንም ይጨምራል" ብለዋል።

የአንገታችን መወፈር ምን ዓይነት ችግር ያስከትላል?

የአንድ ሰው አንገት ከተለመደው በተለየ ወፍራም ከሆነ ለልብ፣ ለደም ቧንቧ፣ ለዓይነት 2 የስኳር በሽታ የሚያጋልጥ የሜታቦሊዝም ችግር እንዳለበት ሊያመለክት ይችላል።

ምክንያቱም በሰውነታችን ውስጥ ከልክ ያለፈ ስብ ካለ ተጨማሪ ስቦች በደም ማስተላለፊያ ቱቦ ውስጥ ይገባሉ ማለት ነው።

በደልሒ ሰር ጋንጋ ራም ሆስፒታል ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት ዶ/ር ሞሺን ዋሊ እንደሚሉት ወፍራም አንገት ያለው ሰው ከፍተኛ መጠን ያለው ኮሌስትሮል፣ የጉበት ስብ እና የደም ግፊት ሊኖርበት ይችላል። ይህም ልዩ ምርመራ ያስፈልገዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በእንቅልፍ ሰዓት የአየር ማጠር ሊያስከትል ይችላል።

አንገታችን ቀጭን ቢሆንስ ?

የኪንግስተን ዩኒቨርሲቲው ባለሙያ ዶ/ር አሕመድ ኤልቤዲዊይ እንደሚሉት አንገታችን ቀጭን ቢሆን መደናገጥ የለብንም።

"ጤናማ አመጋገብ እና መደበኛ አካላዊ እንቅስቃሴ ለአጠቃላይ ጤናችን እንዲሁም ክብደት ለመቀነስ ይረዳናል" ብለዋል።

አካላዊ እንቅስቃሴ እና የክብደት ሥልጠናዎች ከወገብ በላይ ያለውን የሰውነት ክፍል ስብ ለመቀነስ ይረዳል። ከዚህም በተጨማሪ ጥራት ያለው እንቅልፍ የሜታቦሊዝም ሥርዓታችንን ለመቆጣጠር ይረዳል። የተመጣጠነ ምግብ ማለትም ፍራፍሬዎች እና አትክልቶች ያለ አላስፈላጊ ካሎሪ ጠቃሚ የሆኑ ንጥረ ነገሮችን ይሰጡናል።


በያዘችው ስልክ በቪዲዮ እያወራች አንገቷን የምትመለከት ሴት ምስል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አንገት ከተለመደው በተለየ ከቀጠነ የደም ማነስ ምልክት ሊሆን ይችላል

በጣም ከቀጠነስ?

ቀጭን አንገት ከአካላዊ ውበት ጋር ይያያዛል። ሰዎች ትኩረትን ለመሳብ በአንገታቸው ላይ ጌጥ ያደርጋሉ። ይህም ቆንጆ ሆነው እንዲታዩ ያደርጋቸዋል።

በአንዳንድ የአፍሪካ አገራት ሴቶች አንገታቸው ቀጭን እና ረጅም እንዲሆንላቸው የተለዩ ጌጣ ጌጦች ያደርጋሉ።

ምንም እንኳን ይህ የውበት መለኪያ ተደርጎ ቢወሰድም ከተለመደው በተለየ ቀጭን የሆነ አንገት የደም ማነስ ምልክት ሊሆን እንደሚችል የሕክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ።

" እንዲህ ዓይነት ሰዎች አይረን፣ ቫይታሚኖች እና ሌሎች አጋዥ ንጥረ ነገሮች ይሰጣቸዋል።በአብዛኛው ወደ የደም ልገሳ ሊያመራ ይችላል።" ይላሉ በሕንድ ቤንጋሉሩ ከተማ ተቀማጭነታቸውን ያደረጉት ዶክተር አትሪያ ኒሃራቻንድራ።

አንገቷ ላይ ከጨሌ የተሰራ ትልቅ ጌጥ ያደረገች ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የአንገት ቀለበት የአፍሪካዊነት መገለጫ ተደርጎ ይወሰዳል።

ቀጭን አንገት ያላቸው ሰዎች በጀርባ አጥንታቸው ላይ ተጨማሪ አጥንቶች ሊኖራቸው ይችላል። በአከርካሪ አጥንታችን ሰባት ትንንሽ አጥን��ች [ቨርቴብራ] ያሉ ሲሆን አንዳንድ ሰዎች ስምንት ይኖራቸዋል። ልክ በአንዳንድ ሰዎች ላይ ስድስተኛ ጣት እንደሚኖረው ማለት ነው።

ቨርቴብራ፣ አከርካሪ አጥንታችንን የሚገነቡ የጀርባ አጥንቶች ናቸው። እነዚህ አጥንቶች የሰውነታችን ቅርጽ ለመጠበቅ አከርካሪ አጥንታችንን እና ነርቮቻችንን ይጠብቃሉ።

ምንም እንኳን ስንወለድ ጀምሮ ያሉ ቢሆንም በሆነ አጋጣሚ አንገታችንን ኤክስ ሬይ በምንነሳበት ጊዜ ይታያሉ። ብዙውን ጊዜም ችግር አያስከትሉም።

" በአንዳንድ ሁኔታዎች የቨርቴብራ አጥንቶች ቁጥር ከስምንትም ሊበልጥ ይችላል። ይህም በእጃችን ላይ የመደንዘዝ ስሜት ዓይነት ሕመሞችን ሊያስከትሉ እንደሚችሉ ዶ/ር ዋሊ ይናገራሉ።

ሌላኛው በአንገት ላይ የሚታየው እንቅርት (ጎይተር) ነው። በአንገታችን አካባቢ የሚታይ እብጠት - እንቅርት በአንገታችን የፊተኛው ክፍል ባበጡ የታይሮይድ እጢዎች ምክንያት የሚከሰት ነው። ታይሮይድ ሆርሞንን የሚያመነጭ እጢ ነው።

እንቅርት ብዙውን ጊዜ የሚከሰተው በታችኛው የአንገታችን ክፍል ሲሆን የሚለሰልስ እና ያበጠ ዓይነት ስሜት አለው።አንዳንድ ጊዜ በአንድ በኩል ብቻ ሊያብጥ ይችላል።

እንቅርት ብዙውን ጊዜ ሕመም የለውም፤ ጎጂም አይደለም ።ሆኖም በሕክምና መከታተል እንደሚያስፈልግ የዩናይትድ ኪንግደም ብሔራዊ የጤና አገልግሎት ይመክራል።

በመሆኑም ራሳችሁን በመስታዎት ስታዩ አንገታችሁን ቀረብ ብላችሁ ተመልከቱ። ከምታስቡት በላይ ስለ ጤናችሁ ሁኔታ የሚነግራችሁ ሊኖር ይችላል።