አሜሪካ የውጭ አገር ጎብኝዎችን የአምስት ዓመት የማኅበራዊ ሚዲያ ታሪክ ልትጠይቅ እንደምትችል ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአዲሱ የትራምፕ አስተዳደር ዕቅድ መሠረት ዩናይትድ ኪንግደምን ጨምሮ የበርካታ አገራት ጎብኝዎች ወደ አሜሪካ ለመግባት የአምስት ዓመት የማኅበራዊ ሚዲያ ታሪክ ሊጠየቁ እንደሚችሉ የአገሪቱ ባለሥልጣናት ገለጹ።
አዲሱ ቅድመ ሁኔታ ያለ ቪዛ ለ90 ቀናት አሜሪካን ለመጎብኘት መስፈርቱን የሚያሟሉ የበርካታ አገራት ዜጎች ላይ ተፅዕኖ ሊያደርስ የሚችል ነው።
እነዚህ ዜጎች የጉዞ ፈቃድ ለማግኘት የሚያስችላቸውን የኤሌክትሮኒክ ቅፅ (ኤኤስቲኤ) መሙላት ስለሚጠበቅባቸው አዲሱ የጉዞ ዕቅድ የሚጠይቀውን የማኅበራዊ ሚዲያ ታሪክ ሳያካትቱ ማለፍ አይችሉም።
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ጥር ወር ላይ ወደ ዋይት ሐውስ ከገቡ በኋላ ብሔራዊ ደኅንነትን እንደ ምክንያት በመጥቀስ የአገሪቷን የድንበር ቁጥጥር አጥብቀዋል።
ተንታኞች በበኩላቸው አዲሱ ዕቅድ ጎብኝዎች ላይ መሰናክል እንደሚፈጥር እና የዲጂታል መብታቸውን እንደሚጋፋ ተናግረዋል።
ትራምፕ ግን ዕቅዳቸው በአሜሪካ የቱሪስት ፍሰትን ሊቀንስ እንደሚችል ተጠይቀው "እንደማያሳስባቸው" ገልጸዋል።
ፕሬዚዳንቱ ረቡዕ ዕለት ሲናገሩ " ጥሩ እየሰራን ነው። የምንፈልገው ሰዎች እዚህ መጥተው ሰላም እንዲሆኑ ነው። ሰላም እና ደኅንነት ነው የምንፈልገው። ወደ አገሪቷ መግባት የሌለባቸውን ሰዎች እንዲገቡ አለመፍቀዳችንን ማረጋገጥ አለብን" ብለዋል።
በሚቀጥለው የአውሮፓውያኑ ዓመት አገሪቷ ከካናዳ እና ሜክሲኮ ጋር በመሆን የወንዶች እግር ኳስ የዓለም ዋንጫ ስለምታዘጋጅ እንዲሁም በአውሮፓውያኑ 2028 በሎስ አንጀለስ ከሚካሄደው ኦሎምፒክ ጋር በተያያዘ ወደ አገሪቷ በርካታ ቱሪስቶች እንደሚጎርፉ ይጠበቃል።
ሆኖም በአገር ውስጥ ሚኒስቴር እና በጉምሩክ እና ድንበር ጥበቃ መሥሪያ ቤት የተዘጋጀው አዲሱ ዕቅድ በዚህ ላይ ተፅዕኖ ሊያደርስ እንደሚችል የቱሪዝም ባለሙያዎች እየገለጹ ነው።
በአሜሪካ መንግሥት ይፋዊ ጆርናል ላይ የታተመው ዕቅዱ በኤሌክትሮኒክ የጉዞ ቅጽ የሚሞሉ ሰዎች ባለፈው አምስት ዓመት የተገለገሉበትን ማኅበራዊ ሚዲያ እንዲሰጡ ይጠይቃል።
ሆኖም ምን ዓይነት ልዩ መረጃዎች እንደሚፈለጉ ዝርዝር መረጃዎችን አልሰጠም።
አሁን ላይ ሥራ ላይ ያለው በኦንላይን የሚሞላ የጉዞ ፈቃድ ቅጽ (ኢኤስቲኤ) ከተጓዦች የሚጠይቀው ውስን መረጃዎችን ሲሆን በአንድ ጊዜ 40 ዶላር እንዲከፍሉ ብቻ ነው የሚጠይቀው።
በዚህም ዩናይትድ ኪንግደም፣ አየርላንድ፣ ፈረንሳይ፣ አውስትራሊያ እና ጃፓንን ጨምሮ የ40 አገራት ዜጎች ይህን አገልግሎት ማግኘት የሚችሉ ሲሆን በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ በፈለጉት ጊዜ አሜሪካን እንዲጎበኙ ይፈቅድላቸዋል።
አዲሱ ዕቅድ ግን የማኅበራዊ ሚዲያ መረጃዎችን ከመሰብሰብ በተጨማሪ አመልካቾች ባለፉት ከአምስት እስከ 10 ዓመታት በተከታታይ የተጠቀሙበትን የስልክ ቁጥር እና የኢሜይል አድራሻ እንዲሰጡ እንዲሁም ከቤተሰብ አባላታቸው መረጃዎች እንዲሰበሰብ ይጠይቃል።
ሰነዱ ጥር ወር ላይ ትራምፕ ያስተላለፉትን እና "አሜሪካን ከውጭ አገር ሽብርተኞች እና ሌሎች የብሔራዊ እና የማኅበረሰብ ደኅንነት ስጋቶች መጠበቅ" የሚለውን ፕሬዚደንታዊ ትዕዛዝ ይጠቅሳል።
ከጎብኝዎች የጉዞ መረጃ አሰባሰብ ጋር በተያያዘም ለ60 ቀናት የሕዝብ አስተያየቶች እንዲሰጡበት ይጋብዛል።
ሆኖም አሁን ላይ ወደ አሜሪካ ለሚገቡ መንገደኞች ምንም የተለወጠ ነገር አለመኖሩን የጉምሩክ እና ድንበር ጥበቃ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
" ይህ የመጨረሻው ሕግ አይደለም። የአሜሪካ ዜጎችን ደኅንነት ለመጠበቅ አዲስ የፖሊሲ አማራጮች እንዲኖሩ ውይይት ለመጀመር የሚያስችል የመጀመሪያ እርምጃ ነው" ብለዋል ቃል አቀባዩ።
የዲጂታል መብት ድርጅት ኤሌክትሮኒክ ፍሮንቲየር ፋውንዴሽን ባልደረባ ሶፊያ ኮፕ ዕቅዱን የተቹት ሲሆን " የሰላማዊ ሰዎችን ነጻነት አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል" ሲሉ ለኒውዮርክ ታይምስ ተናግረዋል።
ፍሮግሜን የተባለ የኢሚግሬሽን ተቋም በበኩሉ መንገደኞች የጉዞ ፈቃድ ለማግኘት ለረዥም ጊዜ እንዲጠብቁ ሊያደርግ ይችላል ብሏል።
የትራምፕ አስተዳደር ቀደም ብሎ የተማሪ ቪዛ ወይም የሥራ ቪዛ (H-1B ) የሚያመለክቱ የውጭ ዜጎች የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾችን እንደሚፈትሽ አስታውቆ ነበር።
የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ የአመልካቾችን እና ቤተሰባቸውን የኦንላይን እንቅስቃሴ እንደሚገመግም ጠቅሶ፣ ይህን ለማድረግም አመልካቾች የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾቻቸውን ከግላዊ ወደ ሕዝብ ዕይታ እንዲለውጡ አሳስቦ ነበር።
በአሜሪካ ኤምባሲ እና በሜክሲኮ ግዛት ቆንስላ ድረ ገጽ የወጣው ማስታወቂያም የቪዛ አመልካቾች ባለፉት አምስት ዓመታት ሲጠቀሙባቸው የነበሩትን ሁሉንም የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾቻቸውን ስም እና ሊንክ መዘርዘር እንደሚገባቸው ገልጿል።
ያልተጠቀሰ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጽ ካለም የቪዛ ክልከላን ሊያስከትል እንደሚችል አስጠንቅቋል።
የተማሪዎችን ቪዛ በተመለከተም አንድ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ባለሥልጣን " ይህ አገራችንን ደኅንነቷ የተጠበቀ እንደሚያደርግ አሜሪካውያን ይጠብቃሉ። የትራምፕ አስተዳደርም በየዕለቱ እያደረገ ያለው ይህንን ነው" ብለዋል።
ባለሥልጣናትም "ለአገር ድኅንነት ስጋት የሆኑ እና ሽብረተኛ ተብለው የተፈረጁ ቡድኖችን የሚያስተዋውቁ ፣ የሚደግፉ እንዲሁም ፀረ ሴሚያዊ ትንኮሳ እና ጥቃት የፈፀሙትን" እንዲለዩ ተነግሯቸዋል።
የትራምፕ አስተዳደር እየወሰደ ባለው እርምጃ የድንበር ጥበቃን ለማጠናከር የጉዞ እገዳ የጣለባቸው በአፍሪካ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ እና ካረቢያን የሚገኙ 19 አገራት ቁጥር ክፍ ሊል እንደሚችልም አመልክቷል።
ውሳኔው የመጣው አንድ አፍጋኒስታናዊ በዋሽንግተን ዲሲ ሁለት የብሔራዊ ጥበቃ አባላት ላይ ተኩስ ከፍቶ ጉዳት ካደረሰ እና የአንደኛዋን ሕይወት በመቅጠፍ ከተከሰሰ በኋላ ነው።
ቀደም ብሎ ባለሙያዎች በትራምፕ አስተዳደር ሥር የተዋወቁት ጉዞን በተመለከቱ የሚወጡ የፖሊሲ ለውጦች በአሜሪካ የቱሪዝም ኢንደስትሪ ላይ ተፅዕኖ እንዳሳደሩ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ የዓለም የጉዞ እና የቱሪዝም ምክርቤት አሜሪካ በአውሮፓውያኑ 2025 ከ184 አገራት ውስጥ ጎብኝዎች የሚቀንሱባት ብቸኛዋ አገር እንደምትሆን ገልጾ ነበር።
የጉዞ እገዳዎች ብቻም ሳይሆኑ ሌሎች የትራምፕ አስተዳደር ፖሊሲዎች በአገሪቱ ቱሪዝም ላይ ተፅዕኖ አሳድረዋል።በርካታ ካናዳውያን በትራምፕ የተጣለው ታሪፍ ላይ ተቃውሟቸውን ለመግለጽ ወደ አሜሪካ ላለመጓዝ አድመዋል።
እስከ ኅዳር ወር ድረስ ባሉት አስር ተከታታይ ወራትም ወደ አሜሪካ የሚጓዙ ካናዳውያን ቁጥር ቀንሷል።
እንደ የአሜሪካ የጉዞ ማኅበር ከሆነ ከዚህ በፊት ካናዳውያን ወደ አሜሪካ ከሚገቡ የውጭ ጎብኝዎች አንድ ሦስተኛውን ይሸፍኑ የነበረ ሲሆን በዓመት ከ20 ቢሊዮን ዶላር በላይ ያወጣሉ።















