በአሜሪካ ድጋፍ የተጀመረው የኢራን የኒውክሌር ፕሮግራም ታሪክ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኢራን የኒውክሌር ፕሮግራም ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የቀጠናው የፖለቲካ ትኩሳት ከመሆኑ ባሻገር ከምዕራባውያን ጋር ሆድና ጀርባ አድርጓታል።
የዓለም አቀፉ የአውቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ እአአ በ2003 ለ18 ዓመታት በምሥጢር ኢራን የኒውክሌር ተቋማቷን ስትገነባ መቆየቷን ከደረሰበት ወዲህ ደግሞ ተከታታይ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች እየተካሄዱ ነው።
ይህ ግኝት ኢራን የፈረመችውን የኒውክሌር ጦር መሳርያዎች እና ቴክኖሎጂዎችን ያለ ማስፋፋት ስምምነት የሚጥስ ነው።
በዚህም የተነሳ ከእስራኤል ጋር የጎሪጥ ከመተያየት በተጨማሪ በምዕራባውያን ግፊት በኢራን ላይ የዲፕሎማሲ ውግዘትን፣ ማዕቀብን እንዲሁም ሌሎች ጫናዎችን ሲያሳድሩ ቆይተዋል።
ይህ ደግሞ የምዕራባውያኑን አገራትን ብቻ ሳይሆን የቴህራን ወዳጅ የሆኑትን ቻይና እና ሩሲያንም ያካተተ ነው።
ኢራንን እዚህ ውዝግብ ውስጥ ያስገባት የኒውክሌር ፕሮግራም በወቅቱ ሥልጣን ላይ የነበረው የፕሬዝዳንት መሐመድ ኻታሚ መንግሥት ለሰላማዊ ዓላማ ነው በማለት ቢምል ቢገዘትም ሰሚ አላገኝም ነበር።
የእንቅስቃሴው አስተባባሪ የሆነችው አሜሪካም ኢራን ውስጥ የተገኙትን ማስረጃዎች በመጥቀስ ቴህራን የአውቶሚክ ጦር መሳሪያ ለመታጠቅ ትፈልጋለች ለሚለው ጥርጣሬዋ እንደ ማረጋገጫ ታቀርበዋለች።
የኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብር የጆርጅ ደብልዩ ቡሽ፣ የባራክ ኦባማ፣ የዶናልድ ትራምፕ እና የጆ ባይደን ተከታታይ የአሜሪካ አስተዳደሮች ማዕከላዊ ጉዳይ ሆኖ ቆይቷል።
እነዚህ የአሜሪካ ፕሬዝደንቶች የኢራንን የኒውክሌር መርሃ ግብር በመካከለኛው ምሥራቅ ያለውን የኃይል ሚዛን የሚቀይር መሆኑን በመጥቀስ መፍትሄ ለማበጀት የተለያዩ መንገዶችን ተጠቅመዋል።
ፕሬዝደንት ቡሽ በ2002 "አክሲስ ኦቭ ኢቭል" (የክፋት ማኅበር) በተሰኘው ዝነኛ ንግግራቸው ኢራንን የጠቀሱ ሲሆን፣ ያንንም ተከትሎ የተጠናከረ ዓለም አቀፍ ማዕቀብ እንዲጣልባት አድርገዋል።
ኦባማ በስምንት ዓመት የሥልጣን ዘመናቸውን ከቴህራን ጋር ሲደራደሩ አሳልፈዋል።
ከዩናይትድ ኪንግደም፣ ከፈረንሳይ፣ ከሩሲያ፣ ከቻይና እና ከጀርመን መንግሥታት ጋር በመሆንም አጠቃላይ የድርጊት መርሃ ግብር በአውሮፓውያኑ 2015 ተፈራርመዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዶናልድ ትራምፕ በመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው አሜሪካን ከዚህ ስምምነት በማስውጣት አዲስ የአንድ ወገን ማዕቀብ በኢራን ላይ ጥለዋል።
በምላሹ ቴህራን በፈረመችው ስምምነት ላይ የተጣሉትን ገደቦች ችላ ማለት ጀመረች።
ከዚያም ዩራኒየም የምታበለጽግበት ደረጃን ወደ 60 በመቶ አሳደገች።
ይህም በተለምዶ ኤሌክትሪክ ለማመንጨት ከሚያስፈልገው 4.5 በመቶ እጅጉን የራቀ እና ቦምብ ለመሥራት ከሚያስፈልገው 90 በመቶ ጋር በጣም የቀረበ ነው።
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ኢራን የፈረመችው ስምምነት በአግባቡ ተግባራዊ እንዲሆን ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ የቀረ ሲሆን፣ ትራምፕ የሁለተኛው የሥልጣን ዘመናቸውን ሲጀምሩ ጠንካራ አቋም ወስደዋል።
በቅርቡም አሜሪካ እስራኤል በኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብር ላይ የምታደርገውን ወታደራዊ ዘመቻ የተቀላቀለች ሲሆን፣ የኢራንን የኒውክሌር ተቋማትን በከባድ ቦምቦች ደብድባለች።
አሜሪካ ዛሬ የኢራን የኒውክሌር ተቋማትን ብትደበድብም በ1950ዎቹ ግን ድጋፍ በማድረግ ከፊት ተሰላፊ ነበረች።
ይህ ሁሉ የተጀመረው በፕሬዝዳንት ድዋይት አይዘንአወር ንግግር ነበር።
"የሰላም አተሞች"
በአውሮፓውያኑ ታኅሣሥ 8/1953 በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ፊት ፕሬዝዳንት አይዘንአወር ለወታደራዊ አገልግሎት የሚውለው የኒውክሌር ቴክኖሎጂ ያለውን ስጋት ጠቅሰው ንግግር አድርገዋል።
ፕሬዝዳንቱ ይህንን ስጋት ለመቀነስ ከመፈለግ ባለፈ ቴክኖሎጂው ለሰው ልጅ አገልግሎት እንዲውል ሃሳብ አቅርበዋል።
"ይህን መሳሪያ ከወታደሮች መዳፍ መንጠቁ ብቻውን በቂ አይደለም። ወታደራዊ ጭምብሉን እንዴት እንደሚያወልቁ በሚያውቁ ሰዎች እጅ እናስቀምጠው እና ከሠላም ጋር እናላምደው" ብለዋል።
በመቀጠልም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጥላ ስር የአውቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ እንዲቋቋም ሀሳብ አቀረቡ።
በዚህም ኒውክሌር "ለሰው ልጆች ሰላማዊ አገልግሎት" እና አውቶሚክ ኢነርጂን እንደ ሕክምና እና ግብርና ላሉ ፍላጎቶች መዋል የሚችልበትን መንገድ እንዲፈልግ ሃሳብ አቅርበዋል።
አክለውም "ልዩ ግቡ የኤሌክትሪክ ኃይል ለተቸገሩ የዓለም ክልሎች አትረፍርፎ ማቅረብ ነው" ብለዋል።
ሃሳቡ የኒውክሌር ቁስ የማምረት አቅም ያላቸው ኃይሎች ለተባበሩት መንግሥታት ኤጀንሲ ያንን እንዲሰጡ እና ይህም ደኅንነቱ በተጠበቀ እና በተመራማሪዎች እጅ ውስጥ እንዲቀመጥ ያስችለዋል።
ያ የአይዘንአወር ንግግር ለዓለም አቀፉ የአውቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ (IAEA) መፈጠር መንገድን ጠርጓል።
ከዚህም ባሻገር 'አተምስ ፎር ፒስ' (አተሞች ለሰላም) በመባል የሚታወቀውን ፕሮግራም እንዲጀመር አድርጓል።
በዚህም አሜሪካ በማደግ ላይ ላሉ አገራት የአውቶሚክ ኢነርጂ ሰላማዊ አጠቃቀምን ለመርዳት ትምህርት እና ቴክኖሎጂን እንድትሰጥ ያስችላታል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኒውክሌር ጂኒ ከጠርሙሱ መውጣት
ይህ ንግግር በተባበሩት መንግሥታት ስብሰባ ላይ ከተደረገ በኋላ አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ዩናይትድ ስቴትስ የአውቶሚክ ኢነርጂ ሕግን በማሻሻል የኒውክሌር ቴክኖሎጂን እና ቁሳቁሶችን ለጦር መሳሪያ ልማት ላለመጠቀም ለተስማሙ ሌሎች አገራት መላክን የሚያስችላትን ሕግ አፀደቀች።
በአውሮፓውያኑ 1955 በመጋቢት ወር የአይዘንአወር አስተዳደር አንድ እርምጃ ሄዶ የአሜሪካ የአውቶሚክ ኢነርጂ ኮሚሽን በ"ነፃው ዓለም" ውስጥ ላሉ አገራት በተወሰነ መጠን የኒውክሌር ማምረቻ ቁሳቁስ እንዲያቀርብ እንዲሁም የኒውክሌር ኃይል ማመንጫዎችን በመገንባት እንዲያግዝ አደረገ።
የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር ፔንታገን ከፍተኛ ባለሥልጣን የነበሩት ፒተር አር ላቮይ በጦር መሳሪያዎች ቁጥጥር ማኅበር በታተመ ጽሑፋቸው ላይ ይህንን ዓላማ አብራርተዋል።
"እነዚህ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች የአሜሪካን ዓለም አቀፋዊ አመራር ለማስጠበቅ፣ የሶቪየት ተጽእኖን ለመቀነስ እና የዩራኒየም እና የቶሪየም አቅርቦቶችን ደኅንነቱ የተጠበቀ ለማድረግ የታሰቡ ነበሩ" ሲሉ ጽፈዋል።
ሕንድ ከዋሽንግተን የኒውክሌር እርዳታ የተቀበለች የመጀመሪያዋ አገር ነች።
ሌሎች ተጠቃሚዎች ደግሞ ደቡብ አፍሪካ፣ እስራኤል፣ ቱርክ፣ ፓኪስታን፣ ፖርቱጋል፣ ግሪክ፣ ስፔን፣ አርጀንቲና፣ ብራዚል እና ኢራን ይገኙበታል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአሜሪካ እርሾ የተጀመረው የኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብር
በአውሮፓውያኑ መጋቢት 5/1957 ዩናይትድ ስቴትስ በወቅቱ በመሐመድ ሬዛ ፓህላቪ ከምትመራው ኢራን ጋር ለሲቪል የአውቶሚክ ኢነርጂ አጠቃቀም የትብብር ስምምነት ተፈራረመች።
በ'አተምስ ፎር ፒስ' መርሃ ግብር ጥላ ስር የነበረው ይህ ስምምነት የኢራንን የኒውክሌር መርሃ ግብር ለመጀመር መሠረት ጣለ።
ለዋሽንግተን፣ በዚያ የቀዝቃዛ ጦርነት ወቅት ኢራን ተጨማሪ መስህብ ነበራት።
ጆናህ ግሊክ ኡንተርማን በ2018 በዊልሰን ሴንተር በታተመ ትንታኔያቸው ላይ "በቤተ መዛግብት የተቀመጡ ሰነዶች ከማንም ጋር ወገንተኛ ያልነበረችው ኢራን፣ የሶቭየት ኅብረትን ተጽዕኖ ለመቀነስ የማዕዘን ድንጋይ ተደርጋ ትታይ እንደነበር ያሳያሉ። 'አተምስ ፎር ፒስ' የተሰኘው ፕሮግራም ደግሞ ለምዕራቡ ዓለም የሚኖራትን ታማኝነት ያረጋግጣል።"
እአአ በ1967 ዩናይትድ ስቴትስ ለቴህራን ባለ 5 ሜጋ ዋት የኒውክሌር ምርምር ማብላያ፣ እንዲሁም የተወሰነ መጠን ያለው ከፍተኛ የበለፀገ ዩራኒየም ሰጠች።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከሦስት ዓመት በኋላ ኢራን የኒውክሌር ጦር መሳሪያን ለመያዝም ሆነ ለማልማት እንደማትፈልግ የሚያስገድደውን የኒውክሌር መከላከል ስምምነትን አፀደቀች።
ቢሆንም ግን የኒውክሌር ፕሮግራም ማበልጸግ ሃሳብ የምዕራባውያኑ ወዳጅ በነበሩት በኢራኑ ንጉሥ ሙሉ በሙሉ አልተተወም ነበር።
የኢራን የኒውክሌር ፕሮግራም አባት ተደርገው የሚወሰዱት አክባር ኢተማድ እአአ በ2013 ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የንጉሑን ሃሳብ አብራርተው ነበረ።
"በወቅቱ ሻህ ኢራን በቂ ጥንካሬ ካገኘች እና በቀጣናው ጥቅማችንን ማስጠበቅ የምንችል ከሆነ የአውቶሚክ መሳሪያ አያስፈልግም የሚል ሃሳብ ነበረው። ይህ ከተለወጠ ግን 'ኒውክሌር ሊኖረን ይገባል' የሚል አቋም ነበረ" ሲሉ ተናግረዋል።
ኢተማድ በ1974 የተቋቋመው የኢራን የአውቶሚክ ኢነርጂ ድርጅት ሊቀመንበር የነበሩ ሲሆን፣ የአገሪቱን የኒውክሌር መርሃ ግብር የመጀመሪያ እንቅስቃሴን መርተዋል።
በዚያው ዓመት ንጉሡ ሬዛ ፓህላቪ በሚቀጥሉት ሁለት አስርት ዓመታት እያንዳንዳቸው 23 ሺህ ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያላቸው 23 የኒውክሌር ኃይል ማመንጫዎችን ለመገንባት ማቀዳቸውን አስታውቀዋል። የተሟላውን የኒውክሌር ነዳጅ ምርት ለማዳበርም ፈለጉ።
ነገር ግን ኢራን በዚህ መንገድ ወደፊት ለመራመድ የሚያስችል ብቃት ያላቸው ባለሙያዎች ስለሌሏት ትል��� እንቅፋት ተፈጠረ።
አሪያና ሮውቤሪ በብሩኪንግስ ኢንስቲትዩት ባሳተመው ጽሑፍ ላይ "ኢራን በኒውክሌር ምህንድስና እና በፊዚክስ የሰለጠኑ በርካታ ባለሙያዎች ስለሌሏት የቴህራን የኒውክሌር ማብላያ ለአስር ዓመታት ያህል ውጤታማ አልነበረም" ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አሁንም ይህንን መሰናክል ለማሸነፍ የአሜሪካ እርዳታ ቁልፍ ነበር።
በነሐሴ ወር 1974 የኢራን ባለሥልጣናት ለታዋቂው የማሳቹሴትስ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት (ኤምአይቲ) በኢራን የአውቶሚክ ኢነርጂ ድርጅት ለተመረጡ ተማሪዎች፣ የኢራን የኒውክሌር መሀንዲሶች የመጀመሪያ ትውልዶችን ለማሠልጠን የማስተርስ ፕሮግራም እንዲከፍት ሃሳብ አቀረቡ።
ኢራን ለመጀመሪያዎቹ ሁለት ዓመታት 1.3 ሚሊዮን ዶላር (በአሁኑ ምንዛሪ ስሌት 8.5 ሚሊዮን ዶላር) የከፈለች ሲሆን፣ የትምህርት ፕሮግራሙ ንጉሡ (ሻህ) በሰብዓዊ መብት ረገጣ በመክሰሳቸው እና ለኒውክሌር መስፋፋት አስተዋፅዖ ያደርጋል በሚል ፍራቻ በኤምአይቲ ፕሮፌሰሮች እና ተማሪዎች ተቃውሞ ገጠመው።
ያም ሆነ ይህ፣ ይህ የትምህርት ስምምነት እና በዋሽንግተን እና በቴህራን መካከል የነበረው የኒውክሌር ትብብር በ1979 በኢራን አብዮት በመፈንዳቱ ብዙም ሳይቆይ ተቋረጠ። ውጤቱ ግን አሁንም ድረስ ዘልቆ ቀጥሏል።
የቴክኖሎጂ ታሪክ ፀሐፊዎቹ ስቱዋርት ደብሊው ሌስሊ እና ሮበርት ካርጎን በአንድ ጽሑፋቸው ላይ "በኤምአይቲ ውስጥ ለሻህ የተነደፈው ፕሮግራም በእስላማዊ አብዮተኞች እጅ ይወድቃሉ ብሎ የገመተ ማንም የለም። የሚያሰለጥኗቸው የኢራን ተማሪዎች እና ፋካልቲው አብዮቱን ይደግፋሉ ተብሎ አልታሰበም" ሲሉ ጠቅሰዋል።
በኤምአይቲ አምሳያ የተቋቋመው የአርያመህር የቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ (AMUT) የአብዮታዊ የተማሪ እንቅስቃሴ ዋና ማዕከል ሆነ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
መጀመሪያ ላይ በአያቶላህ ሩሆላህ ኾሜኒ የሚመራው አዲሱ አገዛዝ የሻህን የኒውክሌር ፕሮጀክቶች ውድቅ አድርጎታል።
ያንንም ተከትሎ በዚህ ዘርፍ የሠለጠኑ ብዙ ፕሮፌሰሮች ከአገር ተሰደዱ።
በፍሎሪዳ ኢንተርናሽናል ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ፕሮፌሰር የሆኑት መሐመድ ሆማዩንቫሽ ከ1979ኙ አብዮት በኋላ ኢራናውያን እጅግ በጣም ፀረ ኒውክሌር እንደነበሩ ያስረዳሉ።
"ፕሮጀክቱ የሻህ ተቀጥላ ችግር መስሏቸው ነበር። እንዲያውም የኒውክሌር መርሃ ግብሩን አቁመው ሙሉ ለሙሉ ከሞላ ጎደል አፈረሱት" ሲሉ ለቢቢሲ ሙንዶ ተናግረዋል።
አክለውም "ኢራናውያን ��ኒውክሌር ኃይል ሙሉ በሙሉ ራሳቸውን አግልለው ለአምስት እና ለስድስት ዓመታት ያህል በዝምታ ውስጥ ነበሩ። ለኤሌክትሪክ ኃይል ጥቅም ላይ ይውላል የሚለውም ኢራን የተትረፈረፈ የነዳጅ ሀብት ስለነበራት እንደ ብክነት ቆጥረውት ነበር" ሲሉ አክለዋል።
ሆኖም የኢራን አብዮት ከጊዜ በኋላ የኒውክሌር ቴክኖሎጂን ዋጋ በመገንዘብ ጥለው የሄዱትን ብዙ ባለሙያዎችን ለመመለስ መሞከር ብቻ ሳይሆን፣ የራሱን ምሥጢራዊ የአውቶሚክ ፕሮግራም ማካሄድ ጀመረ።
ያልተጠበቁ ውጤቶች
ነገር ግን 'አተም ለሰላም' በሌሎች አገሮች የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ግንባታ ላይ እና በአሁኑ የኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብር ላይ ምን ያህል ተጽዕኖ አሳድሯል?
እንደ ሆማዩንቫሽ ገለፃ፣ ከዚህ ተነሳሽነት ጀርባ የአይዘንአወር ስጋት በጦር መሳሪያዎች መስክ የኒውክሌር ቴክኖሎጂን መጠቀም ያለው አንድምታ ነበር።
"በመሆኑም ብዙ አገራት በዚያ መንገድ እንዳይጓዙ ለመከላከል፣ ለሲቪል ዓላማ ሲባል የተወሰነ ደረጃ የኒውክሌር ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ቢሆኑ፣ ይህ በተወሰነ ደረጃ ቁጥጥር ሊደረግበት ይችላል ተብሎ ይታሰብ ነበር፤ ተገቢው ጥበቃም ተዘጋጅቷል" ሲሉ ያክላሉ።
ለምሳሌ አሜሪካ ለአገራት ያቀረበችውን ለዩራኒየም ማብላያ ማንቀሳቀሻ፣ ለላብራቶሪ ፍጆታ ብቻ አከራየች እንጂ አልሸጠችም።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዩናይትድ ስቴትስ በዓለም ዙሪያ በሚገኙ ሰላሳ አገሮች ውስጥ የኒውክሌር ኃይልን ለማጥናት እና ምርምርን ለማካሄድ የረዳችው በዚህ መንገድ ነበር።
ወደ ኋላ መለስ ብለን ስንመለከት ግን ይህ ተነሳሽነት ለኒውክሌር መስፋፋት ምን ያህል አስተዋጽኦ እንዳበረከተ በባለሙያዎች መካከል ስምምነት የለም።
ሆማዩንቫሽ 'አተምስ ፎር ፒስ' የኒውክሌር ቴክኖሎጂን ለሰላማዊ ዓላማ ማስተላለፍ የሚቻልበትን ሁኔታ ፈጥሯል ብሎ መከራከር እንደሚቻል ያምናሉ።
እና አገራት ይህን ቴክኖሎጂ እንዴት መጠቀም እንደሚችሉ ከተማሩ በኋላ በተለያዩ አቅጣጫዎች ለመራመድ የራሳቸውን እርምጃዎች መውሰድ ችለዋል።
ይሁን እንጂ 'አተምስ ፎር ፒስ' ባይኖን ኖሮ አንዳንድ አገራት በኒውክሌር ልማት ረገድ ዛሬ ያሉበት ደረጃ ላይ አይደርሱም ነበር ብሎ መከራከር ቀላል እንዳልሆነ ያምናሉ።
ሌሎች ባለሙያዎች ግን የአይዘንአወር ተነሳሽነት የኒውክሌር መስፋፋትን መደገፉ ግልጽ ነው ብለው ይከራከራሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በጆርጂያ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ፕሮፌሰር የሆኑት ጆን ክሪጅ "ይህ ምን ያህል አደገኛ እንደሆነ እና የ'አተም ፎር ፒስ' ተነሳሽነት እንዴት የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ልማትን እንዳበረታታ እና እንዳሳተፈ የሚያሳዩ ብዙ አዳዲስ ጥናቶች አሉ" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"የሲቪል ኒውክሌር ቴክኖሎጂን ማጋራት ከኒውክሌር ጦር መሳሪያ አንፃር ጉልህ የሆነ አንድምታ አለው። ስለዚያ ምንም ጥያቄ የለም" ሲሉ በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ እንዲሁም በአሜሪካ የውጭ ፖሊሲ መካከል ያለውን ግንኙነት የሚያጠኑት ክሪጅ ተናግረዋል።
ይህንን አመለካከት የሚጋሩት እንደ ሕንድ እና ፓኪስታን ያሉ አገራትንም ይጠቅሳሉ።
የአውቶሚክ ቦምብ የሠሩ አገራት የመጀመሪያዎቹ የኒውክሌር ሳይንቲስቶቻቸው የሠለጠኑት በ'አተምስ ፎር ፒስ ኢኒሼቲቭ' ስር ነው።
"በሳይንስ ወይም በኢንዱስትሪ የኒውክሌር ቁሳቁሶችን ለወታደራዊ አገልግሎት እንዲውል የተደረጉበት አጋጣሚዎች ብዙ ናቸው። እነዚህ በ'አተምስ ፎር ፒስ' ስር በተገኙት መሳሪያዎች እና ፅንሰ ሀሳቦች መሠረት የደረጁ ናቸው። አርጀንቲና፣ ብራዚል፣ ታይዋን እና ደቡብ ኮሪያ ለዚህ ምሳሌዎች ናቸው" ሲሉ ፒተር አር ላቮይ ጽፈዋል።
የኢራንን ጉዳይ በተመለከተ፣ ከእስራኤል እና ከአሜሪካ የቦምብ ጥቃት በኋላ ከኒውክሌር መርሃ ግብሯ ምን ያህሌ እንደቀረ፣ የወደፊት ዕጣ ፈንታዋ ምን እንደሆነ በግልጽ የሚታወቅ ነገር የለም።















