ኢትዮጵያውያን ጥገኝነት ጠያቂዎች በአሜሪካ ምን ዓይነት ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው?

አንድ ስደተኛ በፖሊሶች ተየዞ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ባለፈው ዓመት ሐምሌ ላይ የአሜሪካ የፀጥታ ሠራተኞች አንድ ስደተኛን የስደተኞች ጉዳይ ከሚታይበት ችሎት ይዘው ሲወጡ

ዋሽንግተን ውስጥ አንድ አፍጋናዊ ስደተኛ በሁለት የአሜሪካ የብሔራዊ ዘብ አባላት ላይ ጥቃት ከፈጸመ በኋላ የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር የጥገኝነት ጥያቄዎችን በአጠቃላይ አግዷል።

የአሜሪካ የዜግነት እና ስደተኝነት አገልግሎት ሁሉም ጥገኝነት ጠያቂዎች ላይ ተገቢው ምርመራ እስከሚካሄድ ድረስ እገዳው ጸንቶ እንደሚቆይ አሳውቋል።

ትራምፕ "የሦስተኛው ዓለም አገራት" ስደተኞች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ የሚያደርግ "ዘላቂ ዕገዳ" ለመጣል ዕቅድ እንዳላቸው ካመለከቱ በኋላ በአሜሪካ ለሰደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ያለው ሁኔታ አስጨናቂ ሆኗል።

የአሜሪካ ብሔራዊ ዘብ አባላትን ያቆሰለው እና የገደለው አፍጋኒስታናዊ ስደተኛ በመሆኑ የአሜሪካ መንግሥት ከአፍጋኒስታናውያን የሚቀርቡ የጥገኝነት ጥያቄዎችን መቀበል አቁሞ ነበር።

አሁን ደግሞ የአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት ከየትኛውም አገር የስደተኞችን ጥያቄ እንዳይቀበል ትዕዛዝ ተላልፎለታል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው በሜሪላንድ የኢሚግሬሽን ጠበቃ የሆኑት ሔኖክ ገቢሳ እና ሙሉዓለም ጌታቸው የጥገኝነት ጥያቄዎች ላይ የሚካሄደው ምርመራ የሚቀጥል ቢሆንም ውሳኔ ግን አይሰጥም ይላሉ።

የብሔራዊ ዘብ አባላቱ ላይ ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ ትራምፕ ኤርትራን፣ ሱዳንን ጨምሮ ለ19 የውጭ አገር ዜጎች የተሰጡ የመኖሪያ እና የሥራ ፈቃዶች ምርመራ እንዲደረግባቸው አዝዘዋል።

ለመሆኑ የአሜሪካ የስደት እና ጉምሩክ መሥሪያ ቤት (አይስ) ሠራተኞች እያሳደዷቸው የሚገኙት እና ሕገወጥ ስደተኞች የሚባሉት እነማን ናቸው?

በትራምፕ አስተዳደር ሕገወጥ የሚባለው ስደተኛ ማን ነው?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ቢቢሲ ያነጋገራቸው እና በአሜሪካ ከፍተኛ የሕግ አዋቂ የሆኑት ሁለቱ ግሰለቦች አይስ እያሳደደ ያለው በስደተኞች ችሎት ከአሜሪካ እንዲወጡ የተወሰነባቸው ስደተኞች ሆነው፣ በተጨማሪም በወንጀል ወይንም በሌላ ጉዳይ የሚፈለጉ ግለሰቦችን ናቸው ይላሉ።

የትራምፕ አስተዳደር ወደ አገራቸው እመልሳቸዋለው ብሎ የተነሳው ጥገኝነት ጠያቂዎች የወንጀል መዝገብ ላይ ስማቸው የሰፈረ መሆኑን ጠበቃ ሙሉዓለም ይናገራሉ።

የትራምፕ አስተዳደር ሰነድ አልባ ስደተኞችም ቢሆኑ በፍርድ ቤት ከአገር እንዲወጡ ውሳኔ የተላለፈባቸውን ብቻ ከአገር አስወጣለሁ ሲል መናገሩን ጠበቃ ሙሉዓለም ያስታውሳሉ።

የተለያዩ ጥናቶች ግን የሕግ አስከባሪ አካላት ከአገር መውጣት አለባቸው ብለው በቁጥጥር ስር ካዋሏቸው ሰዎች መካከል ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑት ምንም ዓይነት የወንጀል ሪከርድ የሌለባቸው መሆኑን ጠበቃው ይገልጻሉ።

ማንኛውም ጥገኝነት ጠያቂ ፍርድ ቤት ቀርቦ ጥፋተኛ ነው ተብሎ እስካልተፈረደበት ድረስ "ነጻ እነደሆነ ነው የሚቆጠረው" የሚሉት ጠበቃ ሙሉዓለም አሁን ታስረው የሚገኙት አብዛኞቹ ምንም ወንጀል የሌለባቸው በመሆናቸው አስተዳደሩ መጀመሪያ ላይ ከገባው ቃል ወሰኑን አልፎ ሰነድ አልባ ስደተኞችን እያሰረ መሆኑን ያሳያል ብለዋል።

ጠበቃ ሔኖክ ገቢሳ በበኩላቸው ጥገኝነት ጠያቂዎች ጥያቄያቸው ተቀባይነት ሳያገኝ ከቀረ በኋላ ይግባኝ የመጠየቅ መብት አላቸው ይላሉ። አንድ ጥገኝነት ጠያቂ ጉዳዩ በይግባኝ እየታየ እያለ "ሕገወጥ ስደተኛ" ሊባል እንደማይችልም ጨምረው ገልጸዋል።

አንድ የስደተኝነት ጥያቄው ውድቅ የተደረገበት ግለሰብ እስከ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ድረስ በመሄድ ጉዳዩ እንዲታይለት ማድረግ ይችላል።

በአሜሪካ የጥገኝነት ጥያቄዎች ሁለት ዓይነት መልኮች አላቸው። አንደኛው በድንበር በኩል ሕግን ጥሰው የሚገቡ ሰዎች ናቸው።

እነዚህ ካለ ቪዛ የመጡ በመሆናቸው ምርመራ ሳይደረግባቸው ወይንም እንዲገቡ ሳይፈቀድላቸው "ዘለው የገቡ" በመሆናቸው የአሜሪካን ድንበር አልፈው እንደገቡ እጃቸውን በመስጠት ጥገኝነት ይጠይቃሉ።

ድንበር እና ሕግ ጥሰው የሚገቡ ስደተኞች ጉዳያቸው በቀጥታ የሚታየው በኢሚግሬሽን ፍርድ ቤት ውስጥ ይሆናል።

እነርሱም ጥገኝነት ከጠየቁ በኋላ እንደማንኛውም ሰው የሕግ አካሄድን ተከትለው ጥገኝነትን ማግኘት ይችላሉ። ካላገኙ እስከ መጨረሻው ጠቅላይ ፍርድ ቤት ድረስ ጉዳያቸው እንዲታይ መጠየቅ ይችላሉ።

ሔኖክ ገቢሳ ይህ ሂደት ግን ቀላል አንዳልሆነ እና "ጠበቃ ያስፈልጋቸዋል። ሂደቱ ውስብስብ በመሆኑ ብዙ ገንዘብ ያስፈልጋቸዋል" ይላሉ።

በሌላ በኩል ደግሞ በቪዛ የመጡ ምርመራ ተደርጎባቸው በቱሪስት ወይንም በተለያዩ የቪዛ ዓይነቶች ወደ አገር ውስጥ የገቡ ወደ ፍርድ ቤት ሳይሆን ዩኤስሲአይኤስ ወደ ሚባል ተቋም በመሄድ ጥገኝነት ይጠይቃሉ።

እነዚህ ግሰለቦች ክስ ሳይሆን እንደ ውይይት ያለ ቃለ መጠይቅ ይደረግላቸው። ብዙ ጊዜ አሳማኝ የሆነ ምክንያት ካላቸው የጥገኝነት ጥያቄያቸው ተቀባይነት ያገኛል።

ጥያቄያቸው ውድቅ ከተደረገ ወይንም ካልተፈቀደላቸው ግን ወደ ስደተኞች ፍርድ ቤት ተመርቶ ጉዳያቸውን ዳኛ ይመለከተዋል።

ጠበቃ ሔኖክ በሕጋዊ መልክ በቪዛ የገቡ ሰዎች ጥጥያቄ 'አፈርማቲቭ አሳይለም ፕሮሰስ' የሚባለው መሆኑን እና በድንበር በኩል የገቡት የጥገኝነት ጥያቄያቸው ደግሞ 'ዲፌንሲቭ አሳይለም' አንደሚባል ያስረዳሉ።

ሕግን ጥሰው ስለገቡ በሂደቱም "ከዚህ አገር ትባረራላችሁ፤ የማትባረሩበት ምክንያት ምንድን ነው? አሳምኑን" የሚል አካሄድ ነው ይላሉ ጠበቃው።

እስካሁን ባለው ሂደት ከ70 እስከ 80 የሚሆኑ የአሜሪካ ዜጎችም በስህተት ተይዘው መታሰራቸውን ጠበቃ ሙሉዓለም ገልጸዋል።

ከፍተኛው ፍርድ ቤት በዚህ ዓመት ባሳለፈው ውሳኔ መሠረት አይስ ማንኛውንም ሰው በመልኩ፣ በሚናገረው እንግሊዘኛ ዘዬ ወይም በቆዳው ቀለም እና ሌሎች ተመሳሳይ መለያዎች አስቁሞ ምናልባትም ለጥቂት ጊዜ አስሮ ማንነቱን እስከሚያጣራ ድረስ መመርመር እንደሚች መወሰኑን ጠበቃ ሙሉዓለም ተናግረዋል።

ይህ ብዙ ክርክር ያስነሳ ውሳኔ ነው በታሪክም ከመጥፎ የከፍተኛው ፍርድ ቤት ውሳኔዎች መካከል የሚጠቀስ ሊሆን ይችላል ብለው የሕግ ባለሙያዎች አስተየየት ይሰጣሉ።

በአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶች ውስጥ ሕገወጥ ስደተኞችን ማደን እና መያዝ እየተካሄደ ነው

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, በአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶች ውስጥ ሕገወጥ ስደተኞችን ማደን እና መያዝ እየተካሄደ ነው

አይስ የጥገኝነት ጥያቄያቸው በሂደት ያለ ስደተኞችን ሊያስር ይችላል?

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የሕግ ባለሙያዎች የትራምፕ አስተዳደር የጥገኝነት ጥያቄያቸው በሂደት ላይ ያለን ስደተኞች ሊያስር አይችልም ይላሉ።

አስተዳደሩ ሊያስር የሚችለው አንድ ሰው ጥገኝነት ጠይቆ ጉዳዩ እየታየለት ሳለ ወንጀል ከሠራ፣ መደበኛ ወንጀል ከፈጸመ መሆኑንም አብራርተዋል።

ሁለተኛው በድንበር በኩል የገቡ ስደተኞች ማመልከቻቸውን ፍርድ ቤት አስገብተው ጉዳያቸው እየታየ ከሆነ በየጊዜው ወደ ሚመለከተው ቢሮ እየቀረቡ ሪፖርት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

በድንበር የገቡ ስደተኞች ታስረው ስለሚለቀቁ፣ ሲወጡ እየተመለሳችሁ በየጊዜው ሪፖርት ማድረግ አለባችሁ ተብለው እንደሚታዘዙ ጠበቃ ሔኖክ ገቢሳ ይናገራሉ።

"ይህ 'ኦልተርኔቲቭ ዲቴንሽን' የሚባለው ነው። በሚፈለጉበት ጊዜ ሄደው ሪፖርት ካላደረጉ ወዲያውኑ ተይዘው እስር ቤት ሊገቡ ይችላሉ።"

እነዚህ ስደተኞች እስር ቤት ቢገቡም ግን የጥገኝነት ጥያቄያቸውን ከእስር ቤት ሆነው ይከታተላሉ።

"ይህ ግን አይስ ይዟቸው ወደ አገራች ይመልሳቸዋል ማለት አይደለም" በማለት ጠበቃ ሔኖክ ያብራራሉ።

ማንም ሰው እዚህ አገር ውስጥ ገብቶ ወደ አገሩ እንዲመለስ ለማድረግ የዳኛ ውሳኔ ያስፈልገዋል የሚሉት ጠበቃው "ከእስር ቤትም ይሁን ከእስር ቤት ውጪ ጉዳዩን ተከታትሎ ለማስፈጸም የዳኛ ውሳኔ ያስፈልጋል።"

አሜሪካ በሕጋዊ መንገድ በቪዛ ገብቶ የጥገኝነት ጥያቄ ማቅረብ ተዘግቷል?

በአሜሪካ ከፍተኛ የሕግ አዋቂ የሆኑት ሔኖክ ገቢሳ እና ሙሉዓለም ጌታቸው እንደሚሉት ወደ አሜሪካ በሕጋዊ ቪዛ ገብቶ የጥገኝነት ጥያቄ ማቀረብ አሁንም ይቻላል።

ጠበቃ ሔኖክ በ1980ዎቹ ውስጥ በኮንግረስ የፀደቀውን 'ኢሚግሬሽን ናሽናሊቲ' ሕግ ፕሬዝዳንቱ የመሻር ሥልጣን የላቸውም ብለዋል።

"የኮንግረስን ሕግ የሚሽረው ራሱ ኮንግረስ ወይንም ደግሞ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ብቻ ነው" የሚሉት ጠበቃው ጥገኝነት የጠየቁ ሰዎች ለተወሰነ ጊዜ መልስ አይሰጣቸውም ብቻ መባሉን ተናግረዋል።

ጥገኝነትን የመጠየቅ መብት ተዘግቷል የሚል ሕግ፣ ፖሊሲ ወይንም ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ (ኤክስኪውቲቭ ኦርደር) አለመውጣቱን ጠበቃ ሙሉዓለምም አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

የትራምፕ አስተዳደር ከለያቸው 19 አገራት የሚመጡ ስደተኞችን በተመለከተ ጠበቆቹ ሲናገሩ "ከእነዚህ አገራት ቪዛ ግኝቶ መምጣት ከባድ ሆኗል፤ ማንም ሰው ቪዛ ላያገኝም ይችላል" ይላሉ።

ትራምፕ በመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው ወቅት ሰባት የሙስሊም አገራት ላይ የጉዞ እገዳ ጥለው ነበር።

አሁን ደግሞ ኤርትራን፣ ሶማሊያን እና ሱዳንን ጨምሮ ከ19 አገራት የመጡ እና የመኖሪያ እና የሥራ ፈቃድ ያላቸው ስደተኞችን ሰነዳቸው ዳግም ምርመራ እንደሚደረግበት ተገልጿል።

ሕገወጥ ስደተኞችን የሚያጓጉዝ የአሜሪካ ሠራዊት አውሮፕላን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, እስካሁንም ሕገወጥ ናቸው የተባሉ ስደተተኞች ከአሜሪካ እንዲሰወጡ ተደርገው ወደ ተለያዩ አገራት ተወስደዋል

በትራምፕ አቋም ምክንያት የጥገኝነት ጠያቂዎች ጉዳይ ይጓተታል?

ዶናልድ ትራምፕ በመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው ወቅት አስተዳደራቸው "መጨረሻ ያመለከተ መጀመሪያ ይታይለታል" የሚል አሠራር ተከትሎ እንደነበር ጠበቆቹ ያስታውሳሉ።

ይህንን ያደረጉበት ምክንያት ቶሎ ቶሎ የጥገኝነት ጥያቄያቸውን በመዝጋት የሥራ ፈቃድ ሳያገኙ ከአሜሪካ የሚወጡበትን መንገድ ለማመቻቸት መሆኑን ጠበቃ ሙሉዓለም ይናገራሉ።

ይህም በመጀመሪያው ትራምፕ የሥልጣን ዘመን ወቅት ለሁለት ዓመታት ይህ ተግባራዊ ተደርጎ የኮቪድ ወረርሽኝ በመከሰቱ ተቋርጧል።

አሁን ሁለተኛው የትራምፕ አስተዳደር ሲመጣ ደግሞ የቀደመውን አሠራር መልሰው ተግባራዊ ማድረግ መጀመራቸውን ጠበቆቹ ይናገራሉ።

"በሚገርም ሁኔታ ተቃራኒውን ነው እያየን ያለነው" የሚሉት ሔኖክ ገቢሳ፣ ትራምፕ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ ለጥገኝነት ጠያቂዎች ኑሮ ከብዷል ይላሉ።

ይሁን እንጂ በሕጋዊ መንገድ ለገቡ ሰዎች ጥያቄያቸው የሚስተናገድበት ፍጥነት በጣም መጨመሩን ጠበቆቹ ገልጸዋል።

በሕጋዊ መንገድ የገቡ ሰዎች ቃለ መጠይቅ እንዲደረግላቸው ድሮ ዘጠኝ እና 10 ዓመት ነበር የሚጠብቁት የሚሉት የሕግ ባለሙያዎቹ አሁን ግን በአንድ እና በሁለት ወር ውስጥ ለቃለ መተይቅ ሊጠሩ እንደሚችሉ ይናገራሉ።

ጠበቃ ሙሉዓለም 90 በመቶ የሚሆኑ የጥገኝነት ጥያቄ አመልካቾች ከ90 ቀን እስከ 180 ቀን በሆነ ጊዜ ውስጥ ለቃለ መጠይቅ እንደሚጠሩ ይናገራሉ።

ውሳኔ የማግኘት ዕድላቸው ደግሞ 50 በመቶ መሆኑን ገልፀው፣ 50 በመቶ የሚሆኑት ከስድስት ወር በላይ ይወስዳል ብለዋል።

ጠበቃ ሔኖክ "ፕሬዝዳንት ትራምፕ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ አሳማኝ ማስረጃ፣ አሳማኝ ጉዳይ ያላቸው ሰዎች፣ እውነተኛ ጥገኝነት ፈላጊዎች፣ በሁለት ወር ውስጥ ወረቀት ያገኙ በጣም ብዙ ደንበኞች አሉኝ።"

ኢትዮጵያውያን ጥገኝነት ጠያቂዎች ምን ጥንቃቄ ያድርጉ?

ትራምፕ ሶማሊያውያን ስደተኞች በአሜሪካ እንዲኖሩ እንደማይፈልጉ ተናግረዋል። ፕሬዝዳንቱ ሶማሊያውያን ስደተኞች "ወደመጡበት መመለስ አለባቸው" እና "አገራቸው የማትረባ የሆነችው ያለ ምክንያት አይደለም" ብለዋል።

ትራምፕ ሶማሊያውያንን የሚያጣጥሉ ሌሎች አስተያየቶችንም ሰጥተው ሶማሊያውያን ስደተኞች ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ ተናግረዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ጠበቆች ሶማሊያውያንን እና ኢትዮጵያውያንን መለየት አስቸጋሪ መሆኑን ይናገራሉ።

ጠበቃ ሙሉዓለም "ማን ነው ኢትዮጵያዊ የሚለውን ለመለየት አስቸጋሪ ነው። በዚያ ላይ ኢትዮጵያዊ ሶማሌዎች አሉ። በዚህ ሂደት ውስጥ ኢትዮጵያውያን ይጎዳሉ" ብለዋል።

የአይስ መኮንኖች ወደ ሚኒያፖሊስ መሄዳቸው የማይቀር ነው የሚሉት ጠበቃ ሔኖክ በበኩላቸው "ለዚያ ነው እያሟሟቁ ያሉት" ይላሉ።

አክለውም "በዚህ ደግሞ የሚጎዱት ትውልደ ሶማሊያውያን ስደተኞች ብቻ አይደሉም። ማንኛውም የጥገኝነት ጥያቄ ያቀረበ ሰው በዚሁ አጋጣሚ ሊጠቃ ይችላል።"

በአጠቃላይ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ የሚናገሩት ጠበቆቹ በዚህ ሰዓት ጉዳያቸው እየታየ ያለ ጥገኝነት ጠያቂዎች ሌላ ዓይነት ችግር ውስጥ ራሳቸውን እንዳይጨምሩ ይመክራሉ።

መኪና በሚያሽከረክሩበት ወቅት ጥንቃቄ ማድረግ፣ ጠጥቶ አለማሽከርከር፣ ከተገቢው ፍጥነት በላይ አለመንዳት በሚንቀሳቀሱበት ወቅት ተገቢውን ሰነዳቸውን ይዘው መንቀሳቀስ፣ ከፀጥታ አካላት ጋር አምባጓሮ አለመፍጠር፣ የሕግ ወይም የፀጥታ አካላት ሲያስቆሟቸው ላለመታሰር በሚል ለማመልለጥ አለመሞከር ማድረግ ካለባቸው ጥንቃቄዎች መካከል መሆናቸውን ባለሙያዎቹ ዘርዝረዋል።

የጥገኝነት ጥያቄያቸው እየታየ ያሉ ስደተኞች የሥራ ፈቃዳቸውን ወይንም ደረሰኛቸውን ለፀጥታ አካላት አስፈላጊ በሆነበት ጊዜ ሁሉ ማሳየት፣ በቪዛ ያሉ ቪዛቸውን ማሳየት እንደሚጠቅማቸውም መክረዋል።

ከትዳር ወይንም ከፍቅር አጋራቸው ጋር አምባጓሮ ውስጥ አለመግባትም የፀጥታ አካላት ትኩረትን ለመቀነስ አንደሚያግዛቸው ጨምረው ተናግረዋል።

ከተያዙ ግን ወዲያውኑ ወደ ኢሚግሬሽን ጠበቃ መደወል ይኖርባቸዋል።

ሁሌም የጠበቃ ስልክ ይዘው መንቀሳቀስ እና በቁጥጥር ስር ከዋሉ ለጠበቃቸው ወዲያውኑ ማሳወቅ እንዳለባቸው ምክራቸውን ለግሰዋል።