የኒውዚላንድ ፖሊስ 19 ሺህ ዶላር የሚያወጣ የአልማዝ ሃብል ሰርቆ የዋጠ ግለሰብን በቁጥጥር ስር አዋለ

በአልማዝ የተንቆጠቆጠው ሃብል

የፎቶው ባለመብት, New Zealand Police

በአልማዝ የተንቆጠቆጠ ሃብል በመስረቅ የዋጠውን ግለሰብ በቁጥጥር ስር ማዋሉን የኒውዚላንድ ፖሊስ ገለጸ።

የአልማዙ ዋጋ 19,300 ዶላር ሲሆን "በተፈጥሯዊ" መንገድ ተገኝቷል፤ "የሕክምና ጣልቃ ገብነት አላስፈልግም" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።

የ32 ዓመቱን ግለሰብ በማዕከላዊ ኦክላንድ በሚገኘው የጌጣጌጥ መሸጫ ሃብል መስረቁ ታውቆ በደቂቃዎች ውስጥ በቁጥጥር ስር ከዋለ ከአንድ ሳምንት ገደማ በኋላ ነው።

የተወሰደው ሃብል በ60 ነጭ አልማዞች፤ በ15 ሰማያዊ ሳፋየር እና 18 ካራት የወርቅ የተሠራ መሆኑ ታውቋል።

ግለሰቡ በስርቆት ክስ ተመስርቶበታል።

የኒውዚላንድ ፖሊስ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ እንደገለጸው ግለሰቡ የሕክምና ምርመራ ተደርጎለት ያለማቋረጥ ክትትል እየተደረገበት መሆኑን ገልጾ ነበር።

"ይህ ሰው በፖሊስ ቁጥጥር ስር ስለሆነ፣ የተከሰተውን ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት ክትትል የማድረግ ኃላፊነት አለብን" ሲል ፖሊስ በወቅቱ ተናግሯል።

የኦክቶፑስ ኤግ የተባለው ሃብል በ1983 ከወጣው እና ተመሳሳይ ስም ካለው የጄምስ ቦንድ ፊልም ሃሳብ ተወስዶ የተሠራ ነው።

ሃብሉ ወደ መሸጫ ሱቁ እንደሚመለስ ታውቋል።

ተጠርጣሪው ታህሳስ 8 ቀን እንደገና በፍርድ ቤት እንደሚታይ ይጠበቃል።

ግለሰቡ ኅዳር 12 ቀን ከተመሳሳይ የጌጣጌጥ መደብር አይፓድ በመስረቅ እና ከአንድ ቀን በኋላ ደግሞ 60 የአሜሪካን ዶላር የሚያወጡ የድመት መጸዳጃ እና የተባይ መቆጣጠሪያ ምርቶችን ከግለሰብ በመስረቅ መከሰሱን ቢቢሲ ከክስ መዝገቡ ተመልክቷል።