የዜጎችን የጤና መረጃ አሳልፎ ይሰጣል በሚል ስጋት የፈጠረው የኬንያ እና የአሜሪካ ስምምነት

 የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ እና የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ተጨባብጠው

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ስምምነቱን የፈረሙት የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ እና የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ

የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር የአሜሪካ መንግሥት የውጭ ዕርዳታ መርሃ ግብር ላይ ክፍተኛ ለውጥ ካደረገ በኋላ ታሪካዊ የተባለውን የመጀመሪያውን የአምስት ዓመት የጤና ትብብር ስምምነት ከኬንያ ጋር ተፈራረመ።

ይህ የ2.5 ቢሊዮን ዶላር ስምምነት በኬንያ ተላላፊ በሽታዎችን ለመዋጋት የታለመ ነው ተብሏል።

ከትራምፕ ሰፊ የውጭ ፖሊሲ ግቦች ጋር ይጣጣማል የተባለው ይህ ስምምነት ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ጋርም ይፈረማል ተብሎ ይጠበቃል።

በሁለቱ መንግሥታት መካከል የተደረሰው ይህ ስምምነት ግልፅነትን እና ተጠያቂነትን ለማጎልበት የታሰበ መሆኑ ቢነገርም፣ ምሥጢራዊነት ያላቸውን የሕሙማን መረጃን ጨምሮ ወሳኝ የመረጃ ስብስቦችን አሜሪካ በቀላሉ ማግኘት እንድትችል ያደርጋታል የሚል ስጋት ፈጥሯል።

የኬንያ የጤና ሚንስትር አደን ዱዋሌ መረጃዎች ተላልፈው ይሰጣሉ የሚለውን ስጋት ለማስወገድ "ማንነትን የማይለዩ፣ ጥቅል መረጃዎች ብቻ" ይጋራሉ ብለዋል።

ባለፈው ዓመት ጥር ወር ላይ ትራምፕ ሥልጣን በተረከቡበት የመጀመሪያ ቀን በመንግሥት ወጪ ላይ በሚያደርጉት ክለሳ ምክንያት የውጭ ዕርዳታ መቆሙን አስታውቀዋል።

ይህንን ተከትሎም የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ልማት ደርጅት (ዩኤስኤአይዲ) መፍረሱን እና ለድሃ አገራት የሚሰጠው በቢሊዮኖች የሚቆጠር ዕርዳታ ማቋረጡ ይታወሳል።

ይህ ውሳኔም በማደግ ላይ ባሉ አገራት ውስጥ የአንዳንድ መድኃኒቶች አቅርቦት በከፍተኛ ሁኔታ እንዲያሽቆለቁል ምክንያት ሆኗል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በዚህ ዓመት መጀመሪያ መስከረም ላይ የትራምፕ አስተዳደር "አሜሪካ ፈርስት ግሎባል ሄልዝ ስትራቴጂ" የተባለ የዕርዳታ ብክነትን የሚቀንስ እና አሜሪካ ቅድሚያ የምትሰጣቸው ጉዳዮች ላይ ያተኮረ በድርድር ላይ የተመሠረተ የዕርዳታ ሥርዓት ይፋ ተደርጓል።

አሁን ከኬንያ ጋር በተደረሰው ስምምነት መሠረተ አሜሪካ 1.7 ቢሊየን ዶላር ስታበረክት፣ የኬንያ መንግሥት 850 ሚሊየን ዶላር በመሸፈን ቀስ በቀስ ደግሞ ተጨማሪ ኃላፊነቶችን እንዲወስድ ይደረጋል ተብሏል።

ስምምነቱ የኤችአይቪ/ኤድስ፣ የወባ እና የሳንባ በሽታ፣ የእናቶች ጤና እንክብካቤ፣ የፖሊዮ በሽታን ማስወገድ እንዲሁም ለተላላፊ በሽታዎች ወረርሽኝ ምላሽ ዝግጁነት፣ መከላከል እና ሕክምና ላይ ትኩረት ያደረገ ነው።

ከኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ጋር ስምምነቱን የተፈራረሙት የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ስምምነቱን "ታሪካዊ" በማለት ኬንያን "የረጅም ጊዜ የአሜሪካ አጋር" በማለት ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም ኬንያ በሄይቲ ያሉ የወሮበላ ቡድኖችን ለመዋጋት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሚደገፈውን ተልዕኮ በመምራት እና ተሳታፊዎችን በማዋጣት ረገድ ኬንያ ስላላት ሚና አመስግነዋል።

ሩቢዮ "አምስት ወይም 10 አገራትን ማሳተፍ ብንችል እና ኬንያ ካደረገችው ግማሹን ብቻ ብናከናውን የላቀ ስኬትን ማግኘት ይቻላል" ብለዋል።

የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መንግሥታቸው ድጋፎች በዕርዳታ እና በጎ አድራጎት ድርጅቶች በኩል ሳይሆን በቀጥታ በመንግሥታት በኩል እንዲደርስ እንደሚፈልግ አስረድተዋል።

"እንደ ኬንያ ያሉ የቅርብ እና ጠቃሚ አጋሮች ለጤና አጠባበቅ የሚወጣው ገንዘብ እንዴት ጥቅም ላይ እንደሚውል ሚና ሳይኖራቸው በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር መንግሥታዊ ላልሆኑ ድርጅቶች አንሰጥም" ብለዋል።

የኬንያ ፕሬዝዳንት ከአሜሪካ የሚገኘው ገንዘቡ አገራቸው ቅድሚያ ለምትሰጣቸው ጉዳዮች ማለትም ለሆስፒታሎች ዘመናዊ መሣሪያዎችን ለመግዛት እና የጤና ሠራተኞችን ቁጥር ለማሳደግ እንደሚውል ተናግረዋል።

ዊሊያም ሩቶ አክለውም "እያንዳንዱ ሺሊንግ እና እያንዳንዱ ዶላር በተገቢው ሁኔታ፣ በብቃት እና በተጠያቂነት እንደሚወጣ አረጋግጣለሁ" ብለዋል።

አንዳንድ ኬንያውያን ይህ ስምምነት ዩናይትድ ስቴትስ እንደ የኤችአይቪ፣ የቲቢ ሕክምና ታሪክ እና የኬንያውያንን የክትባት መረጃዎችን የመሳሰሉ የግል የሕክምና መረጃዎችን እንድታገኝ ያደርጋታል በሚል ስጋት ሙሉ የስምምነቱ ይዘት እንዲገለጽ እየጠየቁ ነው።

"ለአሜሪካ እንዲጋሩ የሚደረጉት ምን ዓይነት ልዩ የመረጃ ምድቦች ናቸው? የዘረ መል መረጃ፣ የበሽታ ክስተት ሁኔታ፣ የአእምሮ ጤና መረጃዎች፣ የኢንሹራንስ ክፍያ ጥያቄዎች፣ የሆስፒታል መዛግብት ወይም ባዮሜትሪክስ? እነዚህን የሚያካትት ካልሆነ ለምን በግልጽ አልተጻፈም?" በማለት ጠበቃ ዊሊስ ኦቲኖ በኤክስ ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።

ታዋቂው ኬንያዊ ምሥጢር አጋላጭ ኔልሰን አመንያ ተመሳሳይ ስጋቶችን በማንሳት የኬንያ መንግሥት ሙሉውን የስምምነቱን ይዘት ለሕዝብ ይፋ እንዲያደርግ በማለት "ራሳችን እናንብበው" ሲሉ ጠይቀዋል።

የጤና ሚኒስትሩ ዱአሌ ግን የኬንያውያን የጤና መረጃ ደኅንነቱ የተጠበቀ እና በኬንያ ሕጎች ሙሉ በሙሉ ጥበቃ የሚደረግለት መሆኑን በመግለጽ ስጋቱን ውድቅ አድርገውታል።

ለዚህም ማስተማመኛ "የጤና መረጃዎች በሙሉ ወሳኝ አገራዊ ሀብቶች ናቸው" በማለት አስፈላጊው ጥበቃ እንደሚደረግላቸው አረጋግጠዋል።

የአሜሪካ ባለሥልጣናት ግን ከኬንያ የሚጋሩትን የጤና በመረጃዎችን በተመለከተ በተነሳው ስጋት ላይ እስካሁን አስተያየት አልሰጡም።

የአሜሪካ ባለስልጣናት እንደሚሉት ከኬንያ በተጨማሪ ሌሎች በርካታ የአፍሪካ አገራት እየተጠናቀቀ ባለው የአውሮፓውያን ዓመት ውስጥ ተመሳሳይ ስምምነት ይፈራረማሉ ተብሎ ይጠበቃል።