በአጓጊ የስራ እድል ተታልለው ከተወሰዱ በኋላ ለሩሲያ እንዲዋጉ የተደረጉት ኬንያውያን

ኬንያዊው ዴቪድ ኩሎባ እና አንድ የሩሲያ ወታደር ጫካ ውስጥ የወታደር ልብስ ለብሰው

የፎቶው ባለመብት, Kuloba family

የምስሉ መግለጫ, ኬንያዊው ዴቪድ ኩሎባ እና አንድ የሩሲያ

ዴቪድ ኩሎባ፤ በሩሲያ ለሚገኝ ተቋም የጥበቃ አገልግሎት የመስጠት ስራን ያገኘው ኬንያ ውስጥ በሚገኝ አንድ የሰራተኛ ቅጥር ድርጅት በኩል ነበር። ልጇ ወደ ሩሲያ የመጓዙ ነገር ያልተዋጠላት እናቱ የስራ እድሉን እንዳይቀበል አስጠንቅቃው ነበር።

ድህነት በተንሰራፋበት 'ኪቤራ' በተባለው የናይሮቢ ከተማ መንደር ከሚኖር ቤተሰብ ለወጣ ልጅ ውጭ አገር ስራ ማግኘት ደስታን የሚያጭር ነገር ነው። የ22 ዓመቱ ዴቪድ ለውዝ ከማዞር እስከ ቀን ስራ ድረስ ያገኘውን ይሰራል።

የረጅም ጊዜ ተስፋው ወደ አረብ አገራት ሄዶ ስራ ማግኘት ነበር። እናቱ፤ የጥበቃ ስራውን ያገኘው የት አገር እንደሆነ ስትሰማ ተደናግጣለች።

"ስልኩን አሳየኝና፤ 'ተመልከቺ፣ ሩሲያ ነው' አለኝ" ስትል እናት ሱዛን ኩሎባ ስለ ጉዳዩ የሰማችበትን የመጀመሪያ ቅጽበት ለቢቢሲ ኒውስዴይ ፕሮግራም ተናግራለች።

" 'ቴሌቪዥን ላይ ስለ ሩሲያ የሚያሳዩትን አትመለከትም? መቼም ጥሩ ነገር አይደለም' አልኩት" ትላለች።

የቀረበለት የስራ እድል ትክክለኛ እንደሆነ ያመነው ልጇ፤ ከአቋሙ ፈቀቅ አላለም። ሩሲያ እንደደረሰ ሰባት ሺህ ዶላር ሊከፍሉት ቃል እንደገቡለት ይናገር ነበር። ቋሚ ገቢ ለሌለው ሰው ይህንን ያህል ገንዘብ ሕይወትን የሚቀይር ነው።

ተቃውሞዋን ላሰማችው እናቱ መች ቀን እንደሚበር ያልተናገረው ዴቪድ፤ ነሐሴ ወር ላይ ወደ ሩሲያ ተጓዘ። በኋላ ላይ በሰላም መድረሱን ለማሳወቅ ወታደራዊ ዩኒፎርም ለብሶ ፎቶግራፍ ሲልክላት የተሰማት ድንጋጤ ነበር።

"እናቴ፤ ተነግሮን የመጣነው ስራ ተቀይሯል፤ ይሄም ግን መጥፎ አይደለም" እንዳላት ታስታውሳለች።

ልጇ እንደሚያስረዳው፤ እርሱ እና የተወሰኑ ሌሎች ኬንያውያን የሁለት ሳምንት የውጊያ ስልጠና ተሰጥቷቸዋል። ስልጠናውን አጠናቅቀው ሩሲያ ከ2014 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ወረረቻት ዩክሬን ወደሚገኝ የውጊያ ቀጣና እየተጓዙ እንደሆነ በወቅቱ ተናግሯል።

ከቀናት በኋላ ደግሞ እርሱ እና ሌሎች ሰዎች በሩሲያ ቁጥጥር ስር በሚገኝ አካባቢ ላይ ድንገተኛ ጥቃት እንደተከፈተባቸው ገልጿል። ይህንን የሰማችው እናት ወደ ቤቱ እንዲመለስ ለምናዋለች።

" 'ዴቪድ እባክህን ያንን አካበቢ ለቅቀህ ውጣ' አልኩት። 'እንዴት እወጣለሁ? ኮንትራት ፈርሜያለሁ። ቢያንስ አንድ ዓመት ስጪኝ' አለኝ" ስትል ንግግራቸውን ታስታውሳለች።

"ከዛ የፈራሁት መልዕክት ደረሰኝ" ትላለች።

በመስከረም ወር መጨረሻ፤ ዴቪድ ወደ ጦርነት እየሄደ መሆኑን የሚገልጽ 'የድምጽ መልዕክት' ላከላት። ምናልባት በሕይወት የማልወጣ ከሆነ በሚልም በሩሲያኛ የተጻፈ የሩሲያ ሠራዊት መታወቂያ እና የውል ስምምነት አያይዞ ልኮላታል።

አንድ ነገር የሚደርስበት ከሆነ ሰነዶቹን ወደ ሩሲያ ኤምባሲ ይዛ እንድትሄድ አሳስቧታል። ለመጨረሻ ጊዜ ድምጹን የሰማችው የዚህ ጊዜ ነው።

በሩሲያኛ የተጻፈ ኬንያዊው ዴቪድ ኩሎባ መታወቂያ

የፎቶው ባለመብት, Kuloba family

የምስሉ መግለጫ, በሩሲያኛ የተጻፈ ኬንያዊው ዴቪድ ኩሎባ መታወቂያ
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ግራ መጋባት እና ፍርሃት የወረራት እናት ብዙም ሳይቆይ ልጇ እንደሞተ ከጓደኛው ሰማች።

" 'እንዴት አወቅክ' ብዬ ጓደኛውን ጠየቅኩት። 'ሩሲያ ውስጥ የተቀበለንን ኤጀንት ስልክ ቁጥር ልስጥሽ' አለኝ" በማለት ተናገራለች።

ወደ ተሰጣት ቁጥር መልዕክት ስትልክ በመጀመሪያ ምላሽ የተሰጣት በሩሲያኛ ነበር። ማን እንደሆነች ከነገረቻቸው በኋላ ግን የሚያነጋግራት ሰው ዴቪድ እንደጠፋ እና ሞቷል ተብሎ እንደሚገመት በእንግሊዘኛ ነገራት።

"ስለ ልጅሽ ይህንን የምነግርሽ እያዘንኩ ነው" ነበር ያላት።

የልጇ አስከሬን ፎቶን ወይም ልጇ ሬሳ ክፍል ውስጥ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነገር እንዲልኩላት ብትጠይቅም መልስ አላገኘችም።

ግለሰቡ ያለው "እጅግ ሩቅ" የሆነ አካባቢ እንደሆነ በመግለጽ፤ ራሷ ወደ ሩሲያ እንድትመጣ ወይም ሌላ ዘመድ እንድትልክ ተግሯታል። ቤተሰባቸው ግን ይህንን ለማድረግ አቅም የለውም። ኋላ ላይ ያው ሰው፤ ምንም ዓይነት ሰነዶችን ሳያቀርብ ለልጇ ሞት "ካሳ" እንደሚከፈላት ነገራት።

ሱዛን እንደምትናገረው፤ ዴቪድን በተመለከተ ከሩሲያ ባለሥልጣናት ያገኘችው ይፋዊ ማረጋገጫ የለም። ኬንያ ውስጥ የሚገኘውን የሩሲያ ኤምባሲ በጎበኘችበት ወቅት ባልስልጣናቱ "ከሠራዊቱ ጋር ግንኙነት እንደሌላቸው" ገልጸውላታል።

ሀዘን ውስጥ ከመቀመጥ ውጪ በቀጣይ ምን ማድረግ እንዳለባት እንደማታውቅ ታስረዳለች። "እንዴት ነው የምጀምረው? ምክንያቱም ምንም ነገር አናውቅም። የመጀመሪያ ልጄ ነው። እርሱ ላይ ጥገኛ ነበርኩ" ስትል ግራ መጋባቷን ትገልጻለች።

ልጁ ለስራ ወደ ሩሲያ የሄደበት ሌላ ኬንያዊ አባት ደግሞ፤ ልጁ የሄደው በሹፍርና ተቀጥሮ እንጂ ወታደራዊ ውጊያ ጋር የሚገናኝ እንዳልነበር ይናገራል።

ወጣቱ ኬንያዊ ዩክሬን ውስጥ ቆስሏል። ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኬንያ ቢመለስም ያሳለፈው ሁኔታ በፈጠረበት ስነ ልቦናዊ ጉዳት ምክንያት የደረሰበትን አይናገርም። ቢቢሲ ደህንነቱን ለመጠበቅ ሲል ማንነቱን ላለመግለጽ ተስማምሟል።

አባት ልጁ ወደ ሩሲያ መጓዙን ያወቀው ጉዳት እንደደረሰበት ሲነገረው ነው። "ሰዎች እየሄዱ እንደሆነ ሲጠቁመኝ ነበር" የሚሉት አባት እንዳያደርገው መምከራቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ኬንያዊው ዴቪድ ኩሎባ

የፎቶው ባለመብት, Kuloba family

የምስሉ መግለጫ, ይህንን ፎቶ ለእናቱ የላከው ዴቪድ ኩሎባ፤ ከመስከረም መጨረሻ በኋላ ድምጹ አልተሰማም

"ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ጦርነቱን ስከታተል ነበር። ምቾት እየተሰማኝ አልነበረም" ይላሉ። የስራ ቅጥር ወኪሎች በየወሩ 1,500 ዶላር እንደሚያገኝ ቃል ገብተውለት እንደነበር ያስታውሳሉ።

ልክ እንደ ዴቪድ ሁሉ ሌላኛውም ኬንያዊ ወጣት ወደ ውጊያ ግንባር ከመወሰዱ በፊት ሁለት ሳምንት ስልጠና እንደተሰጠው ተናግሯል።

"ጫካ ውስጥ እንደተጎዳ እና አምስት ቀን ሙሉ ሕክምና እንዳላገኘ ይናገራል። የሕመም ማስታገሻ እየወሰደ ነበር" ሲሉ አባቱ ያስረዳሉ።

ኋላ ላይ ወደ ሩሲያ ድንበር ተወስዶ የመጀመሪያ ደረጃ ሕክምና ካገኘ በኋላ ወደ ሴንት ፒተርበርግ ከተማ ተልኳል።

"የሌሎች ተዋጊዎች የተበታተነ አስከሬን" መመልከቱን ይገልጻል። ብዙዎቹ እንደ እርሱ በትክክል ባልተረዱት ሁኔታ አንድ ዓመት የውል ስምምምነት መፈረማቸውን እንዳስረዳው አባቱ ተናግሯል።

ባለፈው ወር የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር 200 ገደማ ኬንያውያን በሩሲያ እየተዋጉ እንደሆነ እንደሚታወቅ አስታውቀዋል። የቅጥር ምልመላ መረቡ አሁንም በስራ ላይ እንዳለም እውቅና ሰጥተዋል።

መንግሥት ይህንን ያስታወቀው አንድ ወጣት ኬንያዊ አትሌት መስከረም ላይ ዩክሬን ውስጥ ከተያዘ በኋላ ተታልሎ የሩሲያን ሠራዊት እንዲቀላቀል እንደተደረገ መናገሩን ተከትሎ ነው።

የኬንያ መንግሥት እንደሚገልጸው በአሁኑ ሰዓት በርካታ የቅጥር ኤጀንሲዎች ምርመራ እየደረገባቸው ነው' ��ተወሰኑትም ፈቃዳቸው ታግዷል። የአገሪቱ ፓርላማ የመከላከያ እና የውጭ ጉዳይ ኮሚቴም ጉዳዩን ይዞታል።

ዘመዶቻቸው ለሩሲያ ጦር እንዲዋጉ የተደረገባቸው ቤተሰቦች ግን መንግሥት የሚሰጠው ምላሽ አዝጋሚ እንደሆነ በማንሳት ይወቅሳሉ።

ተታልለው ውጊያ ውስጥ የገቡ ኬንያውያንን ለማስመለስ ምን እየተደረገ እንደሆነ የተጠየቁት የኬንያ ፓርላማ መንግሥት ተጠሪ ሲልቫኑስ ኦሶሮ፤ ሂደቱ የዲፕሎማሲ መንገዶችን መከተል እንዳለበት ተናግረዋል።

ልጇ ወደ ሩሲያ የተወሰደባት እናት ሱዛን ኩሎባ
የምስሉ መግለጫ, እናት ሱዛን ኩሎባ የልጇን እጣ ፋንታ በተመለከተ እስካሁን ከሩሲያ ባለስልጣናት በይፋ የተነገራት ነገር እንደሌለ ታስረዳለች

"በፈቃደኝነት ኮንትራት ተፈርሟል፤ ምንም እንኳ አውቀው ባይሆንም። በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ብቻ ነው ሊፈታ የሚችለው። ይህ ጥረት እየተደረገ ነው" ብለዋል።

አፍሪካውያንን ለሩሲያ የማዋጋት ጉዳይ ኬንያ ውስጥ ብቻ የተገደበ አይደለም። በበርካታ የአፍሪካ አገራት የሚገኙ ባለሥልጣናት ወጣቶች አጓጊ የስራ እድል ከቀረበላቸው በኋላ ለሩሲያ ጦር እንደተቀጠሩ አስታውቀዋል።

ልጆቻቸው የተወሰዱባቸው ቤተሰቦች በይፋ ወጥተው ለመናገር አይደፍሩም። ይህንን ማድረጋቸው በሩሲያ የሚገኙት ዘመዶቻቸው ላይ የሚያመጣውን መዘዝ በተመለከተ ፍርሃት ይሰማቸዋል።

ደቡብ አፍሪካ ውስጥ የቀድሞ አገሪቱ ፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማ ልጅ በዚህ የቅጥር ሂደት ውስጥ ተሳትፋ መገኘቷ መነጋገሪያ ሆኗል። እርሷ ግን የቀረቡባትን ውንጀላዎች አስተባብላለች።

የዩክሬን ባለስልጣናት በበኩላቸው፤ ለሩሲያ ሲዋጋ የተያዘ ሰው የሚቆጠረው እንደ ጠላት ተዋጊ እንደሆነ እና ብቸኛው ነጻ መውጫ መንገድ እጅ ሰጥቶ እንደ የጦር እስረኛ መቆጠር እንደሆነ በተደጋጋሚ አስጠንቅቀዋል።

ኬንያዊቷ እናት ሱዛን ኩሎባ የልጇን እጣ ፈንታ በተመለከተ እስካሁን ድረስ ምንም ይፋዊ ማረጋገጫ አላገኘችም። ሞቶ ከሆነም አስከሬኑ ወደ ኬንያ እንዲላክ ትፈልጋለች።

"ልቤ ተሰብሯል። ሊያግዘን ነበር የፈለገው። የተሻለ ስራ እንዳገኘ ነበር ያሰበው ትላለች።